ለዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12 /2005 (ዋኢማ) - የድንበር ክለላ ስራ ለተጠናቀቀላቸው ሰባት የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ኢንፎርሜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይረክተር አቶ መብራቱ ሃይሉ ለዋልታ እንደገለጹት የህግ ማዕቀፉ የተዘጀው ለጋምቤላ፣ ባሌ ተራሮች፣ ቃፍታ - ሽራሮ፣ ስንቅሌ፣ ባቢሌ ዝሆኖችና ስንቀሌ ቆርኬዎች የዱር እንስሳት ጥበቃ ስፍራዎች ነው።

የሰባቱ ስፍራዎች ድንበር ክለላ ሥራው የተከናወነው በ2004 በጀት ዓመት እንደሆኑ የገለጹት አቶ መብራቱ የአቢያታ-ሻላ ሐይቆች ብሄራዊ ፓርክ ዳር ድንበር ክለላም ጥናቱ ተጠናቆ ቀጣይ ስራዎችን ለማካሄድ ዝግጅት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በገራይሌ፣ አላጥሽ፣ አብጃታና ኦሞ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ውስጥ ለሚገኙ 6 መቶ 84 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና እንደተካሄደም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

እንደ አቶ መብራቱ ገለጻ በያንጉዲራሳ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታም 35 ኪሎ ሜትር አዲስ ጥርጊያ መንገድ ተሰርቷል።