‹‹የቴሌ የአገልግሎት ጥራት ጉድለት ከአቅም ጋር የሚያያዝ ነው››ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር

  • PDF

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ኢትዮ ቴሌኮም ተብሎ በአዲስ አደረጃጀት ከተቋቋመ በኋላ፣ ማኔጅመንቱን ፍራንስ ቴሌኮም የተባለው የፈረንሣይ ኩባንያ ተረክቦት በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡
የሁለት ዓመት ኮንትራት ፈርሞ በ30 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ማኔጅመንቱን የተረከበው ፍራንስ ቴሌኮም የኮንትራት ጊዜውን ከግማሽ በላይ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህ ወቅት መሥራት ያለበትን ያህል ሥራ ሠርቷል ወይ? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ በቴሌ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብዙ ጊዜ ትችት የሚቀርብበት የኔትወርክ መቆራረጥና በቅርቡም የቅደመ ክፍያ ካርድ አሞላል ችግር ታይቶበታል፡፡ ይህም አብዛኛውን ደንበኛ ከማማረሩም በላይ ቴሌ ምን እየሠራ ነው የሚለውን ጥያቄ በምሬት እንዲሰነዝር አድርጓል፡፡ በፍራንስ ቴሌኮም ማኔጅመንት የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያና የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ኢትዮ ቴሌኮም የሚል ስያሜ ይዞ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ያለውን እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የፍራንስ ቴሌኮም ዕጣ ፈንታና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ ሰብሳቢና የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩን ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል ባለፈው ረቡዕ በቴሌ ሞዴል የአገልግሎት መስጫ ተቋም ምርቃ ላይ ከሪፖርተር ጋዜጣና ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ዳዊት ታዬ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

-   የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ከተሸጋገረ በኋላ በተከናወኑ ሥራዎች ላይ የመንግሥት ግምገማ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- የቴሌኮም ዘርፍ ሰፊ ነው፡፡ አንድ ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ዓይነት ሥራዎች ናቸው ያሉት፡፡ ለውጡም አንድ ብቻ አይደለም፤ ብዙ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ነው የሚለወጠው፡፡ ተቋማዊ አደረጃጀቱ፣ መዋቅሩም ሆነ ሌላው ነገር በሙሉ እንደ አዲስ ነው የተጀመረው፡፡ አንዱ ትልቁ ነገር የተቋም መልክ ይዞ ወደ ሙሉ ሥራ መግባቱ ነው፡፡ የሰው ኃይሉን ቦታ ቦታ ማስያዝ፣ አንዳንድ ጉድለቶችን ማስተካከልና የመሳሰሉት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ምደባ ያላገኙት ደግሞ ተደራጅተው ኩባንያ እንዲያቋቁሙ ተደርጓል፡፡ (ህዳሴ የሚል ኩባንያ ተፈጥሮ ወደ ሥራ ተገብቷል)፡፡ እነሱም የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ትልቁ ነገር ተቋሙን እንደተቋም ሥራ ማስጀመር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የሚቀጥለው አገልግሎት የማዳረስ ሥራ ነው፡፡ ቀደም ብሎ የተጀመረው የማስፋፊያ ሥራ ነበር፡፡ በውሉ መሠረት የማስፋፋት ሥራው ተጠናቅቋል፡፡ የማስፋፊያ ሥራው ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም በተሟላ ሁኔታ የተጠናቀቀበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ቀሪውም እየተፈተሸ ወደ አገልግሎት የሚገባበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡ ማስፋፋቱ በዕቅዱ መሠረት የተሠራ ነው፡፡ ሽግግሩም እያለ ይሠራ ነበር፡፡ ብዙ ችግር አልገጠመውም፡፡ ዋናው ኔትወርክ ማቅረብ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ አገልግሎትን ለተጠቃሚው ወይም ለእያንዳንዳችን የማድረስ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ዙሪያ በተለይ በሞባይል ስርጭት ጥሩ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የሞባይልን አገልግሎት ለተገልጋዩ ለማድረስ በተሠራው ሥራ እስከ ታህሳስ 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ወደ 14 ሚሊዮን የሞባይል ደንበኞች እንዲኖሩን ተደርጓል፡፡ አሁን ይህ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ዕድገቱ ጥሩ ነው፡፡ ከአቅም አንፃር ሲታይ ጥሩ ተሠርቷል፡፡ እስከ ሰኔ 2004 ዓ.ም. 19 ሚሊዮን ደንበኞች ይኖሩናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ በዚህ አካሄድ የታቀደው ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ ስለዚህ ተደራሽነቱ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የጀመርነው በኋላ ቢሆንም ፍጥነት አለ፡፡ የኢንተርኔትና የብሮድባንድ አገልግሎት ደግሞ በዕቅድ ደረጃ ጥሩ ነው፤ እኛ ከምንፈልገው ደረጃ አንፃር ሲታይ ግን ገና ነው፡፡ ብዙ መሥራት አለብን፡፡ እንደሚታወቀው በብሮድባንድ አካባቢ የነበረው ችግር ዋጋው ነው፡፡ በዋጋ ጉዳይ በግል ደረጃ ይቅርና በተቋም ደረጃ ደንበኛ ለመሆን አስቸጋሪ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር አዲስ የዋጋ ክለሳ ተደርጐለታል፡፡ የተወሰነ ደረጃ መሻሻልም ሊኖር ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በግል ደንበኛ መሆን የሚቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ በግላችን የብሮድባንድ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን፡፡ ቤታችን ሆነን መጠቀም እንችላለን፡፡ ዋጋውም ቀንሷል፡፡ ሁሉም ይችለዋል ባይባልም አሁን ያለው ዋጋ ከአገልግሎቱ ጠቀሜታ አንፃር ለመገናኛ አገልግሎት መክፈል የሚችል ሰው ሊከፍለው የሚችለው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አሁን ያለን የብሮድባንድ ዋጋ ከሌሎች አገሮች ዋጋ ጋር ሲነፃፀርም ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡

በፊት የነበረን ዋጋ በዓለም ደረጃ ሲታይ ውድ የሚባል ነበር፡፡ በብሮድባንድ ዋጋ ውድነት በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጠን ነበር፡፡ አሁን ግን አጠቃላይ ደረጃችንን የምናየውና የምናውቀው በሚቀጥለው ዓመት ቢሆንም ደረጃችን በጣም ይሻሻላል፡፡ በዚህ ረገድ ወደተገልጋዩ ለመድረስ ጥሩ ዕድገት ታይቷል፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን ብዙ መሥራት አለብን፡፡ አገልግሎቱን ለማስፋፋት የሚያስችል አቅም አለን፡፡ ዋጋውንም የቀነስን በመሆኑ ለኅብረተሰቡ የማዳረስ ሥራችን እንቀጥላለን፡፡ ዋናው የሚያሳስበው ነገር ግን ጥራት ነው፡፡ ጥራት ላይ ገና ነን፡፡ ለውጦችና መሻሻሎች ቢኖሩም ነባሩን ከአዲሱ ጋር እያጣጣሙ መሄድ ላይ ግን ችግሮች አሉ፡፡ ቀጥታ ኔትወርክ ነው እየሠራን ያለነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ቅድመ ክፍያ ካርድ መሙላትን መመልከት ይቻላል፡፡ የሲስተም ዕድገት ስላለ የገጠመ ችግር ነው፡፡

እስካሁን በነበረው አሠራር ሦስት አራት ዓይነት ክፍያ ነው የነበረው፡፡ ገጠሩም ከተማውም ለየብቻ የተለያየ ክፍያ ነበራቸው፡፡ ይህንን የክፍያ ሥርዓት አንድ ወጥ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ይህ የሲስተም ዕድገት ነው፡፡ ነገር ግን ደንበኞችን ማስተናገድ ላይ ችግር ነበረው፡፡ ይህም ደንበኞችን አማሯል፡፡ የመጠቀሚያ ዋጋ መሙላት ያልተቻለበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ደንበኞችን አማሯል፡፡

ይህ የጥራት አካል ነው፡፡ በዕድገት ላይ የታየ ቢሆንም መፍጠን አለብን ማለት ነው፡፡ ችግሮች ባይታዩ ጥሩ ነው፤ ግን ሲታዩ ቶሎ ብለን መፍትሔ መውሰድ ሲገባን መጓተት አለ ማለት ነው፡፡ ይህ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ በቴሌ አገልግሎት የጥራት ችግር አለ፡፡ መንስዔዎቹም ይታወቃሉ፡፡ በኩባንያው [በፍራንስ ቴሌኮም] ደረጃ መሥራት ያለበትን ሥራ ስላልተሠራ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ፋይበር ሲቆረጥ ጥራት ብቻ ሳይሆን ግንኙነትም ይጠፋል፡፡ ይኼ ይደጋገማል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይልም ሲቋረጥ ችግር ይፈጠራል፡፡ የቴሌ አገልግሎቶች በአብዛኛው በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ናቸው፡፡ (ገጠር ላይ ያሉት በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ናቸው) እንዲህ ዓይነት ችግሮችም ሲታዩ በአገልግሎቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ስለዚህ ሌሎች ተደራራቢ ችግሮችም በጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ መሆናቸውን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለቴክኒካዊ ችግሮች መፍትሔ መስጠት አለብን፡፡ ከዚህ ውጭ ያለውን ችግር ለምሳሌ ኬብል የመቁረጥና የመሳሰሉትን ተግባራት ለማስቆም ኅብረተሰቡን የማስተማር ሥራ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች ለመፍታት ብዙ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡   

-   ከአገልግሎት ጥራት ጋር በተያያዘ ሰሞኑን የቅድሚያ ክፍያ ካርድ መሙላት አስቸጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ምንድነው ችግሩ? ችግሩ መቼ ሊቃለል ይችላል፡፡

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- ከሞላ ጐደል አሁን እንደገለጽኩት ነው፡፡ በአንድ በኩል ሲስተም ከመቀየር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ነባሩን ሲስተም በአዲስ የመቀየር ጉዳይ ነው፡፡ ሦስትና አራት ዓይነት የነበሩት ወደ አንድ ሥርዓት እየተቀየሩ ነው፡፡ ጉዳዩን ከተጠቃሚው አንፃር ስናየው ሥራ ለማቃለል ነው፡፡ የተለያዩ ካርዶች መያዝ የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ በገጠርና በከተማ ለኢቪዲዮ፣ ለሞባይልና ለመሳሰሉት እየተባለ የሚለያየውን በአንድ ካርድ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ አንድ ካርድ ገዝተህ የፈለግከውን አገልግሎት መጠቀም ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ይህ አገልግሎትን ማሻሻልና ከዕድገት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሲታይ ግን የቴሌ የአገልግሎት ጥራት ጉድለት ከአቅም ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ተጠቃሚው እየበዛ ነው፡፡ በአንድ ወር አንድ ሚሊዮን ተጠቃሚ የሚጨምርበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንጠብቀውም ባይባልም መፍጠን እንዳለብን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን አገልግሎቱን ለማሻሻል ሥራው ሲጀመር ተመጣጣኝ የሆነ ዝግጅት አልነበረም፡፡ በሙሉ አቅሙ ሊያስተናግድ የሚችል ሲስተም ከመጀመሪያው መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ይኼ ያሠራናል፤ በሒደት እናሻሽለዋለን ተብሎ ይገባል ግን ሳይሆን ይቀራል፡፡

-   እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመቅረፍ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- አሁን እኮ ተቃሏል፡፡

-   ለምሳሌ እኔ ትናንት አጋጥሞኛል?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- ሁለተኛ ብትደግም ይሠራልሃል፡፡ ለማንኛውም ችግሩን ማስወገድ አለብን፡፡ አሁንም የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ የማቃለያ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በሚቀጥለው ወርም የሚሠራ ሥራ አለ፡፡ አቅምን የመጨመር ጉዳይ ነው፡፡ አቅሙን እያሳደግ ካልሄድክ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሊሞላ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አቅሙን እያሳደግህ ትሄዳለህ፡፡ ሶፍት ዌር የማሳደግ ጉዳይ አለ፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዘ ፈቃድም አለ፡፡ መሠረተ ልማትም አለ፡፡ ምንም ውስብስብነት የለውም፡፡ ሆኖም አገልግሎቱ ስለማይገኝ ተጠቃሚውን ያበሳጫል፡፡ በጥቅሉ የተመቻቸና እንዲሁም የተደላደለ ሲስተምን ስትቀይር አቅሙን ከፍ አድርገህ ማስገባት ነበረብህ፡፡ ስለዚህ የዝግጅት ጉድለት አለበት ማለት ነው፡፡ ዝግጁቱን አስበህ ከፍ ያለ አቅም ይዘህ ካልሆነና ተቀራራቢ ከሆነ ዕድገቱ ቶሎ እየጨመረ መጨናነቅ ይፈጥራል፡፡ ሁሉም በአንድ ላይ ስለሚጠቃለል የአቅም ጉዳይ ይነሳል ማለት ነው፡፡ በጥቅሉ ለችግሩ መንስዔ በአንድ በኩል የዝግጅት ችግር ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ አስቀድመህ ማሰብ አለብህ፡፡ ፕላንም ስላለ ጭምር፡፡ ለምሳሌ አሥር ከነበረ ለሃያ ብለን ማዘጋጀት አለብህ ማለት ነው፡፡ አሥር ከነበረ አሥራ ሁለት ብለህ ከጀመርከው መጣበቡ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ችግሩ የአቅም ጉዳይ ነበር፡፡ አሁን እሱን የሚያቃልል ሥራ ነው የተሠራው፡፡ ዋናው መፍትሔ ግን ከአንድ ወር በኋላ አቅም የመጨመሩ ሥራ ይሠራል፤ መፍትሔውም ይኼው ነው፡፡

-   ከዋጋ አንፃር ሞባይልና መደበኛ ስልክን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በተለይ የሞባይል ታሪፍ አሁን ካለው ዋጋ በታችም መቀነስ እንዳለበት የሚናገሩ አሉ፡፡ የሰዎችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ባገናዘበ መንገድ መሆን አለበትም ይላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ታሪፍ ለመቀነስ የተያዘ ዕቅድ አለ?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- በነገራችን ላይ ታሪፉ የሚቀነስ አይደለም፡፡ መረጃዎችን ብታይ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ በዓለም ላይም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ዝቅተኛ ታሪፍ ካላቸው አገሮች አንዱ የኢትዮጵያ ነው፡፡ ቀደም ብሎም ቢሆን ውድ የሚባለው ታሪፋችን ብሮድባንዱ ነው እንጂ፣ የሞባይልና የመደበኛ ስልክ ታሪፍ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡ የዓለምን የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን መረጃ ሰብስቦ ሪፖርት የሚያደርገው የዓለም አቀፍ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኅብረት (ITU) መረጃዎችን ብትመለከት፣ ዝቅተኛ ታሪፍ ካላቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን ነው የሚጠቅሰው፡፡ እንደምታስታውሱት ከወራት በፊት ደግሞ ከከተማ ወደ ክልሎች የነበረው ታሪፍ ድሮም ዝቅተኛ ነበር፤ አሁን ደግሞ እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡

አንዳንድ አገሮች የድምፅ አገልግሎት በነፃ ይሰጣሉ፡፡ ‹‹ባንድል ሰርቪስ›› የሚባል ነገር አላቸው፡፡ አብዛኛው ገቢያቸው ዳታ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ገቢያቸውን ከዚህ አገልግሎት ስለሚያገኙ ደንበኛቸውን የድምፅ አገልግሎትን በነፃ እንሰጥኃለን ይሉታል፡፡ ለቤተሰብህም እንደ ምርቃት ነፃ አገልግሎት እንሰጣለን የሚሉ አሉ፡፡ ይህ የሚሆነው የበለጠ አገልግሎቱ ወደ ዳታ እየተቀየረ ሲሄድ የመቀነስ ዕድሉ ሊመጣ ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በነፃ የምትልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ዋናው ገቢህ ከብሮድባንድ፣ ከኢንተርኔትና ከኤስኤምኤስ ከሆነ ልታደርገው ትችላለህ፡፡ የእኛ ግን በግልባጭ ነው፡፡ ዋናው ገቢ የድምፅ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ደረጃም ቢሆን የእኛ ዋጋ ዝቅተኛ ነው፡፡ የዳታው አጠቃቀም እየጨመረ ካልሄደ በስተቀር አሁን ያለው ዋጋ ተመጣጣኝ ነው፡፡

-   የገጠር ተጠቃሚዎችን በተመለከተ ለምሳሌ በኬንያ በገጠር ከፍተኛ ተጠቃሚዎች አሉዋቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ገና ነው፡፡ በተለይ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ገና አላደገም፡፡ ይህንን ለማበረታታት ያደረጋችሁት ጥረት አለ?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- ይህ የመረጃ ጉዳይ ነው፡፡ በገጠር እኛ እንሻላለን፡፡ በገጠር ተደራሽነት እኛ የተሻለ ሥራ ሠርተናል፡፡ በሞባይል ቁጥር የእነሱ ይበልጣል፡፡ ግን ሩቅ የሆኑ ገጠሮችን በተመለከተ እኛ መሠረተ ልማት በማስፋፋት ረገድ እያንዳንዱ ቀበሌ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ በተደራሽነት የእኛ ይበልጣል፡፡ በሞባይል ቁጥር ግን የእነሱ ነው፡፡ እነሱን ከኢትዮጵያ ጋር ስታነፃፅረው በርከት ያሉ ከተሞች አሉዋቸው፡፡ አብዛኛው ከተማ ነው፡፡ ገጠሩ አነስተኛ ነው፡፡ የእኛ ግን በግልባጩ ነው የሚታየው፡፡ ከተሞቻችን ትንሽ ናቸው፡፡ በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ወደ 16 እና 17 ከመቶ ነው፡፡ ወደ 83 በመቶው የሚሆገው ደግሞ ገጠር ነው የሚኖረው፡፡ ስለዚህ እነሱ ከተማን ያዳርሳሉ፡፡ ከተማ ማዳረስ ብዙም ችግር የለውም፡፡ ችግሩ ገጠር ላይ ነው፡፡ መንገድ የሌለባቸውና ትራንስፖርት የማይገባባቸውን በሔሊኮፕተር ጭምር ሄደን ታወር ተክለናል፡፡ እንደዚህ የሠራ አገር አታገኝም፡፡ በዚህ ረገድ እንኳን ኬንያ ሌላውም አገር አልሠራም፡፡ ስለዚህ በገጠር የመሠረተ ልማት ሽፋን የእኛ ይበልጣል፤ ግን አገልግሎቱ ገና ነው፡፡ አሁን ነው እየተጀመረ ያለው፡፡ አሁን የገጠሩ እየተሸፈነ ነው ያለው እንጂ ሙሉ አገልግሎት አላገኘም፡፡ ዘግይተን ስለጀመርን ነው እንጂ በመሠረተ ልማት ደረጃ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ 

-    ከገቢ አንፃር ቴሌ በአምስትና በስድስት ወራት ውስጥ ወደ 5.6 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል የሚል መረጃ አለ፡፡ የሚገኘው ገቢ ታሳቢ ተደርጐ የአገልግሎት ታሪፉ የሚቀነስበት ሁኔታ ይኖራል?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- በዛ?

-   ለምሳሌ በዓመት ውስጥ ምን ያህል ይጠበቃል?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- በዛ ነው የምትለው? እኛ ደግሞ የምንለው አነሰ ነው፡፡ 5.6 ቢሊዮን ብር ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይ መሥራት አለብን የሚል አመለካከት ነው ያለን፡፡ መታየት ያለበት ስንት ተሠርቶ ነው ይህ የተገኘው በሚል ቁጥሩን ብናየው ትልቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹አርኩ›› የሚባል መለኪያ አለ፡፡ በዚያ ዝቅተኛ ነን፡፡ ቴሌኮሞችን የምታወዳድርበት ከአንዷ መስመር ስንት ገቢ ተገኘ በሚል ነው፡፡ በዚያ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ነው ከምንልበት ምክንያት አንዱ ታሪፉ ነው፡፡ ሌላው አገልግሎቱን በተመለከተ ቁጥሩ አሁን ገና እየጨመረ ያለው እንጂ በአገልግሎት ብዛት ገና ነን፡፡ በዚህ ምክንያት ገቢውን ለአገልግሎት ዓይነቶቹ አካፍለህ መስመር ስታስገባው ገቢው ዝቅተኛ መሆኑን ታያለህ፡፡ አንዱም ከእነሱ ጋር (ፍራንስ ቴሌኮም) የሚያጨቃጭቀን ይህ ነው፡፡ ወደ ዓለም አቀፉ ሌላው ቀርቶ ወደ አፍሪካ ልምድ ደረጃ አላመጣችሁትም ብለናል፤ እነሱ ዝም ብለው እየተናገሩ ሊኖሩ አይችሉም፡፡ የአገልግሎቱ ጥራት እየተሻሻለ በሄደ ቁጥር ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል ነው እኛ የምንለው፡፡ ገቢም ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ከታሪፍ ጋር አናያይዘው፡፡ ዕውነታውን ብታየውና ዓለም አቀፍ መረጃዎችን ብትመለከት አሁንም ታሪፉ ትንሽ ነው፡፡ ይህ ታሪፍ ስለበዛ እንቀንሰው በሚል ብንሄድ የኦፕሬሽን፣ የጥገናና ሌሎችም ብዙ ሥራዎች ስላሉ ይህ መሠራት አለበት፡፡

የመንግሥት በጎ ፈቃድ ተጨምሮበት ነው እንጂ ከውጪው አንፃር ታሪፋችን አነስተኛ ነው፡፡ አማካሪዎች እንዴት ይቀንሳል ነው የሚሉት፡፡ አንተ ደግሞ ካልወረደ ትላለህ፡፡ ተወዳዳሪ በሌለበትም ቢሆን ዋጋችን ዝቅተኛ ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ኬንያ አራትና አምስት ተወዳዳሪዎች ያሉዋቸው ቢሆንም የእኛ ታሪፍ ከእነርሱ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የሞባይልና የመደበኛ ስልክ ታሪፍ የእኛ ዝቅተኛ መሆኑን በመረጃ ማቅረብ ይችላል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ዋጋውን አሁን ባለው ተመጣጣኝ ደረጃ ያደረግንበት ምክንያት ደግሞ ኅብረተሰቡ የመክፈል አቅሙ ዝቅተኛ ስለሆነ ነው፡፡
ገቢያችንን በዋናነት በልማት ነው ማግኘት ያለብን ከሚል ነው፡፡ ለልማት ስንንቀሳቀስ እንጂ በታሪፍ ከቴሌ በሚገኘው ገቢ አይደለም ቁምነገሩ፡፡ ግን እሱም መስፋፋት አለበት፡፡ ዕዳ ስላለብን መክፈል ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ በነፃ ልታስኬደው አትችልም፡፡ ለማንኛውም ዋጋው ተመጣጣኝ ነው ወይ ብለህ ማነፃፀር አለብህ እንጂ ገቢው ስለጨመረ ብዙ ነው ብለህ ማሰብ የለብህም፡፡ በዚህ ዓይነት ነገ ገቢው 10 ቢሊዮን ብር ቢደርስና ገቢው እየጨመረ ቢሄድ እየተዘረፈን ነው ልትል ነው? 

-   የቴሌን ማኔጅመንት ኮንትራት የወሰደው የፍራንስ ቴሌኮም እስካሁን ያለው አፈጻጸም ምን ደረጃ ደርሷል ብላችሁ ታስባላችሁ? የእናንተ ግምገማ ምን ያሳያል?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- አፈጻጸሙ የተለያየ ነው፡፡ ቴሌኮም ሰፊ ዘርፍ ያለው በመሆኑ በሁሉም መስክ ለውጥ ትፈልጋለህ፡፡ በጣም ጥሩ የሄዱበት ነገር ቢኖርም ጥራት ላይ ግን አፈጻጸማችን ጥሩ አይደለም፡፡ የጥራቱ ችግር ግን የተወሰኑ ሰዎች ጉዳይ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ የኔትወርክ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ አንፃር ስናየው ደግሞ ማኔጅመንቱን እነሱ ስለወሰዱ የራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ለተቆረጠ ፋይበር እነሱ ተጠያቂ ናቸው ማለት አንችልም፡፡ ችግሩ ከተቋሙ ይወጣና ሌላ አካልን የሚመለከት ጉዳይ የሚሆንበትም አጋጣሚ አለ፡፡ ከተቋሙ ውጭ ኅብረተሰቡን የሚመለከት ጉዳይም አለ፡፡ ጠቅለል ተደርጐ ሲታይ ጥራት ባለው አገልግሎት አፈጻጸም ይጐላል፡፡ በዚህ ሰበብ ኢንተርኔት ይቆራረጣል፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ የጥራት ጉድለቱን የእናንተ ጉዳይ ነው ብሎ ማለት ዝም ብሎ መለጠፍ ይሆናል፡፡ ከፍራንስ ቴሌኮም ቁጥጥር ውጭ የወጣም ነገር አለ፡፡ እንደ መንግሥት እንደ ሕዝብ ማንቀሳቀስ ያለብን ነገር አለ፡፡ ይህ ጉዳይ በአገልግሎታችን ላይ ትልቅ ጉዳት ፈጥሯል፡፡ ለማንኛውም ጥራት ላይ ብዙ አልሄድንም፡፡ ለጥራት መጓደሉ የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ ለሁሉም መፍትሔ ማምጣት ባይቻልም በርከት ያለውን ችግር ግን ማቃለል እንችላለን፡፡ ይህም ሆኖ ግን እነሱን ማስተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ፈጥነው መፍትሔ ያለማምጣታቸውን ችግር አድርገን አይተነዋል፡፡ በሌሎች አገልግሎታቸው ባለው አፈጻጸማቸው ግን ጥሩ የሄዱበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ በሽያጭ፣ ከደንበኞች ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ የውስጥ አሠራር ሥርዓት፣ ዓለም አቀፍ የምንላቸውን የሥራ ሒደቶች ማስገባት፣ በማንዋል ሲሠሩ የቆዩትን ወደ ዘመናዊ አሠራር መቀየርና የመሳሰሉት ሥራዎቻቸው ጥሩ ናቸው፡፡ የውስጥ ሥራን ሥርዓት ማስያዝ ላይ ብዙ ርቀት ሄደዋል፡፡ 

-   የኢትዮ ቴሌኮምን ማኔጅመንት ኮንትራት የወሰደው ፍራንስ ቴሌኮም በኮንትራት ውሉ መሠረት መሥራት የሚገባውን ሥራ ባለመሥራቱ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጠው ይችላል? ኮንትራታቸውንስ የማራዘም ሐሳብ አለ?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- እነሱ እየጠየቁ ያሉትን ጥያቄ ነው የጠየቅኸኝ፡፡ እኛ ይራዘማል አይራዘምም ማለት አንችልም፡፡ እስካሁን ያከናወኑዋቸውን ሥራዎቻቸውን ደምረን ውጤቱን መገምገም አለብን፡፡ በመጨረሻ በምናገኘው ውጤት አርኪ ነው ካልን የተወሰነ ጊዜ ሊኖር ይችላል፡፡ እንደምታስታውሱት በኮንትራት ውሉ ውስጥ የስድስት ወራት ጊዜ አለ፡፡ አይ ከዚህ በላይ አንሄድም ካልን ከአሁን ጀምረን ሽግግሩን ልንጀምር እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ወደመተካት እንሄዳለን፡፡ በኮንትራት ማራዘምም ሆነ በእኛ ሰዎች የመተካቱ ሥራ ላይ ብዙ አማራጮች አሉን፡፡ ለማንኛውም በኮንትራት ውሉ ላይ ተጨማሪ ስድስት ወራት ለመስጠት የሚያስችል ዕድል ያለ ቢሆንም፣ ስድስት ወራትን ለመጨመር ከፈለግን እሱን እናስቀጥላለን፡፡ ኮንትራቱ በስድስት ወራት ይራዘም ቢባል እንኳን የሚራዘምላቸው ቀደም ብሎ በነበረው ሁኔታ አይደለም፡፡ ለውጦችና ዕድገቶች ስላሉን፣ የእኛም ሠራተኞች ኃላፊነቱን ለመውሰድ የሚችሉ ስለሆኑ እየተካን ልንሄድ እንችላለን፡፡ ወይም ከአሁን ጀምረን መረከብ እንጀምር ማለት እንችላለን፡፡ ነገር ግን አማራጮቻችን አይተን ውሳኔያችንን ከማሳወቃችን በፊት ግምገማውን ማድረግ አለብን፡፡ ለማንኛውም በዚህ ረገድ ብዙ አማራጮች አሉን፡፡ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመወሰን መገምገም አለብን፡፡ አማራጮችን እናያለን፡፡ በሦስት ወራት ውስጥ አንድ ደረጃ ላይ እንደርሳለን፡፡ እነርሱም ቁርጣቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡ 

- ፍራንስ ቴሌኮም ኮንትራቱ ይራዘምልን ብሎ በይፋ ጠይቋል?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- እነሱማ ይጠይቃሉ፡፡ አማካሪ ናቸው እኮ፡፡ ሠርተው ገንዘብ ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ገቢ የሚያስገኝ ሥራ አልፈልግም ልትል አትችልም፡፡ እነሱ ለብዙ ዓመታት መቆየት ይፈልጋሉ፡፡ እኛ ግን በዚህ ሐሳብ ልንቀጥል አንችልም፡፡ ዲዛይናችን ለዚያ አይደለም፡፡ አሁን ባለው ሽግግር አዳዲስ ነገሮች እንዲያስገቡልንና እንዲያስጀምሩልን ነው፡፡ ሠራተኞች እንዲለማመዱልን ነው፡፡ እንዲሠለጥኑልን ጭምር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ግን ገና ነው፡፡ 

-   አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮ ቴሌኮምን ማኔጅመንት ኢትዮጵያውያን መረከብ የሚችሉበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በየዘርፉ ተተኪ ሊሆኑ የሚችሉ ባለሙያዎችን በየሦስት ወሩ ማቅረብ አለባቸው፡፡ በዚህም መሠረት በየሦስት ወሩ እየገመገሙና እያጠኑ እገሌ ለዚህ ዘርፍ ተተኪ መሆን ይችላል እየተባለ ወደኛ ይመጣል፡፡ ይህ አሠራር ከመጀመሪያው ጀምሮ እየተሠራበት የቆየ ነው፡፡ እኛ እከሌ ይሁን ከምንል ሙያውንና ሥራውን እያዩ ወደ ላይ እያደገ የሚመጣውን ሰው በሁሉም ዘርፍ ተተኪ አምጥተዋል፡፡ ኃላፊነቱንና ሥራውን ሊቀበል የሚችል ሰው እያቀረቡ ነው፡፡ እነዚህን ተተኪዎች ደግሞ ማብቃት ያስፈልጋል፡፡ ጊዜ መስጠት አለብን፡፡ እነሱ [ፍራንስ ቴሌኮም] እንደ ምክትል ሆነው እንዲያገለግሉ፣ ተተኪው ደግሞ ከላይ ሆኖ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡ በዚህ ረገድ ድጋፍ እየሰጡን ይቀጥላሉ፡፡ ይህ በኮንትራት ውላችን ውስጥ አለ፡፡ እነርሱ ከታች ሆነው ለተወሰነ ወር ድጋፍ ይሰጡና ወደ መረካከቡ ይኬዳል፡፡ እስካሁን በዚህ ዓይነት መንገድ ነው እየሠራን ያለነው እንጂ ዝም ብሎ ኮንትራቱ አይራዘምም፡፡

-   በኮንትራት ውላችሁ ውስጥ እንደተካተተው ፍራንስ ቴሌኮም የሚገባውን ሥራ እየሠራ አለመሆኑ ከተረጋገጠ ሊወሰድበት የሚገባ ዕርምጃ አለ፡፡ በዚህ ረገድ በእስካሁኑ ቆይታው በኮንትራት ውሉ መሠረት ባለመሥራቱ ምን ዕርምጃ ወሰዳችሁ?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- ያባረርንባቸው ሰዎች እኮ አሉ፡፡ በቃል ሳይሆን እነዚህ እነዚህ ብቃት የላቸውም፤ የእኛን ልጆች ማስተማር ስለማይችሉ አባራችሁ በሌሎች ተኩ ብለን አምስት ስድስት የሚሆኑትን እንዲባረሩ አድርገናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃዎች እየታዩ ይወሰዳሉ፡፡ እስከ ኮንትራት ማጠናቀቂያው ድረስ ዝም ብለህ ጠብቀህ መጨረሻ ላይ እቀጣችኋለሁ የምትልበት ነገር የለም፡፡

-  ኢትዮ ቴሌኮም በመንግሥት እጅ እስከ መቼ ይቆያል?

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፡- መንግሥት እስከፈለገው ድረስ ይቀጥላል፡፡ የአጭር ጊዜ ዕቅድ የለም፡፡ በመንግሥት ባለቤትነት መመራቱን ይቀጥላል፡፡ የተወሰነ ጊዜ ከሄድን በኋላ ደግሞ እናየዋለን፡፡ (ምንጭ ሪፖርተር)

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 216 guests