ባን ኪ-ሙን በበርማ መልካም ጅምር መኖሩን አረጋገጡ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 25/2004 (ዋኢማ) - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ-ሙን በበርማ የቀድሞው ወታደራዊ መንግሥት ስፍራውን በጠቅላላ ምርጫ አሸንፎ ለመጣ የሲቪል መንግሥት ከለቀቀ በኋላ አገሪቱን ለመጐብኘት የመጀመሪያ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ሆነዋል። ዋና ጸሐፊው በሰሞኑ የበርማ ጉብኝታቸው ሂደት ከመንግሥቱ መሪዎች፣ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፣ እንዲሁም ከፓርላማ አባላት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት መግለጫ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር የማድረግ ሂደት በመጀመር ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጋር እንደተቀላቀለች መግለፃቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ ከትናንት በስቲያ በበርማ ዋና ከተማ ውስጥ በሰጡት መግለጫ፣ በአገሪቱ ውስጥ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተጀመረው ሽግግር ተስፋ ሰጪ መሆኑን አመልክተው፣ ሂደቱ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል የማድረጉ ሁኔታ ግን ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። ዋና ጸሐፊ ባን ኪ-ሙን በቅርቡ አዲስ የተመረጠው ፓርላማ ሲከፈት በቃለ መሐላ አፈፃፀም ረገድ በአውንግ ሳን ሱኪ በሚመራው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲና በፓርላማው አመራር መካከል የተፈጠረው ልዩነት መፍትሔ እንደሚያገኝ ያላቸውን እምነት መግለፃቸው ታውቋል።
በርማ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ከጀመረችበት በተለይም በኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ በሆኑት ዕውቅ የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ አራማጇ አውንግ ሳን ሱኪ የሚመራው «ናሽናል ሊግ ፎር ዴሞክራሲ ኤንኤስዲ» የተባለው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ራሳቸውንና 42 አባሎችን በፓርላማ አባልነት ለማስመረጥ ከቻለበት ጊዜ ወዲህ በርማን ሲጐበኙ ባን ኪ-ሙን ሦስተኛው ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸው። ከእርሳቸው በፊት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንና የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ካትሪን አሽቶን በርማን በመጐብኘት ከአዲሱ መንግሥት መሪዎችና ከተጠቀሰው ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን መሪ አውንግ ሳን ሱኪ ጋር መነጋገራቸው ታውቋል።
በርማ እ.አ.አ በ1948 ነፃነቷን ከብሪታኒያ ከአገኘች ወዲህ ዴቪድ ካሜሩን የመጀመሪያው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆኑ ተገልጿል። ዴቪድ ካሜሮን በበርማ ጉብኝታቸው ሂደት በአገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የተዘጋጀ መንግሥት መኖሩን አመልክተው፣ መንግሥቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት የማይቀለበስ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት እንዳስገነዘቡ ተገልጿል።
በበርማ እ.አ.አ 2010 ምርጫ አሸንፎ በ2011 መጋቢት ሥልጣንከያዘው መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች መካከል ብዙዎቹ የቀድሞ ወታደራዊ ባለሥልጣኖች በመሆናቸው ለውጡ የይስሙላ ነው የሚል ግምት ቢኖርም እስከአሁን ያሳያቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ግን ለለውጥ የቆመ መሆኑን አመልካቾች እንደሆኑ ተገልጿል። ለበርካታ ዓመታት በእስር ቤትና በቁም እስር የቆዩትን የዴሞክራሲ ንቅናቄ መሪ አውግ ሳን ሱኪን መፍታቱ በፖለቲካ እንዲሳተፉ ማድረጉ በዚህ ረገድ በገንቢ መልኩ ይጠቀሳል። ለአበረከቱት አስተዋፅኦ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆኑት አውንግ ሳን ሱኪ እንደተጠቀሰው በቅርቡ በአገሪቱ በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ አሸንፈዋል።
እ.አ.አ በ1990 በአገሪቱ ውስጥ በተካሄደው ምርጫ በአውንግ ሳን ሱኪ የሚመራው የፖለቲካ ፓርቲ ሲያሸንፍ የጦር ኃይሉ ውጤቱን በመሰረዝ ራሱ ሥልጣን መያዙ ይታወቃል። የአሸናፊውን የፖለቲካ ፓርቲ መሪም አስሯል። የአገሪቱን ስም «ምያንማር» በሚል ስም ለውጦ ሥልጣን የያዘው ወታደራዊ መንግሥት ምዕራባውያን በፅኑ ከማውገዝ ባሻገር የኢኮኖሚ ዕገዳ ወሳኔም አሳልፈውበታል።
ወታደራዊ መንግሥቱ እንደተጠቀሰው ሥልጣኑን እ.አ.አ በ2010 በተካሄደ ምርጫ ለአሸነፈው የሲቪል መንግሥት አስረክቧል። በዚህም መሠረት በርማ የዴሞክራሲ ጐራውን ተቀላቅላለች ሲል አዘ ዘግቧል።
| < Prev | Next > |
|---|


