የማላዊ ፕሬዚዳንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ሻሩ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 25/2004 (ዋኢማ) - የቀድሞው የማላዊ ፕሬዚዳንት ቢንጉ ሙታሪካ እንደሞቱ በቅርቡ የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን የተረከቡት ጆይስ ባንዳ ተቀናቃኛቸው እንደነበሩ ሲነገርላቸው የቆዩትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒተር ዋሙታሪካን መሻራቸውን ቢቢሲ አመለከተ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢንጉ ዋሙታሪካ ወንድም የሆኑት ፒተር ሙታሪካ ወደፊት ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ሁኔታው ሲመቻችላቸው እንደነበር ታውቋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢንጉ ዋሙታሪክ ይመሩት የነበረው ገዢ የፖለቲካ ፓርቲ አባልና የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን ጆይስ ባንዳን የሻሯቸውም በዚህ ዓላማ መሠረት እንደሆነ ታውቋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢንጉ ዋሙታሪካ አገሪቱን ለስምንተ ዓመታት መርተዋል።

ይሁን እንጂ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢንጉ ዋሙታሪካ እኤአ ሚያዚያ 5 ቀን 2012 በድንገት ሲሞቱ ሁኔታው ተለውጧል። ቢንጉ ዋሙታሪካ እንደሞቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወንድማቸውና ደጋፊዎቻቸው የቀድሞዋን ምክትል ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን መምጣት እንደሚያደናቅፉ ተሰግቶ እነደነበር ቢገለፅም ያ ሳይሆን ቀርቶ የ62 ዓመቷ ጆይስ ባንዳ በሟቹ ፕሬዚዳንት ስፍራ ፕሬዚዳንት በመሆን ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

እ.ኤ.አ ከ2009 አንስቶ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆይስ ባንዳ የሹምሽር እርምጃ የወሰዱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሥርዓተ ቀብር በትውልድ መንደራቸው ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ከተፈፀመ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል። ጆይስ ባንዳ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ሥልጣና ቸውንና ከገዢው የፖለቲካ ፓርቲ «ዴሞክራቲክ ፕሮግሬሲቭ ፓርቲ» አባልነታቸው እንዲወጡ የተደረጉት እኤአ 2010 እንደሆነ ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳ ሰሞኑን በካቢኔያቸው ውስጥ ባካሔዱት ሹምሽር የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ቢንጉ ዋሙታሪካ ወንድም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒተር ዋሙታሪካን ጨምሮ በርካታ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የቅርብ ረዳቶች ከሥልጣን የተወገዱ ሲሆን፤ ባልተጠበቀ ሁኔታ አዳዲስ ሚኒስትሮች መሾማቸው ተሰምቷል። በዚህም መሠረት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባሊኪ ሙሉዚ ልጅ አውስቲን አቱፔሌ ሙሉዚ የኢኮኖሚ ፕላኒንግና የልማት ሚኒስትር ሆነዋል። የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ቢንጉ ዋሙታሪካ አምባገነናዊ ባህሪ አሳይተዋል የሚል ነቀፋ በመሰንዘራቸው ታስረው የነበሩት የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ አራማጅ ጠበቃ ራልፍ ካሳምባሊ በፍትህ ሚኒስትርነት መሾማቸው ተገልጿል።

በማላዊ የተደረገው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ብዙዎቹን እንዳስደነቀ ተገልጿል። የ62 ዓመቷ ደይስ ባንዳ በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን መያዛቸውን በማስመልከት ሰንደይ ታይምስ የተባለው የማላዊ ጋዜጣ ባወጣው ጽሑፍ የሥልጣን ሽግግር ዴሞክራሲያዊ ባህል በማላዊ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ጭምር ስር መስደዱን አመላካች እንደሆነ ገልጿል። ጋዜጣው አገሪቱ ከምትገኝበት የኢኮኖሚ ችግር አኳያ አዲሷ ፕሬዚዳንት ሁኔታውን ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸውም ጨምሮ አስታውቋል።

ቀደም ሲል የቀድሞው ፕሬዚዳንት የተከተሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ የዓለም ባንክን፣ ሌሎች አበዳሪ ድርጅቶችና አጋሮች ድጋፍ እንዲቀንሱ ማድረጉ ታውቋል።

እንደተጠቀሰው ኢኮኖሚውንና የሥልጣን መተካካትን በሚመለከት በተፈጠረ ልዩነት ምክንያት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢንጉ ዋሙታሪካ የገዢው የፖለቲካ ፓርቲ አባልና ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን ጆይስ ባንዳን ከሥልጣን ማስወገዳቸው ተገልጿል። ጆይስ ባንዳ ከሥልጣን ቢወገዱም በራሳቸው የሚመራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሥርተው መንቀሳቀሳቸው አልቀረም። በኋላ የቀድሞው ፕሬዚዳንት በድንገት ሲሞቱ የቀድሞዋ ምክትል ፕሬዚዳንት የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን የሚረከቡበት ሁኔታ ተፈጠረ።

ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳ ሥልጣን በያዙ ማግስት ዓለም አቀፍ ለጋሾችና የልማት ተቋማት ማላዊ በአዲስ አቅጣጫ ለምታካሒደው የልማት ጥረት ድጋፍ እንዲሰጡ መጠየቃቸው ተገልጿል ሲል አዘ ዘግቧል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 159 guests