የአፍሪካ የክትባት ሳምንት ከሰኞ ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2004 (ዋኢማ) - ሁለተኛው የአፍሪካ የክትባት ሳምንት ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በመላ አገሪቱ እንደሚከበር የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢማኖ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በዓሉ ከአገር አቀፉ አከባበር በተጨማሪ በማዕከል ደረጃ በከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ከሚያዝያ 22 ቀን 2004 ጀምሮ በድምቀት ይከበራል፡፡

ሲሶ የሚሆኑት በሕጻናት ላይ የሚከሰቱ የሕመምና ሞት መንስኤዎች በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች በመሆናቸው የክትባትን ተደራሽነት በመላ አገሪቱ እንዲረጋገጥ የሚያስችል ሥራ ሚኒስቴሩ እያከናወነ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ሞት በመቀነስ በጤና መስክ የምዕተ ዓመቱ ግብ ለማሳካት ከያዘችው የሕጻናት ደህንነት ማስጠበቂያ ስልቶች አንዱ የክትባት መርሃ ግብር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በመሆኑም የክትባት ሳምንቱ መከበር በመደበኛነት እየተሰጡ ያሉትን ክትባቶች ሽፋን በማሳደግና ሌላ አዳዲስ ሕይወት አድን ክትባቶችን ለማስጀመር የሚደረገውን ሰፊ ጥረት በማገዝ የአገሪቱን በሽታዎች የመቆጣጠርና የማጥፋት እንቅስቃሴ ስኬታማ የሚያደርግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የመደበኛ ክትባት መርሃ ግብር ሽፋን ከ10 ዓመት በፊት 52 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ግን 86 በመቶ መድረሱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ሲሳይ ጋሹ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሁለተኛውን የአፍሪካ የክትባት ሳምንት "ልጅዎን ያስከትቡ፤ የፖሊዮና የኩፍኝ ወረርሽኝን ይከላከሉ" በሚል ቃል መሪ ቃል ይከበራል፡፡

በዓሉ በክትባት መከላከል የሚቻሉ የሕጻናት በሽታዎች ስርጭትን ለመቆጣጠር የኅብረተሰቡን ግንዛቤ እንዲጎለበት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርና የፖሊዮን በሽታ ከምደረ-ገጽ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል፡፡

በተለይ የፖሊዮ ቫይረስ በአጎራባች አገሮች ውስጥ የመሰራጨት አዝማሚያ በመኖሩ ድንበር ዘለል የፖሊዮ ቫይረስ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ለመቆጣጠር የሚያስችል ከፍተኛ የክትባት ሽፋን ለተከታታይ ዓመታት እንዲኖር ማድረግና በጠንካራ የበሽታ ቅኝትና ዳሰሳ ሥርዓት ዝርጋታ እየተደገፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኩፍኝ ወረርሽኝ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በተለይም ዝቅተኛ የክትባት ሽፋን ባላቸው የተወሰኑ አካባቢዎች አልፎ አልፎ መከሰቱ በሽታውን መከላከል የሚችል ክትባት ህፃናት እንዲወስዱ ኅብረተሰቡ ማድረግ ይጠበቃል፡፡

በዚህ ረገድ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የሚያደርገውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ የዓለም የጤና ድርጅት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ) ተወካይ ዶክተር ትርሲት አሰፋ በበኩላቸው የሕጻናት ሞትን ለመቀነስ ክትባት አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበው ወላጆች፣ አሳዳጊዎችና ኅብረተሰቡ በአጠቃላይ ክትባቱን እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሕጻናትን ሞትን ለመቀነስ የተለያዩ ጠቃሚ ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ መሆን መቻሏን ገልጸው፣ ወደፊትም ለምታደርገው ጥረት የድርጅቱ ድጋፍ እንደማይለያት ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ መንግሥት በጤናው ዘርፍ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት 38 ሺህ ያህል የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን የገጠር ቀበሌዎችን ጨምሮ በመላ አገሪቱ መሰማራቱ ይታወቃል፡፡




  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 166 guests