አርብቶ አደሩን የዘላቂ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 19/2004 (ዋኢማ) - በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን የዘላቂ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን የክልሉ አርብቶ አደሮች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ አርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ኛካል ለዋልታ እንደገለፁት ቢሮው አርብቶ አደሩም ሆነ ከፊል አርብቶ አደሩ ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የሚያጠፋውን ጊዜና ጉልበት በማስቀረት በአንድ ቦታ ተረጋግቶ እንዲኖር የማድረግ ሥራ እየሰራ ነው።
እንደ አቶ ፍቅሩ ማብራሪያ አርብቶ አደሩ ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ሲንቀሳቀስ በውስጥም ሆነ ከውጭ ለተለያዩ ግጭቶች የመጋለጡ እድል የሰፋ ነበር።ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግስታት ድርጅት/ኢጋድ/ እና ከአዋሳኝ አገሮች ጋር በመተባበር አርብቶ አደሩን ያሳተፈ ጥናት ተከናውኗል።
በጥናቱም አርብቶ አደሩ በአንድ አካባቢ ተወስኖ የተረጋጋ ሕይወት በመምራት የዘላቂ ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን ሙሉ ፍላጎቱን አሳይቷል ብለዋል።
የኢፌዲሪ መንግስትም ሆነ የክልሉ መንግስት የአርብቶ አደሩን ፍላጎትና አገሪቱ የነደፈቻቸውን የልማት ዕቅዶች መነሻ በማድረግ አርብቶ አደሩንና ከፍል አርብቶ አደሩን በልማት ለማሳተፍ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ አቶ ፍቅሩ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለይም በደቡብ ኦሞ ዞን የኩራዝ ስኳር ኮርፖሬሽን ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ አርብቶ አደሩን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የኩራዝ ስኳር ኮርፖሬሽን መቋቋሙን ተከትሎ አርብቶ አደሩ በመስኖ በመታገዝ በሰብልና ቋሚ ተክሎች ልማት ላይ በመሳተፍ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ የድጋፍና ክትትል ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። እንደ አቶ ፍቅሩ ገለፃ አርብቶ አደሩ ቶሎ ወደ ልማቱ እንዲገባም የመስኖ ውሃና የእርሻ መሬት የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻችቷል።
በአካባቢው እየተስፋፋ ያለውን የመሠረተ ልማትና የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ከተጠቀመ አርብቶ አደሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምግብ ዋስትናውን በማረጋገጥ ወደ ባለሀብትነት እንደሚሸጋገርም አቶ ፍቅሩ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት የክልሉ መንግስት አርብቶ አደሩን በመንደር በማሰባሰብ በመስኖ ውሃ በመታገዝ የሸንኮራ አገዳ አልምቶ ለፋብሪካው በማቅረብ ገቢ እንዲያገኝ ለማስቻል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኦሞ ወንዝን ተከትለው ለሚቋቋሙ ስድስት የስኳር ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚያገለግል የሸንኮራ አገዳ ተከላ ከተያዘው ዓመት መጀመሪያ አንስቶ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትን ጠቅሰን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።
የፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው በስኳር ፋብሪካዎቹ የግንባታ ሂደት የአካባቢው አርብቶ አደሮች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ይሆናሉ። ፋብሪካዎቹ የምርት አገልግሎት ሲጀምሩ ደግሞ የሸንኮራ አገዳ ቅጠሎችን እና የሞላሰስ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ሥራዎችን ማከናወን ይችላሉ።
| < Prev | Next > |
|---|


