አክራሪዎችን ለማበረታታት የተላለፈ መልዕክት
ኢብሳ ነመራ
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፓርቲያቸውን መሰረታዊ መርሆች፣ ፖሊሲዎችና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከመርህና ፖሊሲዎች አኳያ የሚይዙዋቸውን አቋሞች በተለይ ለአባሎቻቸው የሚያስገነዝቡበትና የሚያሳውቁበት ልሣን አላቸው፤ ጋዜጣ፣ መፅሄት …፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በሕገመንግስት ተረጋግጦ፣ ፓርቲዎች በፈቀዱት አመለካከትና አቋም ተደራጅተው በይፋ በሚንቀሣቀሡበት፣ የፖለቲካ ሥልጣን ለመረከብና ለመጋራት በሚፎካከሩበት አገር፣ የእነዚህ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችም ልሳናት ዓላማ ይህ ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ አባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ፓርቲያቸው ምን አይነት ፖሊሲና አቋሞች እንዳሉት የነጠረ ግንዛቤ ይኖራቸዋል፡፡ ሕዝቡም ፓርቲው ምርጫ ውስጥ ሲገባ፣ የሚያቀርቡለት ፖሊሲዎችና አቋሞች ላይ ግልፅ እይታ እንዲኖረው ስለሚያግዝ ፓርቲው በሰላማዊ መንገድ የሕዝብ ድጋፍና የምርጫ ድምፅ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የሕዝብን ድምፅ ማግኘት ሳይችል ሲቀርም ራስን የመፈተሽና የማጠናከር ዕድል ይሰጠዋል፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ - አንድነት ልሣን የሆነው “ ፍኖተ ነፃነት” የተባለ ጋዜጣ ግን ከዚህ ተገቢ የሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ ልሣን ዓላማና ተግባር ያፈነገጠ አካሄድ የሚታይበት ሆኖ አግኘቼዋለሁ፡፡
ይህ እንደ ፓርቲ ልሳንነቱ በቀዳሚነት ለአባላቱ ከመከፋፈሉ ወይም ከመሰራጨቱ ይልቅ በጋዜጣ አዟሪዎች እጂ የሚቸበቸበው “ፍኖተ ነፃነት” ፓርቲው ምን አይነት ፖሊሲዎችን እንደሚከተል የሚገልፅ፣ ፖሊሲውን ከተጨባጭ ሁኔታና ከመርሕ አኳያ የሚተነትን ሐሳብ አስተናግዶ አያውቅም ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባት የፓርቲውን ፖሊሲ አውቃለሁ የሚል ከተገኘ፣ በምርጫ ወቅት የገለፁትን የሚያስታውሱ ብቻ ናቸው፡፡
ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ወገን የተነሳን ቅሬታ “ ቅሬታው ተገቢ ነው ወይንስ አይደለም፣ ከሕገመንግስቱ አኳያ ምን ይመስላል? በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ላይ ምን እንደምታ አለው?” የሚለው ጉዳይ ሳያስጨንቀው ያለወጉ አጣምሞ በመተርጎም እያራገቡ ማግለብለብ ይቀናዋል፡፡ አንዳንዴም እዚህና እዚያ ከሚወረውራቸው ቅንጭብጭብ ሃሳቦቹ ቃርመን ከተረዳነው ወይም የተረዳን ከሚመስለን አቋሙም ጋር ጭምር የሚጋጩ አቋሞችን የሚያንፀባርቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በአጠቃላይ ሕዝብን ሕገወጥ ለሆነ የመንግስት ለውጥ እንቅስቃሴ በሚያነሳሳ አኳኋን የመንጫጫት ክፉ አባዜ ዋነኛው መገለጫው ነው፡፡
ፍኖተ ነፃነት አና ወይም አንድነት ፓርቲ አንድ ሰሞን ህዝብን ለተቃውሞ ያነሳሳል ብለው ያሰቡትን አጀንዳ፣ ያለምንም የመርሕ ትንታኔ ውሸት ጭምር በመቀላቀል ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ ለመክተት ሲያስጮሁ ይቆዩና የትም እንደማያደርሳቸው ሲረዱ፣ ያለምንም ሀፍረት ወደ ሌላ ሰሞነኛ ጉዳይ ይዘላሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ እዚህ ደርሰል፡፡
ይህ የአንድነት ልሳን የሆነው “ፍኖተ ነጻነት” ጋዜጣ ስርጭት ከጀመረበት ግዜ አንስቶ እስካሁን ሲከተል የቆየውን አካሄድ ጉዳዩን ለማጤን ለሚሹ ይህን ያህል አስታውሼ፣ ከአንድ የጋዜጣው እትም ላይ ይህንኑ ባሕሪውን የሚያሳይ ጉዳይ ወስጄ መመልከት ላይ ላተኩር፡፡
በዚሕ ፅሁፍ ላይ አነሳው ዘንድ የሸነቆጠኝ ፍኖተ ነፃነት የማክሰኞ 16፣ 2004 ዕትሙ ላይ የሰፈረ አንድ ጉዳይ አጋጥሞኛል፡፡ ጋዜጣው በዚህ ዕትሙ ከቅርብ ግዜ ወዲህ መነጋገሪያ የሆነውን በእሥልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተፈጠረ አለመግባባት የሚመለከት ዜናና መጣጥፍ አውጥቷል ፡፡
ፍኖተ ነፃነት በሚያዝያ 16 ዕትሙ ይህን ጉዳይ በተመለከተ «መንግስት በሙስሊሙ ማህበረሰብ እንቅስቃሴ መደናገጡን አንድ የመንግስት ሰነድ አጋለጠ» የሚል ዜና፣ እንዲሁም ሰለሞን ስዩም በተባሉ ፀሐፊ «የሃይማኖት ነፃነትና በአብዮታዊ ዴሞክራሲያ ሁሉንም የመቆጣጠር አባዜ ግጭት» በሚል የቀረበ ፅሁፍ አስነብቦናል፡፡ “መንግስት በሙስሊሙ ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ተደናገጠ” በሚል በቀረበው ጽሁፍ ልጀምር፡፡
መንግስት በሙስሊሙ እንቅስቃሴ መደናገጡን በስውር በተገኘ ሰነድ ተጋለጠ የሚለውን የተመለከተ ማንኛውም ግለሰብ አንድ የሚፈጠርበት ስሜት አለ፡፡ ይህም “ከሐይማኖት ጋር በተገናኘ፣ መንግስት ሕገ-መንግስቱን ተላልፎ በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የወሰነበት አለያም ጣልቃ የገባበት አንዳች ምስጢር ተገኘ” የሚል ነው፡፡
ይህ “የመንግስትን መደናገጥ” አጋለጠ የተባለና ለከፍተኛ አመራሮች እንደተሰጠ ከተነገረ ሰነድ በዜናው ላይ የተጠቀሰ ሃሳብ ግን ሕገ-መንግስቱ ላይ ከሰፈረው፣ በተለያየ ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት በይፋ ከገለጹት የተለየ አንዳችም ስውር ሚስጥር አልያዘም፡፡
የፍኖተ ነፃነት ዜና ተገኘ ያለን ምስጢራዊ ሰነድ «መንግስት በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ በሰላምና በሕገ መንግስቱ ዙሪያ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር የዜጎችና የመንግስት መብትም ግዴታም ነው» በሚል ርዕስ ለውውይት የተዘጋጀ መሆኑን ነግሮናል፡፡
አንድነት ወይም የፍኖተ ነፃነት አዘጋጆች የዚህ አይነት ሰነድ አግኝተዋል ብለን ብናስብ እንኳን፣ የሰነዱ አጀንዳ መንግስት በሕ-ገመንግስት የተጣለበትን የሕዝቡንና የአገሪቱን ሰላም የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችለውን ተግባር እያከናወነ ከመሆኑ ያለፈ የሚያሳየው እንዳችም ነገር የለም፡፡
የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው ሕገ-መንግስት ሁሌም መከበር አለበት፤ የአገሪቱና የሕዝቧም ሰላም መረጋገጥ አለበት፡፡ ይህ ጉዳይ “መሆን አለበት፣ የለም የለበትም” ለሚል ድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ይህን ሕገ-መንግስትና ሰላም የማስከበር ኃላፊነት ደግሞ በሕዝብ ውክልና ስልጣን የተሰጠው መንግስት ብቻ ነው፡፡ ሕገ-መንግስቱን የሚጥሱና ሰላም ሊያናጉ የሚችሉ ችግሮች ሲያጋጥሙ ይህን በይፋ አሳውቆ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር መንቀሳቀሱ፣ የተጣለበትን ሐላፊነት ጠንቅቆ የተገነዘበ፣ የሕዘብን የበላይነት የተቀበለና ህዝቡን የሚያከብር መንግስት መገለጫ ነው።
በመሆኑም የህዘብን ሃላፊነት የተረከበው መንግስት የሰየማቸው ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ ባለስልጣናት ተወያዩበት የተባለው አጀንዳ፣ መንግስት ለህዝብ ያለውን ታማኝነት፣ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ይህም በውክልና ስልጣን የሰጠው ሕዝብ መንግስት እንዲኮራ የሚያደርግ ነው።
የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 27 (የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት) በሚል ርዕሰ አንቀጽ 5 ላይ “ሐይማኖትና እምነት የመግለፅ መብት ሊገደብ የሚችለው የህዝብን ደህንነት፣ ሰላምና ጤናን፣ ትምህርትን የህዝብን የሞራል ሁኔታ የሌሎች ዜጎችን መሰረታዊ መብቶች፣ ነፃነቶች እና መንግስት ከሃይማኖት ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕጎች ይሆናል” እንደሚል አስተውሉ ።
ወደዜናው ዝርዝር እንዝለቅ። አንድነት እና/ወይም ፍኖተ ነፃነት አገኘሁት ያለው ሰነድ፤ “አገራችን የራሳቸውን ሃይማኖት ሕገ-መንግስታዊ ሽፋን ሰጥተውና ይፋ የሃገሪቱ ሃይማኖት አድርገው የሌላውን ያረከሱ መሪዎች የነበሩበትን ፀረ -ሁሉም ዓይነት ሃይማኖቶች አቋም በነበረው የደርግ ስርዓት ውስጥም አልፋለች።” እንደሚል ተጠቅሷል፡፡ ይህ በስውር የተፈፀመ ማንም የማያውቀው ምስጢር ሳይሆን፣ ሁላችንም የምናስታውሰው የቅርብ ግዜ ታሪካችን አንዱ አስክፊ ክፍል ነው፡፡
ሰነዱ፣ “ቀደምት ስርዓቶች በተከተሉዋቸው የሃይማኖት ጭቆናዎች ምክንያት የተፈጠሩና ስር ሰደው የቆዩ የፍትህ መጓደሎችን ለማረምም እጅግ አበረታች እንቅስቃሴ በማድረግ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። የእምነት ቦታዎችን ለመገንባት የነበሩ ችግሮችን በመቅረፋችን ባለፉት 20 አመታት በሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ የእምነት መዳረሻ ቦታዎች በከፍተኛ መጠንና ፍጥነት ተስፋፍተዋል፡፡” እንደሚልም ተጠቅሷል፡፡ይህም በይፋ የሚታይ የቅርብ ግዜ ታሪካችን በጎ ገፅታ ነው፡፡
ይህ “መንግስት መደናገጡን” ያሳያል በሚል ፍኖተ ነፃነት በጠቀሰው ሰነድ፣ የተገለፀው ሃሳብ መንግስት በህገመንግስቱ አንቀፅ 27 (የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት´ ንኡስ አንቀፅ 1. “ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት አለው። ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለፅ መብትን ያካትታል” በሚል የሰፈረው በአገሪቱ በተግባር መረጋገጡን ያመለክታል።
ፍኖተ ነፃነት |ምስጢራዊ´ ያለው ሰነድ “ማንም እንደሚያውቀው፣ በእስልምና እምነት ስም የሚንቀሳቀስ ነገር ግን የእሰልምና መሰረቶችን ከመናድ ጀምሮ ፀረ ሕገመንገስት አቋሞች የሚያራምድ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ አለ” እንደሚል ጠቅሶ፣ መንግስት በአደባባይ “ህገመንግስታዊ ስጋት” ብሎ በተደጋጋሚ በይፋ የሚገልፀውን ነገር በድብቅ አገኘሁት ብሎ ሹክ ብሎናል።
ይህንን ፀረ ሕገ-መንግስት አቋም የሚያራምድ ቡድን በተመለከተ፣ ሰነዱ ካዋርጂያና ዋሃቢያ የተባለ ቡድንን እንደሚጠቅስ፣ ሁለቱ ቡድኖች በፀረዴሞክራሲና ፀረ ሕገ-መንግስት አቋማቸው ተመሳሳይ መሆናቸውን፣ ከመሰረቱ “ሃይማኖት ከመንግስት ተነጥሎ መሄድ አይችልም፤ መንግስትም ሐይማኖትን ማገልገል አለበት” የሚል አቋም አላቸው እንደሚል ይገልፃል። መንግስት በአገሪቱ የዚህ አይንት እንቅስቃሴ ለመኖሩ ማስረጃ እንዳለው፣ አካሄዱ የሃይማኖትና የመንግስትን መለያየት ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ የሚፃረር መሆኑን በተደጋጋሚ ለሕዝብ አሳውቋል፡፡
አያይዞም “ይህ አቋም እንደኛ ባለ የበርካታ ሐይማኖቶች ቤት በሆኑ ሃገሮች ቀርቶ ሙሉ በሙሉ ሙስሊም በሆኑትም የሺአዋችን፣ የሱፊዎችን … ህልውና በማጥፋት ጭምር በመፈታተን የሚታወቅ መሆኑን፤ አቋሙ ከእስልምና ጋር ምንም ዝምድና የሌለው ፤ ከዚህ ይልቅ የፖለቲካ ይዘት እንዳለው፡ ይህን አቋም መተቸት እስልምናን መተቸት ሊሆን እንደማይችል” መግለፁን ጠቅሷል። ከላይ የተነሳውን በይፋ የተገለፀ የመንግስት አቋም የሰማ ማንኛውም ሰላማዊ ዜጋ ከዚህ የተለየ አቋም ሊይዝ እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡
ልብ በሉ መንግስት በእስልምና እንቅስቃሴ መደናገጡን ያሳያል ተብሎ በፍኖተ ነፃነት የቀረበው “ምስጢራዊ ሰነድ” መንግስት አንዳችም ቦታ የሚያስደነግጥ ጉዳይ ገጥሞት ሕገ-መንግስታዊ ያልሆነ የዘፈቀደ እርምጃ ሊወሰድ እንዳሰበ አያሳይም።
ከዚህ ይልቅ በህገመንግስቱ (የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት በሚለው ርዕስ አንቀፅ 11 ንኡስ አንቀጽ 1፣ 2፣ና 3 መንግስትና ሐይማኖት የተለያዩ ናቸው፣ መንግስታዊ ሐይማኖት አይኖርም፣ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚለውን በጥንቃቄና በተገቢው መንገድ እያስፈፀመ መሆኑን በግልፅ ያሳያል። ሕገ መንግስቱን የሚፃረርና የአገሪቱን ሰላም የሚያናጋ ጉዳይ አጋጥሞት ቢደናገጥ ደግሞ ተገቢ ነው፤ ከዚህ በላይ መንግስትን ሊያሳስብ የሚችል ጉዳይ ባለመኖሩ፡፡ ተደናግጦ እንኳን ቢሆን ሕገ-መንግስቱንና የሕዘቡን ሰላም ለማስጥበቅ ያለውን ንቃትና ቁርጠኝነት እንጂ ስህተት መስራቱን አያመለክትም፡፡
ከወርጂያ ከዚህ ቀደም በጅማና በአካባቢው አንዳንድ ወረዳዎች በክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ ከተፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ጀርባ የነበረ ቡድን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አክራሪ ቡድኖቹ በተለይ ከእኛ የተለየ አስተምህሮ ይክተላሉ ያሉዋቸውን ሙስሊሞች መስጊዶቻቸውን አቃጥለዋል፣ መቃብር ምሰው አፅም አውጥተው ጥለዋል፣ ሰዎችን ደብድበው ከቀያቸው አፈናቅለዋቸዋል፡፡ በዚህ ድርጊታቸው ቡድኖቹ የሌሎች ሐይማኖቶችና የተለየ የሚሉትን የእስልምና ሓይማኖት አስተምህሮ አማኞችን ሕገ-መንግስታዊ መብት እንደማይቀበሉ በተግባር አረጋግጠዋል።
የእነዚህ ቡድኖች አላማ የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች በሕገ-መንግስት በተረጋገጠላቸው የእምነት ነፃነት መሰረት እንዲኖሩ ማድረግ ሳይሆን በዋነኝነት የመንግስት ስልጣን ጥያቄ ነው፤ ኢስላማዊ መንግስት የመመስረት ጥያቄ፡፡ በመሆኑም ይህን ሕገ-መንግስቱን የሚፃረር አቋም መንግስት መከላከል አለበት።
እንግዲህ ዋናው ጉዳይ ፍኖተ ነፃነት “ምስጢራዊ ሰነድ ” አገኘሁ በሚል “ መንግስት ተዳነገጠ ” ብሎ መጮህ ለምን ፈለገ? አገኘሁት ባለው ሰነድ ላይ ተጠቅሶ እንዳየነው ተገቢና ህጋዊ የመንግስትን አካሄድ ከማሳየት ያለፈ አንድም ህዝብን ቅር የሚያሰኝና የሚያስቆጣ ነገር የለውም። የአንድነት ልሳን ያሰበው፤ ጉዳዩን በሰነዱ ላይ በሰፈረው ቁም ነገር ሳይሆን በዜናው ርዕስ ላይ እንዳጮኽው “መንግስት ተደናግጧል” ብሎ አክራሪ ቡድኖቹን “በርቱ ግፉ” በሚል መበረታታት እንዲያድርባቸው ማድረግ ነው፤ በቃ።
| < Prev | Next > |
|---|


