ኢትዮጵያና ኡጋንዳን ጨምሮ በዓለም ላይ ካሉ ስድስት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቶች የሚገኙት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2004 (ዋኢማ) - በዓለም ላይ ያሉ ስድስት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቶች የሚገኙት ኢትዮጵያና ኡጋንዳን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች መሆኑን መሠረታቸው ብሪታኒያ የሆኑ አማካሪ ኢኮኖሚስቶች አስታወቁ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት በሁሉም ዘርፍ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ያለች አገር ስትሆን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በያመቱ 15 በመቶ ያህል ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገች ነው።

የአማካሪ ኢኮኖሚስቶቹ ተቋም ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በዓለም አፍሪካ ከእስያ ቀጥላ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች አህጉር ናት።

በአፍሪካ አሁንም ድህነት፣ ረሃብና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩም የዴሞክራሲ ማበብና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በተለይም ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሕጋዊ መሠረቶች በመቀመጣቸው የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ አህጉሪቱ እየመጣ ነው ብሏል ሪፖርቱ።

አፍሪካ ዶት ኖ የተባለ ድረገፅ ላይ የወጣው ይኸው ሪፖርት በ2010 መካከለኛ ገቢ ያላቸው አፍሪካውያን ቁጥር እያደገ ሄዶ 313 ሚሊየን መድረሱንና ይህም የአኅጉሪቱን ሕዝብ 34 በመቶ እንደሚያህል አመልክቷል።

ድረገፁ ላይ የወጣው ይኸው ዘገባ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር በቅርቡ ያደረጉትን ንግግር በመጥቀስ እንዳለው በአኅጉሪቱ አዲስ አስተሳሰብ ያላቸው መሪዎች ትውልድ ተፈጥሯል።

ብሌየር የኢኮኖሚና የሕግ ማሻሻያዎች በአህጉሪቱ መካሄዳቸው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ማለታቸውን አሥፍሯል።

ከዚህም ሌላ በምዕራብ የሚገኙ አንዳንድ ወገኖች ቻይና ወደ አህጉሪቱ በመግባቷ ይነቅፋሉ፤ ይሁንና ተጨባጩ ጉዳይ ግን ቻይና ካፒታልና አቅም ያላት አገር መሆኗ ነው ሲሉ መናገራቸውንም ገልጿል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 156 guests