ወርቅና ፋንዲያ፤ ያልተገባ ንፅፅር

  • PDF

 

ኢብሳ ነመራ

ኤርትራ ጦርነት እየተካሄደባት ያለች ሃገር አይደችም፤ የእርስበርስም ሆነ የውጭ ጦርነት የለባትም። ይሁን እንጂ ሃገራቸውን ለቀው የሚሰደዱ ኤርትራውያን ቁጥር ረጅም ግዜ የቆየ አስከፊ ጦርነት እየተካሄደባቸው ከሚገኙት ሶሪያና ኢራቅ በመቀጠል ከፍተኛውን ቁጥር ይዘዋል። እርግጥ ስደት በየትኛውም ሃገር የነበረ፣ ያለና ለወደፊትም የሚኖር ነው። ሰዎች ከደሃ ሃገር ብቻ ሳይሆን የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ካሉ ሃገራትም ይሰደዳሉ፤ ለስራ፣ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወዘተ። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የሚገለባበጥበት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መስፋፋት የብዙ ታዳጊ ሃገራት ዜጎችን ህይወት አደገኛ በሆነ አኳኋን እንዲሰደዱ አነሳስቷል። ኢትዮጵያውያንም የዚህ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ከመሆን አላመለጡም። ያም ሆነ ይህ በኤርትራ የሚታየው የሃገሪቱ ዜጎች ስደት ከጦርነት ውጭ በሆነ ሁኔታ ታይቶ የማይታወቅ ነው።

ይሁን እንጂ የኤርትራ መንግስት  የዜጎቹን የስደት መንስኤ የማስተካካል ፈላጎት እያሳየ አይደለም። እንዲያውም በገሃድ የሚታየውን የኤርትራውያን ስደት ሲክድ ነው የሚደመጠው። በቅርቡ በኬንያ የኤርትራ አምባሳደር በየነ ርእሶም በዛው ሃገር የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሆኑት ዲና ሙፍቲ ጋር ኬ ቲ ኤን በተሰኘ የኬንያ ቴሌቪዥነ ቶክ ሾው ላይ ቀርበው በሁለቱ ሃገራት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ክርክር ቢጤ በገጠሙበት ወቅት የኤርትራው አምባሳደር ከሃገራቸው የተሰደደው አርትራዊ ቁጥር ከ800 እንደማይበልጥና ኤርትራዊ ነን የሚሉት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን መናገራቸው ለዚህ በአስረጂነት ይጠቀሳል። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ በኢትዮጵያ የምትገኘ ኤርትራዊ በሰጠችው አስተያያት፣ በሶስት ቀናት ውስጥ 800 ኤርትራውያን ወደኢትዮጵያ ይገባሉ ማለቷ የኤርትራ መንግስት ምን ያህል እውትን ተቀበሎ የማሰተካካል ፈላጎት እንደሌለው የሚሳይ ነው።

ኤርትራውያን ከዚህ ቀደም በሰላማዊ ሃገር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲሰደዱ ያደረጓቸው ምክንያቶች ላይ ብዙ ስለተወራ ለማስታወስ ያህል በጥቂቱ አነሳለሁ። ኤርትራ ነፃ ሃገር ሆና ከተመሰረተች በኋላ ባሉት ዓመታት  የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለማሻሻል ምንም አይነት የልማት ስትራቴጂ ነደፎ አልተንቀሳቀሰም። በግብርና ላይ ጥገኛ የሆነው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከመሻሻለ ይልቅ እያሽቆለቆለ ነው የሄደው። በሃገሪቱ የነበረው የጎጁ ኢንደስትሪ ከህዝቡ የስራ ባህል ጋር ኢኮኖሚውን ወደኢንደስትሪ ለማሸጋጋር ጥሩ መደላድል ነበር። ይሁን እንጂ ይህ በተለይ አብዛኞቹ የሃገሪቱ ዋና ከተማ - አስማራ ነዋሪዎች የተሰማሩበት የጎጆ ኢንደስትሪ፣ እንኳን የሃገሪቱን እድገት ሊደግፍ ባለቤቶቹንም ማሳደር አቀቶት ተንኮታኩቷል።

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ከነበሩት ጋር ሲነፃፃሩ ግዙፍ ሊባሉ የሚችሉት የጨርቃጨርቅና የአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች ምንም አይነት ማስፋፋያ አልተደረገባቸውም። ከዚህ በተጨማሪ በእርጅና ምክንያት ማምረት ወደማይቸሉበት ደረጃ ተሸጋግረዋል። ይህ የሆነው በስርአቱ ፍፁም አምባገነናዊነት ሳቢያ ኤርትራውያንም ሆኑ የውጭ ሃገር ባለሃብቶች በሃገሪቱ በኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ፍቃደኞች ባለመሆናቸው ነው። በዚህ አኳኋን የኮሰሰውን የሃገሪቱ ኢኮኖሚ የተደገፈው የኢሳያስ መንግስት ደግሞ ልማት ዋነኛ አጀንዳው አይደለም፤ የልማት በጀት የመመደብ አቅምም የለውም። በዚህ አኳኋን አበረታች ደረጃ ላይ የነበረው የሃገሪቱ የጎጆ ኢንዱስትሪም ሆነ ሌሎች ኢንደስትሪዎች ጎልብተው ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ይልቅ እንደነበሩ መቀጠል እንኳን በማይችሉበት ሁኔታ ቀንጭረዋል፤ የከሰሙም አሉ።

የኤርትራ መንግስት ማቆየት የሚፈልገው ትውስታም የወደፊት ራእዩም ጦርነትና ጦርነት ብቻ ነው። አፈራቸው ተጠራርጎ አንዲት አረንጓዴ ቅጠል የማይታይባቸው የኤርትራ ተራሮች አገግመው ለልማት እንዲውሉ ከማደረግ ይልቅ፣ በነፃነት ትግሉ ወቅት ተራሮቹ ላይ ተሰርተው የነበሩትን ወታደራዊ ምሽጎች የማደስ ስራ ነው የተሰራው። ኤርትራ ከረጅም ግዜ የነጻነት ትግል ተላቃ ሳትረጋጋ ነበር የኢሳያሰ አመራር የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎትን ያወጀው። ከዚያን ግዜ ጀምሮ እስካሁን የብሄራዊ ውትድርና የግዳጀ አገልግሎቱ ቀጥሏል። እስካሁን ለግዳጅ የሄደ እንጂ የተመለሰ ወጣት አልታየም፤ በግዳጅ ላይ ያሉ ኤርትራውያን መቼ ወደሰላማዊ ሲቪል ህይወታቸው እንደሚመለሱ የሚያውቅ ኤርትራዊም የለም።

ኤርትራ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት ያስችላት የነበረውን ዩኒቨርሲቲዋን (አስመራ ዩኒቨርሲቲ) ዘግታለች። ለኤርትራ መንግስተ ዩኒቨርሲቲ ስርአቱን የሚቃወሙ ምሁራንን ከመፍጠርና በስርአቱ ላይ ስጋት ከማሳደር ውጪ ዋጋ ያለው ሆኖ አልታየውም። ይህ ደግሞ ተምረው የተሻለ ህይወት መምራት የሚፈልጉ ወጣቶችን ተስፋ የሚቀጭ ድርጊት ነው።

ይህ  በኤርትራ ያለውን ሁኔታ ለማሳየት ያህል በአጭሩ የተገለጸ እውነታ ኤርትራ ነፃነቷን ባወጀችበት ወቅት ወጣት የነበሩ የአሁን ጎልማሶች በመከነው ነፃነታቸው በግነው በሃገራቸው ተስፋ እንዲያጡ አድርጓቸዋል። ከነፃነት በኋላ የተወለዱ ወጣቶች መጪ ህይወታቸው ድቅድቅ ጨለማ እንዲሆን ከወዲሁ ወስኗል።  ኤርትራውያንን በአንድ ሰላማዊ ሃገር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሃገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ያስገደደው ይህ ከላይ ያሰፈረኩት በግልፅ የሚታይ፤ የአደባባይ እውነታ ነው።

እነዚህ በተለያዩ ሃገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሰየመው የኤርትራ የሰብአዊ መብት አያያዝ አጣሪ ቡድን ያወጣውን በሃገሪቱ ያለውን አስከፊ የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚያመለክት ሪፖርትና በሪፖርቱ ላይ የቀረበውን የኤርትራ ባለስልጣናት ፈፅመዋል በተባሉት ወንጀል ለፍርድ እንዲቀርቡ የሰጠውን ምክረ ሃሳብ በመደገፍ በኢትዮጵያ ትግራይና አዲሰ አበባ፣ በስዊዘርላንድ ጄኔቭ፣ በእስራኤልና ሌሎችም ቦታዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል። እርግጥ ሪፖርቱን በመቃወም የተሰለፉም እንደነበሩ ሰምተናል፤ በስዊዘርላንደ ጄኔቭ።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሰየመው የኤርትራ የሰብአዊ መብት አያያዝ አጣሪ ቡድን ያወጣው ሪፖርት በተለያዩ ድረገፆች ላይ ስለተለጠፈ፣ ኤርትራውያኑ ሪፖርቱን በመደገፍ ያካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍም እንዲሁ በተለያዩ ሚዲያዎች በስፋት ስለተዘገበ አልመለስበትም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኤርትራ መንግስት ላይ የወጣውን የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ዋጋ ያሳጣል ያሉትን አቋም አንጸባርቀዋል። የዚህ ፅሁፍ ትኩረትም እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በተለይ በጄኔቭ ሪፖርቱን በመቃወም የተደረገው የተቃወሞ ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያውያንም ተሳትፈዋል። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የኢሳያሰ አፈወርቂ መንግስት ኢትዮጵያ ወረራ ልትፈፅምብን ነው የሚል ስጋትን በመፍጠር የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ቀጠናው የማተራመስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ የሆኑ ግንቦት 7ን የመሳሳሉ አሸባሪ ቡድኖች አጋፋሪዎች ናቸው። ኢትዮጵያውያኑ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ሪፖርቱን ተቃውመው የተሰለፉት፣ በኤርትራ መንግስት ትዕዛዝ ነው፤ በግንቦት 7 በኩል በተላለፈ ትዕዛዝ።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኤርትራውያን ላይ የሚደርሰውን፣ በዚህ ዘመን ይፈፀማል ተብሎ የማይገመት አስከፊ የሰብአዊ መብትና የነጻነት ጥሰት ችላ ብለው የኤርትራን መንግስት የሚደግፍ አቋም መያዛቸው በዙዎችን በተለይ ኤርትራውያንን እጅግ አስገረሟል፤ አሳዝኗልም። ኤርትራውያኑ፣ በስቃያቸው በሚቆምሩት  በእነዚህ የኢሳያስ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርጊት እጅግ አዝነዋል፤ ጣልቃ ገብነታቸውም አናዷቸዋል።

ከእነዚህ ምንም የማያውቁ ኢሳያስ አፈወርቂና የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች የአመለካካት አባቶች የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አጣሪ ቡድን ሪፖርት ዋጋ ሊያሳጣ ያስችላል ያሉትን አቋም በይፋ የገለጹበት ሁኔታ አለ። ቀዳሚውና በዚህ ፅሁፍ የማተኩርበት፣ በኢትዮጵያም የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈፀማል፤ አጣሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን ትቶ ንጹኋን ኤርትራ መንካቱ ተገቢ አይደለም የሚል ነው። ይህ አቋም የኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ አማካሪ የማነ ገብረ አብ በጄኔቨ ተገኝተው ከገለፁት የኤርትራ መንግስት አቋም ጋር ተመሳሳይ ነው። የኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ የማነ በሪፖርቱ ላይ አቋማቸውን ሲገልጹ ኤርትራን ለመወንጀል የሚጣደፉ አካላት በራስዋ ህዝብ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የምትፈፅመውና ጦርነት የምትከፍተው ኢትዮጵያ ሆና ሳለች እንዳላዩ ያልፏታል ነበር ያሉት። የኤርትራ የትርምሰ ስትራቴጂ አስፈፃሚ አሸባሪ ቡድኖች አጋፋሪ ኢትዮጵያውያንም ይህንኑ ነው ያንጸባረቁት፤ የታዘዙትን ነው የፈፀሙት ማለት ነው።

ይህን የኤርትራ መንግስት የያዘውንና የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያስተጋቡትን በኢትዮጵያም የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈፀማል የሚል አካሄድ በኢትዮጵያ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በአጭሩ እንመለከተው።

በዚህ ምድር የመንግስት ህግና ፖሊሲ የሚፈፀመው በሰዎች ነው። ሰዎቸ ደግሞ የተለያየ ባህሪና ሰሜት አላቸው። እንዲሁም ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ተለዋዋጭና አንዳንዴ በተለመደው አሰራር ማስተናገድ የማይቻልበት አጋጣሚ አለ። እነዚህ ሁኔታዎች በየትኛውም ሃገር ሰብአዊ መብቶችንና ነፃነቶችን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ እንዳይቻል ያደረጉበት ሁኔታ አለ። የዳበረ የዴሞክራሲ ባህልና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ያሏቸው ምእራባውያንም ቢሆኑ ሰብአዊ መብቶችንና ነፃነቶችን በተሟላ ሁኔታ ማክበር እንዳልቻሉ ግልፅ ነው። ገና ታዳጊ ዴሞክራሲ ያላት ኢትዮጵያም ከዚህ ውጭ ይደለችም።

በመርህ ደረጃ ሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች ምንም ሳይሸራረፉ መከበር ያለባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአንድ ሃገር ያለን የሰብአዊ መብት አያያዝ የመገምገም ስራ በቀዳሚነት ከህገመንግስት ጀመሮ በሃገሪቱ ባሉ ህጎች ላይ የሰፈሩ  የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲሁም የሰብአዊ መብት መከበርን ለማረጋጋጥ ከተዘረጋው ስርአት አኳያ የሚታይ ይሆናል።

የኢፌዴሪ ህገመንግሰት አንድ ሶሰተኛ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች የሰፈሩበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቻው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች የሃገሪቱ ህግ አካል መሆናቸው በህገመንግስቱ ተደንግጓል።  ህገመንግስቱ የሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበርን ማረጋገጥ የሚያስችል ስርአትም አስቀምጧል። ከእነዚህም መሃከል በሃገሪቱ ያለ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን የማዳመጥና የመመርመር እንዲሁም እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ስልጣን በህገመንግስቱ የተሰጠው የሰበአዊ መብት ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደተግባር መግባቱ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

ኮሚሸኑ በሃገሪቱ ያሉ የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚጎለብትበት ሁኔታ ላይ ይሰራል። የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ጥናቶች ያካሂዳል፣ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ያዘጋጃል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት አቤቱታዎችን ያዳምጣል፣ እንዲስተካከሉ ለሚመለከተው ክፍል ያሳስባል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፀሟል የሚል እምነት ሲኖረው በራሱ ተነሳሽነት እንዲሁም ጥያቄ ሲቀርብለት ጉዳዩን መርምሮ ሪፖርት ያቀርባል። ባካሄደው መጣራትም ሊስተካከሉ ይገባል ያላቸውን ግድፈቶች እንዲስተካካሉ ያሳስባል፣ በህግ ሊጠየቁ ይገባል ያላቸውን አካላትና ግለሰቦች ይጠቁማል፣ ጥቆማውና ማሳሰቢያው ተግባራዊ መሆኑን ይከታተላል ወዘተ። ኮሚሸኑ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሃገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝ የድርጊት መርሃ ግብር በማወጣት አፈፃፀሙን ይከታተላል፤ ይገመግማል። በመርሃ ግብሩ መሰረት የተከናወኑ የሰብአዊ መብት አፈጻጸሞችን ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በማቅረብ ያስገመግማል፤ አስተያየቶችን ይቀበላል። በያዝነው ዓመት 2ኛው የሰብአዊ መብት አጠባባቅ የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች በአጠቃላይ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ እንዲሁም የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል - ሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች . . . ላይ አተኩረው የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ የሰብአዊ መብት ማህበራትን ማቋቋም ይችላሉ። እነዚህ በዜጎች የሚመሰረቱ የሰብአዊ መብት ማህበራት የሃገሪቱ ሰብአዊ መብት እንዲጎለብት ጥናቶችን የመስራት፣ ስልጠናዎችን የመስጠት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት አቤቱታዎችን ተቀብለው ወይም በራሳቸው ተነሳሸነት መርምረው ያገኙትን ወጤት በይፋ ለህዝብና ለመንግስት የማሳወቅ፣ የህግ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግና የማሳሰብ ህገመንግስታዊ መብት አላቸው። በዚህ መሰረትም የተደራጁ በርካታ ማህበራት በሃገሪቱ በመነቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚሀ መሃከል የሰብአዊ መብት ጉባኤንና የሴት የህግ ባለሞያዎች ማህበርን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

እናም በኢትዮጵያ የሰበአዊ መብት ሙሉ በሙሉ ተከበሯል ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ ባይኖርም፣ የሰብአዊ መብትና ነፃነት ጉዳይ እንደኤርትራ ኢሳያስ አፈወርቂና ባለሟሎቹ እንደፈለጉ እንደሚደፈጥጡት ስድ አልተተወም። ሰብአዊ መብትን ማስከበርና ማረጋጋጥ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ፣ መቆጣጣርና ማስፈፀም የሚችሉ ተቋማትና ስርአት ተዘርግቷል።

በመሆኑም የተባባሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኤርትራ ላይ እንዳደረገው ኢትዮጵያ ላይ ልዩ ማጣራትን አከናውኖ ሪፖርት ማቀረብ አይጠበቅበትም። ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ከተባባሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር አብራ ስለምትሰራ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚመለከት መረጃ አለው፤ ልዩ ማጣራትና ብርበራ አያሰፈልገውም። በአጠቃላይ ከላይ የተገለፀው የኢሳያስ አፈወርቂ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች ያነሱት የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት አያያዝ ለምን አላጣራም በሚል ከሰብአዊ መብት አኳያ ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማነፃፃር የተደረገው ሙከራ እጅግ የተለያዩ ነገሮችን ለማነፃፃር እንደመሞከር ይቆጠራል። በኢትዮጵያና በኤርትራ ያለው የሰበአዊ መብቶችና ነጻነቶች አያያዝ ከኤርትራ ጋር ማነፃፃር ወርቅን ከፋንዲያ ከማነፃፃር በምንም መልኩ አይለይም።