ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ ከ193 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

  • PDF

አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2004/ዋኢማ/ - ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ ከ193 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተገኘው የ193 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የአግሮፕሮሰሲንግና የፋርማሲቲካልስ ምርቶችና የኬሚካል ውጤቶችን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክ ነው።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከዘርፉ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 334 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ጠቁመው እስካሁን የተገኘው ገቢ ከባለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ56 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

ከተገኘው ገቢ ውስጥ 86 ሚሊዮን 883 ሺ ዶላር ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ 63 ሚሊዮን 403 ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ 37 ሺ 443  ከአግሮ-ኘሮሰሲንግ ምርቶችና 5 ሚሊዮን 737 ሺ 800 ዶላር ደግሞ ከፋርማሲቲካልስና ከኬሚካል ውጤቶች መገኘቱንም ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱ ከማኑፋክቸሪንግ ምርቶች የውጭ ምንዛሪ የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ መላኩ የሀገር ውስጥ ምርቶች ከውጭ የሚገባውን እንዲተኩ ለማድረግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘርፉን ለማሳደግም ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የግብዓት አቅርቦትን በማመቻቸት፣ የምርትና የገበያ ትስስርን በመፍጠር፣ የሎጂስቲክስ የአቅም ግንባታና የፋይናንስ ብድር የማስተባበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ መላኩ ተናግረዋል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 153 guests