በሻእቢያ መንግስት አራማጅነት በሚካሄደው ሽብር ፈጠራ የታገቱ ኢትዮጵያውያን መለቀቅን በማስመልከት ከማስታወቂያ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ

የኤርትራ መንግስት ከጊዜ ወደጊዜ እየገፋበት በሚገኘው የአሸባሪነት የትግል ስልት የእገታ አደጋ ደርሶባቸው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከ52 ቀን አሰቃቂ አፈና በኋላ በትላንትናው እለት ተለቀው ወደሀገራቸው መጥተዋል። ታጋቾቹ ኢትዮጵያውያን በኤርትራ መንግሥት በተላኩ አሸባሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት የካቲት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ሲሆን ከነሱ ጋር አብረው የተያዙት አውሮፓውያን ከ12 ቀን እገታ በኋላ ሲለቀቁ ኢትዮጵያውያኑ ግን ለተጨማሪ 40 ቀናት በአስከፊ ሁኔታ እንደታገቱ ቆይተዋል።

የሻእቢያ መንግሥት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ቢሆንም በግልፅ የአሸባሪነት ተግባር ላይ ተሰማርቶ አካባቢያችንን በማተራመስ ላይ እንደሚገኝ ከማንም የተሰወረ ካለመሆኑም በላይ አምስት አውሮፖውያንን ጨምሮ በአገራቸው ውስጥ በሰላማዊ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ስምንት ኢትዮጵያውያንን ድንበር ተሻግሮ መጥለፉ የዚህ አሸባሪ ተግባሩ ተጨባጭ ማሳያ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና አለም አቀፍ ማህበረሰብ ይህን የመሰለው አሸባሪ ተግባር በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለዛውም የተመድ አባል አገር በሆነ መንግስት ሲፈፀም እየተመለከተ ነገሩን በቸልታ ማለፍ መላውን ሰላም ወዳድ ማህበረሰብ ያስጨነቀና ያሳሰበ ጉዳይ ሆኖ ከርሟል። አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም አውሮፓውያኑ እስኪፈቱ ድረስ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትሩት ሲሰጡ ቆይታው የአውሮፓውያንኑ መፈታት እንደተረጋገጠ ነገሩን ችላ ማለታቸው እጅግ አስተዛዛቢ ክስተት ሆኖ ቆይታል።

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ የእገታው አሸባሪ ድራማ ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያንና አውሮፓውያን ያለአንዳች ልዩነት ሊለቀቁ እንደሚገባ ከመወትወታቸውም በላይ የኤርትራ መንግሥት ጉዳዩን በሃላፊነት እንደሚሸከም በጥብቅ አሳስበው ያለማቋረጥ ታግለዋል። ለዚህ የህዝባችን ታላቅ ትግል ምስጋና ይግባውና ከባልደረቦቻቸው ተነጥለው ለተጨማሪ 40 ቀናት የታገቱት ኢትዮጵውያን በትላንትናው እለት ተለቀው ወደሀገራቸው ለመግባት ችለዋል።

ታጋቾቹ ከተለቀቁ በኋላ ለማረጋገጥ እንደተቻለው የኤርትራ መንግሥት እንደለመደው ዜጐቻችንን በከፊል አቆይቶ በከፊል ለመልቀቅ አቅዶ የነበረ ቢሆንም አስቀድሞ እንዲለቀቁ የፈቀደላቸው የአፋር ብሄረሰብ ተወላጅ ዜጐቻቸውን ሌሎች ኢትዮጵያውያን ካልተለቀቁ በስተቀር አንሄድም በማለት ባካሄዱት ትግል ሁሉም ዜጐቻችን እንዲለቀቁ ለማድረግ አኩሪ ትግል አካሂደዋል። የኤርትራ መንግሥት መላ የአገራችን ህዝቦች ባደረጉት ትግልና እየተፈጠረ በሄደው ተጽእኖ ምክንያት ዜጐቻችንን ለመልቀቅ መገደዱ የትግላችን ውጤት ነው።

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በዚህ አጋጣሚ የአፍሪካ ቀንድን በአሸባሪ የትግል ስልት ለማተራመስ ቆርጦ የተነሳውን የኤርትራ መንግሥት መላው የአለም ህዝብ እንዲያወግዘው ጥሪያቸውን ያቀርባሉ። በተለይ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአፀያፊው የሽብርተኝነት ተግባር ውስጥ የተዘፈቀውንና ለስሙ የተባበሩት መንግሥስታት ድርጅት አባል የሆነውን የኤርትራ መንግሥት ዛሬም ካላባራው የአሸባሪነት ተግባሩ እንዲቆጠብ አስፈላጊውንና ከሱ የሚጠበቀውን እርምጃ እንዲወሰድ ኢትዮጵያ ጥሪዋን ታቀርባለች።

(ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚያዝያ 15 ቀን 1999 ዓ.)