ሠላም ናፋቂ ሠሚ ያጡ ድምፆች

  • PDF

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2/2007 አ.ም- « አቱም ሰባት ማማ ትሓመናላ» የሚለው ዜማ ከመድረኩ ሲሰማ ብዙዎች ከመቀመጫቸው በመነሳት በጭብጨባ አጀቡት፡፡ ከያኒው በመድረኩ ላይ በመንጎራደድ በግሩም ጣዕመ ዜማ መልዕክቱን ማስተላለፉን ተያይዞታል፡፡ «እናታችን ታማለች» የሚለው ዜማ ብዙዎችን በሀዘን ድባብ ወስጥ ከቶ በስሜት ገንዳ ውስጥ እንዲዋኙ አደረገ፡፡ በትዝታ ሰረገላ ወደ ኋላ ወስዶ ስለእናታቸው እንዲያስቡ ገፋፋቸው፡፡ በጭብጨባ ሙዚቃውን እያጀቡ በአካል አዲስ አበባ በሀሳብ ኤርትራ ደርሰዋል፡፡

የፕሮግራሙ ታዳሚዎች እናታቸው ጤነኛ በነበረችበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ አስታወሱ፡፡ ያኔ ልጆቿን በዕቅፏ ሰብስባ የእናትነት ፍቅርን ትለግሳቸው ነበር፡፡ የፍቅርና የሠላም ካባን እንዲከናነቡ የእናትነት ድርሻዋን ተወጥታለች፡፡ ልጆቿም እናታቸው ጤናዋ ተጠብቆ ሠላምና ፍቅር ነግሶባት ለዘላለም እንድትኖር ይጸልዩ ነበር፡፡ የያኔው ሙዚቃ እናታቸው ስላደረገችላቸው ውለታ የሚሰብክና የሚያሞግስ ነበር፡፡ ልማት፣ ሠላምና ዕድገትን የሚያንፀባርቅና የሚያበስር፡፡
ዛሬ ታዲያ ያ ሁሉ ቀርቷል፡፡ ኤርትራ ሠላም ርቋታል፤ጤናዋ ታውኳል፡፡ በጣሙን ታማለች፡፡ ህመሟ ከመሻል ይልቅ እያደር እየባሰባት ነው፡፡ መድኃኒት አጥታ በክፉ ደዌ እየተሰቃየች ነው፡፡ ዙሪያዋን ከበዋት ሲሞጋግሷት፤ሲያወድሷት የነበሩት ልጆቿ ከአጠገቧ እንዲርቁ ተገደዋል፡፡ እጣ ፋንታቸው የስደትን በር ማንኳኳት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የሚወዷት እናታቸውን ያለውዴታቸው በግዴታ እንዲርቋት ተደርጓል፡፡ የእናታቸው መታመም ህመም ሆኖባቸዋል፡፡ ሙዚቃውም እናታችን ታማለች ሆኗል፡፡ ለእናታቸው ህመም መድኃኒት ፍለጋ ድምፃቸውን ጎላ አድርገው እያሰሙ ነው፡፡

ሁሉም ኤርትራዊ ስለ እናቱ ህመም መጨነቅን የየዕለት ሥራው አድርጎታል፡፡ ለታመመች እናቱ መፍትሔ ፍለጋ የአቅሙን ከመባተል አልቦዘነም፡፡ ፍላጎቱ ከፍተኛ ቢሆንም አቅሙ ግን ውስን ሆኖበት መፃዒውን ጊዜ በተስፋ ይጠብቃል፡፡ እናቱ ከበሽታ ተላቃ ፈውስ አግኝታ እንደሚያይ ተስፋ ያደርጋል፡፡ እናቱን ለህመም የዳረጓት ነቀርሳዎች ተመንግለው ተጠያቂ የሚሆኑት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ይጠብቃል፡፡ አዎን «እማማ ኤርትራ ከአፋኞች እጅ ተላቃ ልጆቿን ሰብስባ በሠላም የምትኖርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም» ይላል፡፡ የሠላም አየር የሚተነፈስባት ምድር ትሆናለች፡፡ ከጎረቤቶቿ ጋር በሠላምና በፍቅር የምትኖርበት ጊዜም እሙን እንደሚሆን ይተማመናል፡፡
በአፋኙ አገዛዝ ከሚወዷት አገራቸው እንዲሰደዱ የተደረጉት ኤርትራውያን የተለያዩ አገራትን መዳረሻቸው አድርገዋል፡፡ በማያውቁት አገር የስደት ኑሮን ለመግፋት ተገደዋል፡፡ የኤርትራውያን ስደተኞች ተቀዳሚ የስደት ምርጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ደግሞ ለብዙዎች መጠለያ ሆናለች፡፡ የሠላም አየርን ለመተንፈስ «ከኢትዮጵያ ውጭ የምናማትረው አገር የለም» ሲሉም ይደመጣል፡፡ ነፃነታቸው ተከብሮና ተገቢው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚኖሩም በኩራት ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ እያደረገላቸው ላለው ድጋፍም ክብርና ምስጋና እያቀረቡ ነው፡፡

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በአዲስ አበባ የሙዚቃ ኮንሰርት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በርካታ ስደተኞችን በአንድነት ባሰባሰበው ኮንሰርት ብዙ ኤርትራውያን ታድመዋል፡፡ የኤርትራ ህዝቦች የትጥቅ ትግል የጀመሩበትን 54ኛ ዓመት ለማስታወስ በተዘጋጀው ኮንሰርት ብዙዎች ተደስተዋል፡፡ ከአገራቸው ቢሰደዱም የሚፈልጉትን በዓል «ሁለተኛ አገራችን» በሚሏት ኢትዮጵያ ለማክበር በመቻላቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆኗል፡፡  
ዶክተር በረከት ወልደአብ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ ከኤርትራ እግራቸውን ለስደት አነሱ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጨቋኙና አፋኙ የኢሳያስ መንግስት በአገራቸው እንዳይኖሩ፣እንዳይሰሩ ዕድሉን ስለነፈጋቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ኤርትራ ወስጥ ሀሳብን በነፃነት መግለፅና መቃወም የማይታሰብ በመሆኑ በስደት አገር ሆነው ለመቃወም ተነሱ፡፡ የኤርትራ ችግር እያደር እየባሰበት በመምጣቱ ወጣቱ በብዛት ከአገሩ እየተሰደደ ተቃዉሞውን እያሰማ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ድምፁን የሚሰማው አላገኘም ይላሉ፡፡ ብዙዎች ቢጮሁም የሚሰማቸው በማጣት እየተሰቃዩ ነው፡፡

እንደ ህዝቡ ብሶትና ተቃዉሞ ቢሆን አፋኙ አገዛዝ ይህን ያል ጊዜ ይቆያል የሚል እምነት አልነበራቸውም፡፡ አሁንም ቢሆን ግን ዕድሜው አጭሩ መሆኑ ከሚሰራቸው ሥራዎች እየታየ ነው፡፡ በዕድሜ የገፉ አረጋውያንና ዓይነ ስውራን ሳይቀሩ በብዛት ወደ ኢትዮጵያ እየጎረፉ ነው፡፡ ስቃይና መገፋቱ ይበልጥ ብሶበታል፡፡ አፋኙ አገዛዝ ለህዝቡ ጥያቄ ጥይትና እስርን ምላሽ አድርጎ ገፍቶበታል፡፡ ኤርትራ «ፀሀይ እያለ ፀሀይ የጨለመባት አገር ሆናለች» ብለዋል -ዶክተር በረከት፡፡
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል እያደረገች ያለውን ድጋፍ ዶክተር በረከት እጅግ የሚደነቅና የሚያስደስት ነው ይላሉ፡፡ የሁለቱ አገራት ህዝቦች በታሪክና በባህል የሚመሳሰሉ በመሆናቸው በመካከላቸው ልዩ ፍቅር አለ፡፡ ለዚህም ማሳያው ስደተኛው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከድንበር ጀምሮ በኢትዮጵያውያን የሚደረግለትን ወደር የለሽ አቀባበል መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኤርትራውያን የነፃነት ጥማታቸው ተሳክቶ ሠላም ሰፍኖ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ዶክተር በረከት ሙሉ ተስፋ አላቸው፡፡

ሌላው ስደተኛ ሼህ አሊ መሃመድ አገራቸውን ቢወዱም አፋኙ ሥርዓት ነፃነታቸውን በመግፈፉ ስደትን መርጠዋል፡፡ የኢሳያስ አገዛዝ ጨቋኝና ህዝቡን ለእንግልት የሚዳርግ ሥርዓት ነው ይላሉ፡፡ በሥርዓቱ ተጠቃሚ የሆነዉ ቡድን አባላት ዜጎችን በጭለማ ቤት ውስጥ ለረጅም ዓመታት በማሰር ያሰቃያሉ፡፡ ህፃናትና ሴቶችን ያንገላታሉ፡፡ «ኢሳያስ እስካለ ድረስ ሠላምና ልማትን ማሰብ የማይሳካ ነው»የሚሉት ሼህ አሊ በትግልም ይሁን በፈጣሪ ትዕዛዝ ኢሳያስ ሲወድቅ ሠላምና ዲሞክራሲ መስፈኑ እንደማይቀር ይናገራሉ፡፡

እሳቸው በበኩላቸው ከጤና ጋር በተያያዘ የትጥቅ ትግል ማድረግ ባይችሉም ሀሳብ በመስጠትና ልምዳቸውን በማካፈል ሥርዓቱ እንዲወገድ የበኩላቸውን ጥረት ለማድረግ ተዘጋጅተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በስደት ባሳለፉት ሰባት ዓመት የህዝቡ ድጋፍ አልተለያቸውም፡፡ ለዚህም ምስጋናዬ የላቀ ነው ይላሉ፡፡

የስደት ኑሮ ግድ ቢሆንባቸውም የኢትዮጵያውያን ድጋፍና እንግዳ ተቀባይነት ስሜታቸው እንዳይረበሽ  አድርጓል፡፡ አቶ ግደይ ፀሀይም ይህንኑ ነው የሚመሰክሩት፡፡ «የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለኤርትራውያን የሚያደርጉልን ድጋፍ አገራችን ያለን ነው የሚመስለን» ብለዋል፡፡ ኤርትራውያን የሠላም ጥማት እርካታን የሚያጣጥሙበት ጊዜ ቅርብ ነው ባይ ናቸው፡፡ ህዝባዊ ግንባር ንዲሞክራሲን ፍትህን (ህግደፍ) ቡድኖችም ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጡም፡፡
ህዝቡ ለአገሩ ሠላምና ነፃነት የከፈለው የህይወት መስዋዕትነት በህግደፍ ቡድኖች ውሃ ተቸልሶበታል፡፡ የትጥቅ ትግሉ የተጀመረበትን 54ኛ ዓመት በነፃነት ሲያከብሩ ሰማዕታትን ለመዘከር መልካም አጋጣሚ እነደፈጠረላቸው ጠቁመዋል፡፡ በትግሉ ወቅት ከሁለት መቶ ሺ በላይ ኤርትራውያን የህይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን አቶ ግደይ ያስታውሳሉ፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም ህግደፍ የተሰኘው የጥቂቶች ቡድን የራሱን ጥቅም በማስቀደም የነፃነት ታጋዩን አመድ አፋሽ አድርጓል፡፡ ለሠላምና ዲሞክራሲ የሚያሰማው ጩኸት ሰሚ አልባ ሆኖ  በባርነት ውስጥ እየማቀቀ ነው፡፡

አፋኙ አገዛዝ ህዝቡን እያሰቃየው በመሆኑ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን እንዲረዳና ለመፍትሔ እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የህግደፍ ቡድን ህገ መንግስት እንዳይኖር በማድረግ ጥቂቶች ብቻ እንደፈለጉት እንዲፈነጩበት እያደረገ ነው፡፡ ጥያቄ ማቅረብና መብትን መጠየቅ ለእስርና እንግልት ከሚዳረግባት ኤርትራ የሚመጡ ስደተኞችን በወንድማዊ ፍቅር በመቀበል ለሚያስተናግዱት ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የኤርትራ ስደተኞች በወር በአማካይ ከ500 አይበልጥም ነበር፡፡ ስቃዩና እንግልቱ በመብዛቱ ግን የስደተኛው ቁጥር ከሁለት ሺ በላይ መድረሱንና አንዳንዴም አኃዙ ከፍ ብሎ አምስት ሺ እንደሚደርስ አቶ ግደይ ይናገራሉ፡፡ በጣም አሳዛኙ ጉዳይ ደግሞ ስደተኛው ከአገሩ ለመሰደድም ለአገዛዙ ወታደሮችና የደህንነት ሰዎች እስከ 100ሺ ናቅፋ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም ህዝቡ ቤቱንና ንብረቱን በመሸጥ ሀብቱን ለዘራፊዎች በማስረከብ ለመሰደድ ተገዷል፡፡

የሙዚቃ ኮንሰርቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን በአንድነት በማሰባሰብ ስለ አገራቸውና ህዝባቸው ነፃነት እንዲዘክሩ ረድቷል፡፡ በስደት ላይ ሆነው በነፃነት ኮንሰርቱን ለማካሄድ በመቻላቸውም በጣም ደስተኛ መሆናቸውን የኮንሰርቱ አስተባባሪ ወጣት ተክሌ መዝገበ ተናግሯል፡፡ አብዛኛዎቹ ስደተኞች ወጣቶች በመሆናቸው ለሠላምና ልማት የሚደረገውን ትግል ለማጠናከርና ስደተኛውን ለማነቃቃትና ለማበረታታት ኮንሰርቱ የላቀ ሚና እንዳለውም አክሏል፡፡ በኮንሰርቱ በርካታ የኤርትራ ስደተኞች የታደሙ ሲሆን ሙዚቃ፣ድራማ፣ግጥሞችና የተለያዩ መጣጥፎችም ቀርበዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞቹ ከስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውጭ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ትግላቸው ግቡን እንዲመታና ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ችግሩን ተረድቶ የሚጠበቅበትን እንዲወጣም ለሚመለከታቸው አካላት የማሳወቅ ሥራ እየሰራ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የጎረቤት አገራት ተሰደው የመጡ ከ700ሺ በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞች አቀባበል ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን ለማክበር ብቻ ሳይሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ፅህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ይናገራሉ፡፡

የኤርትራ መንግስት በዜጎቹ ላይ የሚያደርሰውን ከፍተኛ ግፍና መከራ በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኞችን በመቀበልም ተገቢውን ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ነው አቶ አሰግድ የጠቆሙት፡፡ በስደተኞች ፍላጎት ከካምፕ ውጭ እንዲኖሩ የማድረግ አሰራርን ከመተግበሩም በተጨማሪ የቀለምና የሙያ ትምህርትና ስልጠና እንዲያገኙም ተመቻችቷል፡፡ በዚህም ከሁለት ሺ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው እንዲማሩ ተደርጓል፡፡
የኤርትራ ችግር መፍትሄው በኤርትራውያን ጥረት የሚመጣ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ከጎናቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም የኤርትራውያንን ችግር እንዲያውቅና የመፍትሄው አካል እንዲሆን ለማስቻል መንግስት የበኩሉን ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኤርትራውያን ጩኸት ዛሬም አላቆመም፡፡ ጎላ ብሎ እየተደመጠ ያለው ድምፅ ሰሚ ብቻ ሳይሆን አድማጭ ጆሮ እየፈለገ ነው፡፡ የሰሚ ያለህ የሚለው ድምፅ የስደተኞቹ መንደር ቤተኛ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ጩኸቱ ቢበረታም ዛሬም ሰሚ አላገኘም፡፡ አሁንም ግን ስደተኞቹ ተስፋ ሰንቀው ነገ በምድራቸው ሠላም እንደሚሰፍን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው፡፡ ጎልተው እየወጡ ያሉት ሠላም ናፋቂ ድምፆችም ጊዜውን ይጠብቃሉ ሰሚ እንደሚያገኙ ይተማመናሉ፡፡