ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ስድስት ቤተ እምነቶች የሃይማኖት ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው በጋራ ሃገራዊ ጉዳዮች በተለይም በሃገር ደረጃ ሰላምና መረዳዳት እንዲኖር በጋራ ለመስራት የተቋቋመ ተቋም ነው። ተቋሙ ከተቋቋመበት ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል፤- በሃገራችን ለዘመናት የኖረው የሃይማኖት መከባበርና መቻቻል ተጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግና “አክራሪነት”ን ማለትም በጋራ መተዳደሪያው መሰረት” ከእኔ ሌላ ሃይማኖት የለም” በሚል አስተሳሰብ የሌላውን መብትን መኖር የሚጋፋውን አስተሳሰብ ማውገዝ ነው። ምክንያቱም ሰላም የሁሉም የሃይማኖቶች አስተምህሮ መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ።
የጋራ ጉባዔው በፌዴራል ደረጃ ከተመሰረተ በኋላ በዘጠኙ ብሔራዊ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች መዋቅሩን በማስፋት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ወደ ዞንና ወረዳ የሰፋበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ማዋቅሩን ለማስፋት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
ይሁን እንጂ የሃይማኖት ተቋማቱ የእምነትና የሃይማኖት ልዩነቶቻቸውን ጠብቀውና አስጠብቀው “ሃይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነው” የሚለውን የቆየውን የአበው ብሂል በመገንዘብ ይበልጥ በተግባር ለመግለፅ በጋራ በሚሰሩበት በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በምዕራብ አርሲ ዞን፣ በአሰሳሳ ወረዳ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ግጭት በመፍጠር በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ሰምተን በጥልቅ አዝነናል።
በተለይም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አባል ቤተ እምነቶችን አቅፎ ስለ ሰላም ደፋ ቀና በሚልበት ሁኔታና ሁሉም ሃይማኖቶች ሃይማኖታዊ አስተምህሮቻቸውን መሰረት በማድረግ አክራሪነትን በሚያወግዙበት በአሁኑ ወቅት በሰው ሕይወት ላይ አስከፊ ሕልፈት መፈጠሩና ይህ ዓይነቱ ተግባር በየትኛው የሃይማኖት አስተምህሮ መሰረት የሌለው በመሆኑ ተቋሙ በእጅጉ ያወግዘዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


