ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሮተርዳም ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች በበላይነት አሸነፉ

  • PDF

አዲስ አበባ, ሚያዝያ 8 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) - ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በሮተርዳም የተደረገውን ማራቶንን በሁለቱም ጾታዎች በበላይነት ማሸነፋቸውን ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ገለጸ።

ኢዜአ ማህበሩን ጠቅሶ እንደዘገበው በውድድሩ በወንዶች የማነ ጸጋዬ በሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ48ሰከንድ፣በሴቶች ቲኪ ገላና በሁለት ሰዓት ከ18ደቂቃ ከ58ሰከንድ በመግባት አስደናቂ ውጤት አስመዝግበዋል።

የሃያ ሰባት ዓመቱ ወጣት የማነ ጌቱ ፈለቀን በሁለተኝነት ውድድሩን ያሸንፋል ተብሎ የተጠበቀው ኬንያዊውን ሞሰስ ሞሶፕ ደግሞ ሦስተኛ ሆነው እንዲከተሉት አድርጓል።

''ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ወሳኙን እንቅስቃሴ ያደረጉት በ21ና በ25 ኪሎ ሜትር መካከል ነው ያለው'' ዘገባው፣''30ኪሎ ሜትር ላይ ሲደርሱ ውድድሩን መምራት መጀመራቸውን ያመለክታል'' በማለት ዘግቧል።

ውድድሩን በቀዳሚነት ያጠናቀቁት አትሌቶች 35 ኪሎ ሜትር ርቀትን በአንድ ሰዓት ከ42ደቂቃ ከ33 ሰከንድ ሮጠዋል።ሆኖም ጊዜው የሥፍራውን ክብረ ወሰን ለመስበር እንደማያስችል መታወቁን ገልጿል።

በውድድሩ የመጨረሻው ኪሎ ሜትር ላይ የማነ በ20ሜትር ልዩነት መገስገስ ቀጥሎ አሸንፏል።የገባበት ጊዜ አየለ አብሽሮ በቅርቡ በዱባይ ካስመዘገበው በ25ሰከንድ የዘገየ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓትም ሆኗል።

''የዓለምን ክብረ ወሰን ለመስበር ሳይሆን፤ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ መሮጣቸውን የማነና ጌቱ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

''በለንደን ኦሎምፒክ የሚያሳትፍ ሰዓት ማስመዝገብ ከሁሉም የበለጠ መልካሙ ነገር ነው'' ሲሉም አትሌቶቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በሴቶች የ24ዓመቷ ቲኪ ውድድሩን በዓለም አራተኛ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አጠናቃለች።ተወዳዳሪዎቿም በርቀት በማስከተልና ዘና ባለ ሁኔታ ለማሸነፍ መብቃቷን ዘገባው ያስረዳል።

ጣልያንዊያቷ ቫሌሪያ ስትራኔኦ በሁለት ሰዓት ከ23ደቂቃ ከ44 ሰከንድ ሁለተኛ ወጥታለች።የግል ምርጥ ሰዓቷንና የአገሯን ብሄራዊ ክብረ ወሰንም አሻሽላበታለች።

መሪማ ሐሰን በሁለት ሰዓት ከ25ደቂቃ ከ48 ሰከንድ በመግባት ሦስተኛ መውጣቷን የማህበሩን ምንጭ በማድረግ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 234 guests