|
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2001/ዋኢማ/ "መድረክ" በሚል ስያሜ የተሰባሰቡት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊት እያደገ መጥቶ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለመገደብ እስከሞመከር መድረሱን እንደሚያወግዝ ኢዴፓ አስታወቀ። ድርጊቱ መሪዎቹ በሆነ አጋጣሚ የፖለቲካ ስልጣን በእጃቸው ቢገባ በህዝብ ላይ የሚኖረውን አደጋ ያመላከተ መሆኑንም ገልጿል።
የኢዴፓ ፕሬዚደንትና የፓርቲው አመራር አካላት ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በመድረክ ውስጥ የተሰባሰቡት የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች በህገ መንግስቱ ላይ ባላቸው ጭፍን ጥላቻና ዕድሜያቸውን ሙሉ ሲመኙት የነበረውን የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ሲሉ የሌሎችን ሃሳብን የመግለጽ መብት ለመገደብና ህዝቡን ለማወናበድ ሲጥሩ ይስተዋላሉ። ሰሞኑን በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ካለው የኔዘርላንድስ ልዑክ ጋር ለመነጋገር በኤምባሲው በተዘጋጀው ውይይት ላይ የመድረኩ መሪዎች የኢዴፓን ሃሳብን የመግለጽ መብት ለመገደብ መሞከራቸው ፀረ ዴሞክራሲ ባህሪያቸውን ገሃድ ያወጣ እንደሆነ አቶ ልደቱ አስታውቀዋል። መጪውን ምርጫ በሚመለከት በጋራ ለመወያየት ባለመፈለግ የራመዱት አቋም ኤምባሲውንና የልዑካን ቡድኑን እንዳሳዘነና በአገሪቱ ጉዳይ በጋራ ለመወያየት አለመፈለግ ለዴሞክራሲ ግንባታ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ እንደገለጹላቸውም ተናግረዋል። በመድረኩ ውስጥ ካሉት ስብስቦች ገሚሶቹ ሲገዳደሉ የኖሩና ሌሎቹ ደግሞ ከኢህአዴግ ጋር አብረው ሲሰሩ የቆዩና በፓርቲያቸው ውስጥ በተካሄደ ለውጥ ተሸናፊ ሆነው የወጡ አገራዊ ራዕይ የሌላቸው መሆናቸውን አመልክተው፤ ህገ መንግስቱንና ከነሱ የተለየ ሃሳብን ማክበር ውርደት መስሎ የሚታያቸው ፀረ ዴሞክራሲ ኃይሎች መሆናቸውን አጋልጠዋል። ኢዴፓ በፓርላማና በሌሎችም መድረኮች በመሳተፍ ለዴሞክራሲ ግንባታ እያደረገ ያለውን ጥረት ከሌሎች በተለየ ከኢህአዴግ የተሰጠው ችሮታ አስመስለው በማቅረብ ህዝቡን ለማወናበድ ሲጥሩ መቆየታቸውን አመልክተው፤ የፖለቲካ ስልጣን ሳይዙ ሃሳብን ለማፈን ያሳዩት ፍላጎት ማንነታቸውን ይፋ ያወጣ ድርጊት እንደሆነ ጠቁመዋል። እነዚህ ኃይሎች በመጥፎ የታሪክ አጋጣሚ የፖለቲካ ስልጣን በእጃቸው ቢገባ በአገሪቱ ሊከሰት የሚችለውን አምባገነናዊና አፋኝ ስርዓት ከወዲሁ መገመት እንደሚቻል ገልጸው፤ በህይወት ዘመናቸው የሰሩትን ስህተት በሌላ ስህተት የሚያርሙና ፖለቲካን መገዳደያና መበቃቀያ ለማድረግ የወሰኑ መሆናቸውን አመልክተዋል። የመድረክ ስብስብ መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በተመሳሳይ የአፈና ተግባር ላይ የነበሩና ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚለዩበት አማራጭ አጀንዳ የሌላቸው በመሆናቸው ግንባር ፈጥረው አፈና ለመፈፀም ቢጣጣሩ የሚያስደንቅ ጉዳይ አለመሆኑንም የኢዴፓ አመራር አካላት አስታውቀዋል። ኢዴፓ ለህገመንግስቱና በህገ መንግስቱ ለተቋቋሙ ተቋማት እንዲሁም በህግ ለተቋቋሙ የፖለቲካ ኃይሎች አስተሳሰብ ክብር የሚሰጥ ፓርቲ መሆኑን ጠቁመው፤ ፀረ ዴሞክራሲ ኃይሎች ህዝብን በማደናገርና የጥላቻ ፖለቲካን በመስበክ ለስልጣን የሚበቁበት ዕድል እንደማይኖር እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል። ህዝቡም የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎችን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በመመዘን ድጋፉን መስጠትና በስሙ እየማሉ የአፈና ገመድ ከሚቋጥሩለት አጭበርባሪዎች አገሩንና ዴሞክራሲውን እንዲጠብቅ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |