ፍትህና አምደኞቹን በጨረፍታ ስድስት

  • PDF

ዮናስ

አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እና የዜሮ ድምር ፖለቲካ ግንባር

ከፌዴራላዊ ስርዓት ስነ ሳይንስና ከሰፈራ ፕሮግራም መሰረታዊ መርሆዎች፣ ከፌዴራሉ ህገመንግስትና ከደቡብ ክልል ህገመንግስት፣ ከዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መስመር አንፃርና ከፀረ ዴሞክራቲክ ሁሉን የማግኘት ወይ ሁሉን የማጣት አስተሳሰብ አንፃር በዋናነት መቃኘት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የትኩረት አቅጣጫ ሲሆን ግቡ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍሬውን ከገለባው የሚለዩበትን አቅጣጫ ማሳየት ነው።

ይህ ጽሁፍ የፍትህና ዓምደኞቹን በጨረፍታ ስድስተኛ ክፍል ነው። ፍትህ በሚያዚያ 5/2004 ዕትሟ ያስነበበችን ዜናዎችን ጨምሮ ባጠቃላይ ይዘቷ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ጥሩ መገለጫ መሆኗ የታየበት አንደሆነም በአምስተኛው ክፍል አብራርቼ ነበር። ከጉራፈርዳ ወረዳ ጋር ተያይዞ ስለኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የተነሱትን ነጥቦች ደግሞ በዚህኛው ክፍል ላወሳ በይደር ባቆየሁት መሰረት በዚሁ እትም |የእናቴን ዘመዶች ተዉአቸው´ ሲል ካስነበበን አናንያ ሶሪ የተባለው የፍትህ አምደኛ እጀምራለሁ።

|- - - ታዲያ ከዚህ በኋላ እኔ ማነኝ? ሰው፣ ኢትዮጵያዊ ከመሆን በቀር አዎ አዎ- ከሰውነቴ ባሻገር ኢትዮጵያዊ ቀጥሎ የአማራ እና ኦሮሞ ወይም የኦሮሞና የአማራ ውህድ የሆንኩ አዲስ ፍጥረት ነኝ።- - - ´ የሚለው አናንያ በኢትዮጵያ ደቡብ ክልል ቤንች ማጂ በሚባለው ዞን ውስጥ በጉራፈርዳ ወረዳ በእርሻ ሙያ ሲኖሩ የነበሩ ሰው ኢትዮጰያውያን አማሮች በግዳጅ እየተፈናቀሉ ሃብት ንብረት ካፈሩበት አገራቸው ተሰደዋል። ለዚህ ደግሞ የተሰጠ ግልጽ ምክንያት የለም ይላል። አናንያ ይህን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን የተመለከቱ ነጥቦች በማንሳት ከእናቱ ዘመዶች አንፃር ብቻ በማየት ውርጅብኙን አውርዷል።

እኔ ላነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ከላይ በአናንያ ሶሪ የተጠቀሰ ነው ስል ያሰፈርኩት ነጥብ ይበቃኛል።ወደሌላው አምደኛ ከመሸጋገሬ በፊት ግን አናንያንና ሃተታውን በተመለከተ አንባብያን ታጤኑት ዘንድ አንድ ነገር ከጽሁፉ መምዘዝ እፈልጋለሁ። አናንያ በርዕሱ የእናቴን ዘመዶች ተዉአቸው ሲል ነገር ያሳመረ መስሎት ብሄሩን አስቀድሟል። እኔ ማነኝ ሲል ጠይቆ ደግሞ ለመመለስ ትምክህቱ አመለጠው መሰል ሰው ፣ኢትዮጵያዊ አማራ ---  ሲል ኢትዮጵያዊነቱን አስቀድሟል። ብቻ ሁለት እግር አለኝ ብሎ በአንዴ ሁለት ዛፍ ላይ ለመውጣት ያደረገው ሙከራ ይጤንልኝና ዝርዝሩን ወደኋላ እመለስበታለሁ።

ከሰሞኑ ጉራፈርዳ ወረዳ ላይ ስለተፈጠረው አለመግባባት መነሻ ምክንያትና ሌሎችም መሰረታዊ ጉዳዮች በደንብ ባልተፈተሹበትና ግልጽና ወጥ የሆነ መረጃ ተደራሽ ባልሆነበት በዚህ ወቅት ቤንች ማጂ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እጣ ፈንታ አመላካች! ሲል ፖለቲካ እና ስልጣን በሚለው አምድ ስር ያስነበበን ሙሉነህ አያሌው የተባለው ሌላው ፎጣ ጠምጣሚ ነፃ አውጪ አምደኛ ነው።

ነፃ አውጪው ገና ሲጀምር በርካታ የብሄር ፖለቲካ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን የተስማማበት ነው ሲል ያሰፈረውን መመልከት የአምደኛ ነኝ ባዩን ማንነት መረዳት ያስችላል“------ በአብዛኛው አሁን እየተከናወነ ባለው የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓት ላይ ተቀራራቢ አቋም አላቸው። የመጀመሪያው የፌዴራል ስርዓቱን የትም ያልተሞከረ እና ተሞክሮም ለሃያ አመታት ያህል በተግባር ተጨባጭ ለውጥ ያላመጣ ነው ይሉታል። የፌዴራሉ ክልሎችም ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ይችላሉ ተብሎ የነበረውም መከራከሪያ ውሃ የሚቋጥር አልሆነም በማለት ሃሳቡም የራሱ እንዳልሆነና የበርካታ ምሁራን የምርምር ውጤት መሆኑን ለማሳየት በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ አስቀምጧል።

ይቀጥላል ሙሉነህ አሁን ደግሞ ያቀረበው አስረጂ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የተባለን ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። “- - - ጥናቱ በተለያዩ ጊዜያት ተከስተው የነበሩ ድንበር ዘለል እና በክልል ማዕቀፍ ውስጥ የተነሱ ግጭቶችን በዋቢነት ጠቅሶ አቅርቧል። ይህ ሪፖርት ለኢህአዴግ መንግስት የማንቂያ ደወል ከመሆን ይልቅ እንደተለመደው  |ጉንጭ አልፋ ክርክር´  አልያም   |የወጣበትን ወረቀትና የቀለም ዋጋ እንኳ መሸፈን የማይችል፣ የተላላኪዎች ዘገባ አልያም በአቶ መለስ አነጋገር |የአይጥ ምስክር ድንቢጥ´ ከመባል አልተረፈም ይላል።

በዚህ ያላበቃው ሙሉነህ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦችን ህገመንግስት አንቀጽ 34 በመጥቀስ በጉራፈርዳ የተወሰደውን እርምጃ ትክክል አይደለም ሲል በመኮነን ከብሄራችን ማንነት በበለጠ ኢትዮጵያዊ አንድነት ሊያስተሳስረን ይገባል በማለት ጽሁፉን ደምድሟል። በአጠቃላይ ጉራፈርዳን ተንተርሰን ኢትዮጵያዊነትን ካቀነቀንን ቀጣዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕጣ ፈንታ የፈለግነውን አይነት ይሆናል የሚል እንደምታን ያዘለ ሃተታውን ነው ያስነበበን።

ሌላው ዳንኤል ተፈራ በተባለ ፎጣ አልባ አምደኛ የተፃፈው “ትንሳኤ የሚያስፈልገው የኢህአዴግን ፍርሃትና የእኛ ስጋት” እንዲሁም “የወጣቱ የፖለቲካ ፍዘት” በሚል ስም አልባና ፎጣ አልባ “አምደኛ”የተፃፉት ጽሁፎች በይዘት ደረጃ ያልተለያዩና ያው የተለመደው የዜሮ ድምር ፖለቲካ ዝማሬዎች ናቸው። ዓመጽ ናፋቂ እይታዎች ስለመሆናቸውም አንባቢያን አይተው ቢፈርዱ እላለሁ።

እዚህች ጋር ግን በዳንኤል ተፈራ ከቀረበው ፅሁፍ አሁንም አንባብያን ማጤን ያለባችሁ ነገር ያለ ይመስለኛል። እነፍትህና አምደኞቹ የመፃፍ ነፃነት ለነሱ ብቻ የተሰጠ ይመስል ይፅፉና የተለየ አተያይ ያለን ሰዎች ደግሞ ስንጽፍ ከኢህአዴግ ፍቅር በወደቁ ሚዲያዎች መንግስት  እያስፈራራን ነው ይላሉ። ለነገሩ እኔ እንኳን ከዚህ በፊት በራሴ ስም ለፍትህ የላኳቸው ጽሁፎች ለንባብ እንዳልበቁ /የነሱን "መመዘኛ" ሳያሟሉ ቀርተው ነው መሰለኝ/ እኔና እነተመስገን ብቻ ስለሆንን የምናውቀው የነ ፍትህ ወሬ ለጥቂት አንባብያን በተወሰነ ደረጃ እውነት ይሆን? የሚል ጥርጣሬ  ሊያጭር ይችል ይሆናል። ይህም ይሁን ከተባለ እኔና እኔን መሰሎች በነፃ የምንሰጠው አስተያየት በፈለገው ሚዲያ በኩል ይተላለፍ፣ የናንተ አይደለም ለማለት የሚያስችላቸው ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ የሆነስ ሆነና የገዢው ፓርቲ ካድሬዎችን ጨምሮ ማንኛውም ዜጋ የመፃፍና የግል ሃሳቡን የማንጸባረቅ ነፃነት አልተሰጠውም ማለት ነው? ህገ መንግስቱ ለሁሉም  ነው ወይስ ለተቃዋሚና ለነፃው ፕሬስ ብቻ ይሆን የቆመው? ወይስ ከአባላቱ ውጭም ቢሆን ገዢው ፓርቲ የሚፅፍ ደጋፊ የለውም ማለት ይሆን? ሜዳው የሁላችን መሆኑን ልትረዱት መጀመሪያ ይገባል። ደግሞ የሚምታታባችሁ ነገርም አለ። ሌሎቻችሁ በመፃፋችን መአት ስም ስትሰጡን ዳንኤል ተፈራ ደግሞ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የክርክር ግብግብ የምትባል ነገር  አይመቻቸውም ሲል ይደመጣል። ይህን የተምታታና “ለእኛ ብቻ የተሰጠ” የሚል አምባገነን አካሄዳቸውን ነው አንባቢያን ታጤኑልኝ ዘንድ የምሻው።

ያም ሆነ ይህ ካድሬም አላችሁን ሎሌ እንደናንተ የሻቢያ እና የግንቦት 7 ሎሌ ከመሆን ስለሚሻል የመፃፍ ነፃነታችንን ተጠቅመን እንፅፋለን። የብዕር ግብ ግቡንም በደስታ እንገጥማለን። አሸናፊው ምን ጊዜም እውነትና ሃቅ መሆኑን በማመን። ከላይ በፍትህና ዓምደኞቹ የተነሱትን ጉዳዮች ከማየቴ በፊት አሁንም የፍትህና ዓምደኞቹን ማንነት አንባብያን ይረዱ ዘንድ የፍትህ ሌላው ቃል አቀባይ ከሆነው ፍኖተ ነፃነት ላይ ጉራፈርዳን በተመለከተ ለንባብ የበቃ አንድ ምሳሌ እጨምራለሁ። የፍኖተ ነፃነትን ባለቤቶችና ዓምደኞችም ቀጥዬ እነካካለሁ። ከዛም እውነታውን ከሃሰቱ የመለየቱን ጉዳይ ለአንባብያን ትቼ የመከራከሪያ ሃሳቤን በማቅረብ እደመድማለሁ።

ጉዳዩ በጥቅሉ እንዲህ ነው፦ በቤንች ማጂ ዞን ሜኢኒት የተባለ ብሔረሰብ ነበር። ይህ ብሔረሰብ እራሱን በራሱ ማስተዳደር ፈለገና የወረዳ ይገባኛል ጥያቄ አቀረበ። ነገር ግን ወረዳ መመስረት የሚያስችል የህዝብ ብዛት ስላልነበረው በሚመለከተው አካል ተከለከለ። የወረዳ ይገባናል ጥያቄያቸው እንቅልፍ የነሳቸው ሜኢኒቶች ቁጥራቸውን ለሟሟላት ሲሉ ማስታወቂያ ለጠፉ። በእኛ ወረዳ መስራትና መኖር የሚፈልግ ሁሉ ይምጣ መሬት ይሰጠዋል። የሚል ማስታወቂያ። ማስታወቂያውን የተመለከቱት የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ደግሞ ወደስፍራው አመሩና የወረዳው አካል ሆኑ ጉራ ፈርዳ ወረዳም ተፈጠረች። ይላል አጠቃላይ በፍኖተነፃነት የቀረበው ጽሁፍ ።

ትችቴንም ከዚሁ ብጀምር ጥሩ ነው። ሲጀመር ፀሐፊው ምንጭ አለመጥቀሱ ስህተት ነው። ሁለተኛው አመክንዮ ደግሞ ሜኢኒቶች ብሄረሰብ ነበሩ ቁጥር ለማሟላት ሲሉ በእኛ ወረዳ ማንኛውም ሰው መጥቶ መስራት ይችላል ሲሉ ማስታወቂያ አስነገሩ የሚለው ነው። ሜኢኒቶች የወረዳ ጥያቄ ሲያቀርቡ ወረዳ እንዳልነበሩ አስተዳደራቸውም በነበሩበት ሸኮ ወረዳ እንደሆነ ፀሃፊው ጠቁማል። በሸኮ ወረዳ ሥር እንደሆኑ የሚጠቅሰው ፀሃፊ መልሶ ሜኢኒቶች ወደእኛ ወረዳ ኑ ሲሉ ማስታወቂያ አስነገሩ ይለናል። በየትኛው መዋቅርና በየትኛው ወረዳ ማህተም ማስታወቂያ አስነገሩ? ሜኢኒቶች ገና የወረዳ ጥያቄአቸው ሳይመለስ የሸኮ ወረዳን አስተዳደር ጥሰው መሬት የመሸንሸን መብት እንዴት ሊኖራቸው ቻለ? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች በፀሐፊው የታሰበባቸው አይመስሉም። እነዚህን ጥያቄዎች  በማንሳት ብቻ እነፍኖተ ነፃነት ፍትህና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ያለምንም መረጃ የተጣረሰና የዜሮ ድምር ፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ከየትም የቀራረሙትን ዝርክርክ ሃሳቦች እያስነበቡን እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

እነዚህ ናቸው እንግዲህ ስለመፃፍ ነፃነት ሁሌም ቢሆን ተናግረው የማይጠግቡት።ይህን ሃሳብ ፍኖተነፃነት ባስነበበን ሳምንት ፍትህና ዓምደኞቹን የተመለከተ ጽሁፍ ሳቀርብ  የመፃፍ ነፃነቴን   ተጋፉ። ፍኖተ ነፃነትም የመፃፍ ነፃነቴን በሚጋፋ መልኩ "በፍትህ ላይ የተከፈተ ዘመቻ" ነው በሚል ሊቆም ይገባዋል ብሎ በርእሰ አንቀጹ ጭምር አስተጋባ። ከአንድ እናት የመነጩት እነዚህ ፕሬሶች ነፃነቴን ሲጋፉ በግሌ የተረዳሁት ቁም ነገር የለየላቸው አምባገነኖች እንደሆኑና ለዚህች ሃገር የደገሱትን ጥፋት የሚያረጋግጥ፣ ማንነታቸውን የሚያጋልጥ  እንደሆነ ነው። ዳሩ የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ይባል የለ።

በሌላም በኩል አናንያ ሶሪ "የእናቴን ዘመዶች ተዋቸው" ሲል አንዴ ብሄሩ ሌ ጊዜ  ደግሞ ኢትዮጵያዊነቱ እየተደበላለቁበት አስቸግረውታል። የዚህች አስተሳሰብ መነሻና ምንጭ ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። ዴሞክራሲና ልማታዊነት በቅርብ የተሳሰሩ እንደመሆናቸው መጠን የብሄሮች መብትና ልማታዊነትም በቅርብ የተሳሰሩ ጉዳዮች ናቸው። ኪራይ ሰብሳቢነት በሰፈነበት ሁኔታ ዴሞክራሲ ሊኖር እንደማይችል ሁሉ የብሄሮች ጥያቄም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊፈታ የሚችለው ኪራይ ሰብሳቢነት ሲወገድ ብቻ ነው። ኪራይ ሰብሳቢዎች እንደ ፍትህና አምደኞቹ ያሉትን ጨምሮ የብሄር ጥያቄን አንድን ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጭ ጥያቄ አድረገው ያቀርቡታል። ጨቋኞችን ከጭቁኖች ጋር ሳይሆን የአንድ ብሄር ጨቋኞችና ጭቁኖች ባንድ ወገን የሌላው ብሄር ደግሞ በሌላ ወገን የሚሰለፉበት እንደሆነ አድረገውም ያቀርቡታል። ይህ አቀራረብ ደግሞ ለኪራይ ሰብሳቢነት መረብ ያመቻል። ለምሳሌም በአዲስ አበባና በሌሎችም ቦታዎች ላይ መኢአድን ጨምሮ ሌሎች ኪራይ ሰብሳቢዎች ጉራፈርዳን አስታከው የየራሳቸውን ጥያቄና የጥፋት አጀንዳ ወይም ድብቅ ዓላማ ለማራመድና ለማንጸባረቅ ይረዳናል ባሉት መልክ በአማራ ብሄር ስም ለመነገድ ሞክረዋል፡፡

ይሁንና የኪራይ ሰብሳቢው ጥቅም በብሄር መብትና ጥቅም ሽፋን ከተነሳ የህዝብ ድጋፍ ለማግኘትና ተግባራዊ ለማድረግ የተሻለ እድል ስለሚኖር እነፍትህና አምደኞቹ ጉራፈርዳን ለጉድ አራግበውታል። አናንያም የዚሁ አካል ነው። በተመሳሳይ መልኩ የመንገግትን ስልጣን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የፈለጉት በዋናነት ጥገኛው መኢአድ፤  አንድነት እና መድረክ ጉራፈርዳን መፈክራቸው አድርገው ከርመዋል። አናንያን ጨምሮ ሌሎቹም የፍትህ አምደኞች እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ በጉራፈርዳ ወረዳ ተከስቶ ስለነበረው ሁኔታ በመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ እንደሌለ አድረገውም ያቀርባሉ። ምላሹ ግን ተሰጥቷል። የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከሰጡት ምላሽ እንነሳ፦

በቤንች ማጂ ዞን በሚገኙ አስር ወረዳዎች ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ የኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች አሁንም ሰላማዊ ኑሮአቸውን እየመሩ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፦ በዞኑ በ2000 ዓ.ም በተካሄደ ጥናት በጉራፈርዳ ወረዳ 22 ሺህ 46፣ በሜኒ ሻሻ 1ሺህ 484፤ በሜኒት ጎልዲያ ደግሞ 1ሺህ 520 የአማራ ክልል ተወላጆች እንዳሉ ተረጋግጧል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የክልሉ መንግስት በ2001 ዓ.ም አንድ ሰፋሪ ሁለት ሄክታር የእርሻ መሬትና 1ሺህ ካሬ ሜትር የቤት መስሪያ ቦታ አንዲያገኝ መመሪያ ቢያወጣም፤በወቅቱ በተካሄደው የመሬት ልኬት በጉራፈርዳ ወረዳ ከ2-12 ሄክታር፣ በሜኒት ጎልዲያ ከ3-60 ሄክታር መሬት ይዞታ የነበራቸው ሰዎች እንደተገኙም ተገልጿል፡፡

በጉራፈርዳ፣ በሜኒ ሻሻና በሜኒት ጎልዲያ ወረዳዎች የሚገኙ ሰፋሪዎችም በዚሁ ከላይ በተጠቀሰው መመሪያ መሠረት መስተናገዳቸውም በርዕሠ መስተዳድሩ ምላሽ ተካቷል፡፡ ነገር ግን መመሪያው ሊገዛቸው ያልፈቀዱ በርካታዎች በመፈጠራቸው የክልሉ መንግስት በ2001 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ ከነሀሴ 30 ቀን 1999 ድረስ ወደ ዞኑ የገቡ ሰዎች ባሉበት ኑሯቸውን እንዲመሩ ሲደረግ ከነሀሴ 1999 በኋላ ወደ ዞኑ የገቡት ደግሞ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ መደረጉም  ተመልክቷል፡፡

በዚሁ መሰረት በጉራፈርዳ ከሚኖሩት 22 ሺህ 46 የአማራ ክልል ተወላጆች መካከል መመሪያው ከወጣ በኋላ የገቡ 800 ሰዎች በወቅቱ ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ የክልሉ መንግስት እነዚህን ሰዎች በራሱ ትራንስፖርት ባህር ዳር ከተማ ድረስ ወስዶ ለአማራ ክልል መንግስት ማስረከቡንም አቶ ሽፈራው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ የአማራ ክልል መንግስትም እነዚህን ሰዎች በምዕራብ አማራ እንዳሰፈራቸውና አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገላቸው ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ በቂ መረጃ ያላቸው ስለመሆኑም ነግረውናል፡፡ ሌላው ከርዕሰ መስተዳድሩ እኔም ሆንኩ እናንተ ያዳመጥነውና የተመለከትነው በወቅቱ እነዚህን ሰዎች ወደቀዬአቸው ለመመለስ ጥረት ሲደረግ የሁለቱ ክልል መንግስታት መወያየታቸውንና የፌዴራል መንግስትም ጉዳዩ መስመር እንዲይዝ ተሳትፎ ማድረጉን ነው፡፡

መኢአድ ፍትህና ዓምደኞቹ ከነፍኖተ ነፃነትና መድረክ ጋር የግንባር ስጋ ሆነው ሳለ የጥገኞች ግንባር በመፍጠር የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጉዳዩን በማራገብና አሉባልታ በማናፈስ የከረሙ ሲሆን፤ከፍ ሲል ደግሞ መኢአድ የምርጫ ካርድ ከወዲሁ ለመሸመት ያስችለኝ ይሆናል በሚል እሳቤና በይበልጥም ፖለቲካዊ ትርፍ ያስገኝልኛል በሚል ይመስላል ጥቂት ተፈናቃዮችን በጽ/ቤቱ በማስጠለል እንዳቆዬ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ተደምጧል፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እጣ ፈንታ ከቤንች ማጂ ጋር በቀጥታ ያያያዘው ዓምደኛ የኪራይ ሰብሰቢነት ፍላጎቱ ከመናሩ የተነሳ እንጂ ከነመኢአድ የተለየ አስተሳሰብ ኖሮት አይደለም፡፡ እራሱ እንደገለፀውም የአይጧ ምስክር  ነው፡፡ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ማን ሆነና ነው ለፍትህ ዓምደኛ በምንጭነት የሚያገለግለው? የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ በመሆኗም አይደል፡፡ እንደአስፈላጊነቱ የሚጠቀሙበትን ህገ መንግስትም እያነሱ የጥገኛ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሞክረዋል፡፡ ዳሩ ህገመንግስቱን ለምናከብረው ፍቺው በደንብ የሚገባን ስለሆነ የናንተ የተቆነፀለ አስረጅና ሌላም ሌላም ነገራችሁ አይረባንም፤ አይገባንምም፡፡

ሌላው ምላሽ ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ነው፡፡ ሰፈራ በተደራጀ መልክ እንጂ በተናጠል አይከናወንም፡፡ በጉራፈርዳም የተከናወነው ይኸው እንጂ በኢትዮጵያዊነትና እነመኢአድ በሚያናፍሱት አይነት አሉባልታ አይደለም፡፡ ሌላው በነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች ከጉራፈርዳ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ  ፌደራላዊ ሥርዓቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራሊዝም በየትም ሀገር ተሞክሮ ያልተሳካ እንደሆነ በመግለጽ፡፡ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች ህንድንና ናይጄሪያን በዚህ አጋጣሚ እንድትመለከቱ ጋብዣችሁ አልፋለሁ፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓታችን እናንተ እንደምታወሱት ለብተና የሚዳርግና ውጤት አልባ ሳይሆን በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተና አንድነትን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ መፈቃቀድና በህግ የበላይነት የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኀበረሰብ ለመመስረት ቃል የገቡት የቃል ኪዳን ማሰሪያና የጋራ መተዳደሪያቸው የሆነውን የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በማጽደቅ ነው፡፡ ስለሆነም ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማክበር ልዩነቶች በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሥርዓት በህገ መንግስቱ በበቂ ሁኔታ ዘርግተዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማናቸውም አፍራሽ እንቅስቃሴ በሀገር ህልውና ላይ እንደተቃጣ ጥቃት መታየትና የዚህ ዓይነት አፍራሽ ድርጊት በህግ አግባብ የመቆጣጠር የመከላከል ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት የሁሉም አካላት መሆኑን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ፍትህና ዓምደኞቹ እንደሚሉት የሚበታትን አይደለም፡፡ የመተባበር ፌዴራሊዝም (Co- operative federalism) መሆኑን የሚያንፀባርቁ አያሌ ድንጋጌዎችን በኢፌዴሪ ህገ መንግስት እናገኛለን፡፡ እንዲሁም ሌሎች የመተጋገዝ ሁኔታዎችን በማየት መረዳት እንችላለን፡፡ በህገ መንግስቱ መግቢያ የተዘረዘሩት ከላይ የተጠቀሱት ቁምነገሮች የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ህብረ ብሄራዊ ብቻ ሳይሆን የመተባበር ፌዴራሊዝም መሆኑን በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህ የፌዴራሊዝም መርህ በፌዴራልና በክልሎች መካከል መኖር የሚገባውን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በክልሎች መካከልም መኖር የሚገባው ግንኙነት የመተባበርና የመደጋገፍ  መሆን እንዳለበት የሚያሳይ ነው፡፡ ስለሆነም ህልማችሁና ምኞታችሁ ሁሌም ቢሆን ከንቱ እንደሆነ ልትገነዘቡት ይገባል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስፈጻሚውን በመቆጣጠር ረገድ የጀመረውን ጠንካራ እርምጃ እንዴት ያዩታል?




Results

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የአባይን ወንዝ አቅጣጫ የማስቀልበስ ተግባር በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ይከናወናል ብለው ገምተው ነበር




Results