ኢትዮጵያ ፀረ ሽብርተኝነት ትግሏን አጠናክራ ትቀጥላለች

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነት እንደአሁኑ የመላው ዓለም ስጋት ከመሆኑ አመታት አስቀድሞ የጥቃቱ ሰለባ እንደነበረች ይታወቃል፡፡ በነዚህ ጊዜያት በተለያዩ ከተሞች ውስጥ አሸባሪዎች በዜጐቻቸው ህይወት ላይ የፈፀሙት የሞት አደጋና በንብረት ላይ ያስከተሉት ውድመት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

አገራችን አስቀድማ የአሸባሪዎች የጥቃት ሰለባ ሆና ብትቆይም ውሎ አድሮ አደጋው የመላው አለም ስጋት እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ አለም አቀፍ ማህበረሰብ የተቀናጀ የጸረ ሽብርተኝነት ትግል ማካሄድ ጀመረ፡፡ ይህም ለኢትዮጵያ አንድ ትልቅ ጠቃሚ እርምጃ ነበር፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በፀረ ሽብርተኝነት ትግሎ በግንባር ቀደምነት የመሰለፏ ጉዳይ አጠያያቂ አልነበረም፡፡

ሰርገው በመግባት ጥፋት ለማድረስ የሚሞክሩትን የአሸባሪ ቡድን አባላት በፖሊስና ፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም በህዝቡ ትብብር ዓላማቸውን ከማሳካታቸው በፊት በቁጥጥር ሥራ የማዋልና ህግ በሚፈቅደው መሠረት ፍርዳቸውን እንዲያገኙ የማድረጉ ሁኔታ ሳያቋርጥ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም አሸባሪዎችም ሆኑ አዝማቻቸው የኤርትራ መንግሥት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ አልቻሉም፡፡

የአሸባሪዎች ጥቃት አለማአቀፋዊ መልክ መያዙን ተከትሎም ቢሆን ከድህነትና ከኋላቀርነት ጋር መፋለምን የመጀመሪያዉና የመጨረሻው አጀንዳዋ በአደረገችው በኢትዮጵያ ላይ አሸባሪዎች የሚፈጽሙት ጥቃት አልተገታም፡፡ ይልቁን ወንድም የሆነውን የኤርትራን ሕዝብ የማስተዳደር ኃላፊነት የተረከበው የሻእቢያ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ የሽብር ጥቃት የመፈጸምና የማስፈጸም ዋንኛ ተልእኮ ይዞ መንቀሳቀስ ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚሁ መሠረትም በርካታ አሸባሪዎችን በኤርትራና በሌሎች አካባቢዎች ጭምር እያሰለጠነ ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት የሽብር ጥቃት ከመሰንዘር አልታቀበም፡፡

የኤርትራ መንግሥት የቅርብ ጊዜ የሽብር ዘመቻ ከኤርትራ እስከ ሞቃዲሾ ድረስ የተዘረጋ መሆኑ ገሀድ ወጥቷል፡፡ በሶማሊያ የተቋቋመውንና አለምአቀፍ እውቅና ያለውን የሽግግር መንግሥት በማፍረስ ኢትዮጵያን ለማናጋት ይጠቅመኛል ያላቸውን ጸረ ሰላም ኃይሎች ለማደራጀትና በመላው አፍሪካ ቀንድ ትርምስ ለመፍጠር ባለ በሌለ አቅሙ ጥሯል፡፡ ይህም አለመሳካቱን ሲረዳ በተለያዩ ሌሎች መንገዶች የጥፋት ተልእኮውን ለማሳካት ከመንቀሳቀስ አልተቆጠበም፡፡

ከኤርትራ እስከ ሶማሊያ ሞቃዲሾ የተዘረጋውን የሻእቢያ መንግሥት የሽብር መረብ ለማክሸፍ የመከላከያ ሠራዊታችን ከሱማሊያ የሽግግር መንግሥት ኃይሎች ጋር በመሆን ባካሄዱት ፍልሚያ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው የአፍሪካ ቀንድ ለማተራመስ ሶማሊያን ማእከል አድርጐ አንዳች እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችል ማሳየት የተቻለበት ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዚሁ ዘመቻም በርካታ አሸባሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል የተቻለ ሲሆን አብዛኞቹ ከተለቀቁ በኋላ በጥፋት ወንጀል መጠየቅ ያለባቸው ከበርካታ አገሮች የተውጣጡ አሸባሪዎች የአገራችን ህግ በሚፈቅደው መሰረት ለፍርድ ቀርበዋል፡፡ እነዚህ ተጠርጣሪ አሸባሪዎች አያያዝም ሆነ በፍርድ ሂደት የአገሪቱ ህገ መንግሥታዋ አለማአቀፍ ስምምነቶች በሚደነግጉት መሠረት ብቻ እየተካሄደ ያለ ነው፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ እያለ በአገራችን ውስጥ ድብቅ የማሰቃያ እስር ቤቶች እንዳሉና የእስረኞቹም አያያዝ ሰብአዊ መብታቸውን በሚጥስ መልኩ እንደሆነ ተደርጐ የሚቀርበው ዘገባ መሠረተ ቢስ መሆኑን ተጠርጣሪ አሸባሪዎች ራሳቸው አረጋግጠዋል፡፡ መንግሥት የሀገሪቱን ህገ መንግሥትና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በማክበር ተጠርጣሪዎቹ በፍርድ የሚዳኙበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ በዚህም ሂደቱ የመጨረሻውን ብይን የሚያገኝ ይሆናል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከድህነት ለመላቀቅ ሰፊ ርብርብ አካሂደን የተሳካ ውጤት ማስመዝገብ በጀመርንበት ሁኔታ በአገራችን ላይ የሚቃጣን የትኛውንም አይነት የሽብር ጥቃት ለመከላከል የተጀመረውና በመካሄድ ላይ ያለው ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ለዚህም መላው ህዝባችን ከፖሊስና ፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር በአገራችን ላይ ሊፈፀም የሚቃጣን ማንኛውንም ሙከራ ለማምከን እንደከአሁን ቀደሙ ሁሉ ነቅቶ መጠበቅና መመከት እንዳለበት መንግሥት በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ ይፈልጋል፡፡

(ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚያዝያ 5 ቀን 1999 ዓ.)

Back