በእንግሊዝ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ስራ እየፈጠሩ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18 2004 /ዋኢማ/ - ታዳሽ የኃይል ምንጮች በዓላማችን የኃይል አቅርቦት ውስጥ የ16 በመቶ ድርሻ አላቸው። በታዳሽ የኃይል ምንጭ ሥር የሚካተቱት እንደ ንፋስ፣የፀሐይ ብርሃን፣የውሃኃይል፣ ከዕፅዋትና ከእንፋሎትና ከሌሎች የሚገኙ የኃይል አቅርቦቶች ናቸው።
እነዚህ የኃይል ምንጮች አሁን አሁን በዓለማችን እጅግ በማደግ ላይ የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ የወጡ ዘገባዎች ደግሞ በተለይ በእንግሊዝ ታዳሽ የኃይል ምንጮች የሥራ ምንጭና የዕድገት መሠረት እየሆኑ መምጣታቸውን ይፋ አድርገዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ በእንግሊዝ የታዳሸ ኃይል ኢንዱስትሪው 110 ሺ ያህል የሥራ ዕደሎችን ፈጥሯል። እ.ኤ.አ በ2020 ደግሞ 400 ሺ ያህል የስራ ዕድሎችን ሊፈጥር እንደሚችል አንድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
የእንግሊዝ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ማህበርና የማህበሩ አማካሪዎች እንዳስታወቁት ኢንዱስትሪው በየአመቱ በእንግሊዝ ኢኮኖሚ ላይ የ 12.5 ቢሊዮን ፓወንድ እሴት ይጨምራል፡፡
ባለፈው ሳምንት ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እንደገለጸው በ2020 አነስተኛ የካርቦን ልቀት ያላቸው አስተማማኝ የኃይል ምንጮች በአውሮፓ ብቻ አምስት ሚሊዮን ያህል የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡
በሪፖርቱ የተቀመጡት የህዝብ አስተያየት ውጤቶች እንደሚያመለክቱት ታዳሽ የኋይል ምንጮቹ የህዝብ ድጋፍ እንዳላቸው ነው ፡፡
በምሳሌነት የታዳሽ የኃይል ምንጭ ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋይነር ሀርትኔል እንደተናገሩት “ታዳሽ የኃይል ምንጮችን መጠቀም የሥራ እድል ከመፍጠሩም በላይ ከውጪ ለምናስገባው የኃይል ፍጆታዎች ገንዘብ ከማውጣት ይልቅ ገንዘቡ በእንግሊዝ ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲንሸራሸር ማድረግ የተሻለ ነው” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም “በዘርፉ የሥራ ዕድል ፡ የኢኮኖሚና የኃይል አማራጭነቱን በተመለከተ የሚገጥሙትን እንቅፋቶች ለማስወገድ የኃይል አማራጮችን ታዳሽና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቃል” በማለት ተናግረዋል ፡፡
በእንግሊዝ እ.ኤ.አ ከ2009/10 እስከ 2010/11 ድረስ የታዳሽ የኃይል ምንጭ ዘርፉ በ11 በመቶ ያደገ ሲሆን ከአገሪቱ 1.4 በመቶ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ሪፖርቱ ከዚህም በተጨማሪ እንዳስቀመጠው እንግሊዝ ከታዳሽ የኃይል ምንጭ የወጪ ንግድ 1.6 ቢሊዮን ፓውንድ ያህል ገቢ አንዳገኘችና ከዚህም ውስጥ የነፋስ ቴክኖሎጂው ከፍተኛውን ድርሻ እንደወሰደ ያሳያል ፡፡
እንግሊዝ በ2020 ከአጠቃላይ የኃይል ፍጆታዋ 15 በመቶ ከተለያዩ የታዳሽ የኃይል ምንጮች ለማግኘት እንደግብ ያስቀመጠች ቢሆንም ግቡ ቀላል ፈተና እንዳማይገጥመው ተገምቷል፡፡
ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ የታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚጠቀሙት ቴክኖሎጂዎች የሚያስወጡት ተጨማሪ ወጪ ሲሆን ይህም መንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር የነዳጅ ዘይትን በኃይል አማራጭነት የመጠቀም ፍላጎቱን እንዲያራምድ ሊያስገድደው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ እንግሊዝ በረጅም ጊዜ ለማሳካት ያስቀመጠችውን አለም አቀፍ የጋዝ ልቀት ቅነሳ ህግ ይፃረራል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የአየር ፀባይ ለውጥ ሚኒስትሩ ግሬግ ባርከር እንግሊዝ የጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ያወጣችው ህግ እንዲከበር በሙሉ ኃይላችን እንቀሳቀሳለን ብለዋል።
“ታዳሽ የኃይል ምንጭ የሚያበረክተው ንጹህና አስተማማኝ ኃይልን ብቻ ሳይሆን ሃገሪቱ ከውጪ በሚገቡ የኃይል ምንጮች ላይ ያላትን ጥገኝነት በማስወገድና በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢንቨስትመንቶችንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ እድሎችን በመፍጠር ረገድ በእንግሊዝ ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ እድገት የሚያሳይ ዘርፍ ይሆናል”ብለዋል፡፡
የታዳሽ የኃይል ምንጭ ማህበሩ ባወጣው ሪፖርት ላይ በዘርፉ ስላሉት እድሎችና ተግዳሮቶች ያስቀመጠ ሲሆን የተሻለውን አመራጭ በመውሰድ ለእንገሊዝ የበለጠ ጥቅም በሚያሰገኝ መልኩ እንደሚሰሩ ገልጸዋል ፡፡
አንዳንድ ተንታኞች ባሰቀመጡት ስሌት እንግሊዘ የ2020 ግቧን አሳካቸ ማለት ሃገሪቷ ከውጭ ለምታስገባው የኃይል ምንጭ የምታወጣውን ገንዘብ ከ60 ቢሊዮን ፓውንድ በታች ያደርገዋል ፡፡
ሆኖም በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ ዘመቻ የሚያደርጉ ወገኖች የሚጠይቁት በዘርፉ የሚገኘው ጥቅም በሙሉ ለእንግሊዝ መዋሉን በመጠራጠር ነው፡፡
አዲስ የተቋቋመው የነፋስ ኃይልን የሚቃወም ብሄራዊ ድርጅት እንዳስታወቀው በሃገሪቱ የነፋስ ኃይል መሣሪያዎችን የሚተክሉ ኩባንያዎች የሰው ኃይል የሚቀጥሩት ከሌሎች ሃገራት እንደሆነ በመጠቆም ይህም የእንግሊዝን ጥቅም የሚፃረር ነው ብሎታል፡፡
ሌላው በ2009 የታተመው የአውሮፓ ኮሚሽን የኢኮኖሚያዊ ሞዴል እንደሚያሳየው የታዳሽ የኋይል ምንጮች ከፍተኛ ውጪዎችን አስከትሉ ማለት እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ከዘርፉ ከሚገኘው የስራ ዕድልና ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሊያጋጥማቸው ይችላል በሚል አስነብቧል፡፡
ይህ ሪፖርት ይፋ የሆነው እንግሊዝ በንጹህ የኃይል ምንጭ ላይ በሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረገውን ውይይት ከማስተናገዷ በፊት ሲሆን የለንደኑ ጉባኤ አነስተኛ የካርቦን ልቀት ያላቸው የኃይል ምንጮችን በሚመለከት እንዲሁም በተያያዠ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
የህዝብ አስተያየት ውጤቶች እንደሚያሳዩት 64 በመቶ እንግሊዛውያን አዋቂ ሰዎች የታዳሽ የኃይል አማራጮች የወደፊቱ ትልቁ የኃይል ምንጭ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡
በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተደረገው የህዝብ አስተያየት ጥቆማ አንደሚያሳየው አብዛኛው ዜጋ የነፋስ የኃይል ምንጭን እንደሚፈለግና አሁን እንግሊዝ የነፋስ ኋይልን ለማመንጨት ምታደርገውን የሁለት በመቶ ድጎማ እንደሚደግፉም ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


