በኮንሶ የሚካሄደው ብሔራዊ በዓል የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስተዋወቅ ፋይዳው የጎላ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2004 (ዋኢማ) - ኢትዮጵያ ያሏትን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች ከማሳወቅ አንፃር የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድር ብሔራዊ በዓል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የኢትዮጵያ ቅርሰ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የኮንሶ መልክዓ ምድር የሀገሪቱ ዘጠነኛ ቅርሰ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበበት አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ''ቅርስ የህዳሴያችን ማሳያና የዘላቂ ልማታችን መሠረት ነው'' በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ጀምሮ ኮንሶ ካራት ከተማ መከበር ተጀመሯል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ በለሥልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ቀለሟ መኮንን በዓሉን አስመልክተው እንደገለጡት ኢትዮጵያ በዩኒስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘጠኝ ቅርሶች ባለቤት በመሆን በአፍሪካ ብዙ ቅርስ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆናለች፡፡
እነዚህ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ለሀገርና ለውጭ ጎብኝዎች በማስተዋወቅና ቅርሶቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች መሰረተ ልማት በማሟላት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡
የኮንሶ ባህላዊ መልክዓምድር በዩኒስኮ እውቅና ማግኘቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ ሀገራት ቀዳሚ ከማድረጉም በላይ በደቡብ ክልል ከጥያ ትክል ድንጋይና ከኦሞ ሸለቆ ቀጥሎ ሦስተኛ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ክልሉንም በብዛት ቀዳሚ አድርጐታል ብለዋል፡፡
ለኮንሶ ባህላዊ መልክዓምድር ብሔራዊ እውቅና ለመስጠትና የዩኔስኮ አርማ ለማቆም በሚከበረው ክብረ በአል ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲፕሎማቶች እና አምባሳደሮች ታዋቂ ግለሰቦች የውጭና የአገር ውስጥ ሚዲያ ባለሙያዎች እንደሚገኙ ወይዘሮ ቀለሟ ገልጠዋል፡፡
እንደ ኢዜአ ዘገባ ዩኔስኮ የኮንሶን ባህላዊ የመልክዓ ምድር ሁኔታን ታሪካዊ ቅርስ ሆኖ በዓለም መዝገብ ላይ እንዲመዘገብ ያደረገው እ.አ.አ ሐምሌ 2011መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


