|
ግንቦት 08, 2000 ዓ.ም
የአንዲት
ሀገር ዋናው ሀብት ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ በሀገሩ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትንና
አመለካከትን ይዞ ልዩነቱን እያጠበበና እርስ በርስ እየተቻቻለ እጅና ጓንት ሆኖ ከሰራ
ሀገር የማትለማበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ሀገሪቱን
ከድህነት ማጥ ለማላቀቅ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ፖሊሲ ነድፎ በመተግበር
ላይ ይገኛል፡፡ የገጠር እርሻ ልማትን ማዕከል ያደረገው ይሄው ፖሊሲ ውጤታማነቱ በተግባር
እየታየ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅና
ድንቅ ክስተት በያዝነው ዘመን እውን ሁኗል፡፡ የገበሬ የሚሊኒየሮች መፈጠር፡፡ የኢትዮጵያ
ገበሬ ከእጅ ወዳፍ ያለፈ ምርት አምርቶ የሚያውቅበት ወቅት በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ
አይታወቅም ነበር፡፡ ይሄ ግን አሁን እውን ሆነ፡፡ ይሄ ውጤት ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር
የተጣጣመ ፖሊሲ በመነደፉ ምክንያት የመጣ ነው፡፡ ለውጡ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡
በሀገሪቱ ያለው የመብራት፣ የስልክ፣
የመንገድ፣ የትምህርትና የጤና ሽፋንና ጥራት በእጅጉ እያደገና ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻለ
መምጣቱ ያደባባይ ምስጢር ነው፡፡ “ዓይን እያላቸው የማያዩ፤ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ”
ካልሆነ በስተቀር ኢህአዴግ በዚች ሀገር መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱንና ህዝብን ሊጠቅም
የሚችል አጀንዳ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
ይሄንን ኢትዮጵያ እያሳየች ያለችውን
ሁለንተናዊ ለውጥ እውን እንዲሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስተዋጽኦ ወሳኝ አለው፡፡
የአሁኗ ኢትዮጵያ ከትናትናዋ ጋር ስትነጻጸር ምን ትመስላለች? በውጭ ሀገር የሚኖሩ
ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መጥተው በሀገራቸው ልማት እንዲሳተፉ የሚደረገው ጥረትስ ምን
ይመስላል? የሚሉና ሌሎችም ተዛማጅ ጥያቄዎችን አንስተን ከ20 ዓመታት የስደት ኖሮ በኋላ
ሀገራቸውን ለማየት ከመጡት ከኢንጂኒየር መኮነንን ካሳ ጋር ቃለምልልስ አድርገናል
እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ዋልታ፡-
ኢንጂኒየር መኮንን ካሳ በአሜሪካ የኢህአዴግ ደጋፊ ፎረም ሊቀመንበር ጥሪያችን አክብረው
ለዚህ ቃለመጠይቅ በመምጣትዎ በጣም እናመሰግናለን፡፡
ኢንጂኒየር መኮንን፡-
እኔም ይሄንን ዕድል ስለሰጠኝ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልን አመሰግናለሁ፡፡
ዋልታ፡-
ከህይወት ታሪክዎ እንጀምርና ወደ ውጭ ሀገር ከመሄድዎ በፊትና ከሄዱ በኋላ ያለውን ሁኔታ
አጠር አድርገው ቢገልፁልን?
ኢንጂኒየር መኮነን፡-
የተወለድኩትና ያደግኩት ጎንደር ከተማ ነው፡፡ የ19 ዓመት ልጅ እያለሁ ሰኔ 25 ቀን
1976 ዓ.ም ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ሆኘ በአርማጭሆ አድርገን ለአስራ አምስት ቀናት
በእግራችን ተጉዘን ሱዳን ገባን፡፡ ከዚያም የስደተኞች መቀበያ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ
ከተቀመጥን በኋላ ወደ ገዳርፍ ሄጀ የቤት ሰራተኛ ሆኘ ሳገለግል ቆየሁ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ
በኋላም ወደ ካርቱም ገባሁ፡፡ ከዚያም በ1980 ዓ.ም ዕድል አግኝቸ ወደ አሜሪካ ከተማ
ሲያትል ለመሄድ በቃሁ፡፡ እዚያው የታክሲ አሽከርካሪ ሆኘ እየሰራሁ ትምህርቴን በመከታተል
ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዋሽንግተን በተባለው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በሜካኒካል እንጂነሪንግ
የመጀመሪያ ድገሪ በ1987 አገኘሁ፡፡ በመቀጠልም በአሜሪካ ታዋቂ በሆኑ የተለያዩ መስሪያ
ቤቶችና ኩባንያዎች እየተዘዋወርኩ ሰራሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሬድመንት ዋሽንግተን አካባቢ
በሚገኝ ሶፍትዌር የሚሰራ ትልቅ ካምፓኒ በሲኒየር ማናጄር የሀላፊነት ቦታ ላይ እገኛለሁ፡፡
ዋልታ፡-
መጀመሪያ ከመሄድዎ በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያና በውጭ አገር ለ20 አመታት ቆይተው
ሲመለሱ ያይዋትን ኢትዮጵያ በንጽጽር ቢያስረዱን?
ኢንጂኒየር መኮንን፡-
በ1970ዎቹ ኢትዮጵያን ሳውቃት በጣም በጣም ግፍ የበዛበት፣ በደል የነገሰባትና ድህነት
የሚፈነጭባት ሀገር ነበረች፡፡ ባደግኩበት በጎንደር ከተማ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት
ስላላቸው ብቻ በርካታ ወጣቶች ከናቶቻቸው ጉያ እየተነጠቁ ቀይሽብር የሚረሸኑበት ዘመን
ነበር፡፡ በአንድ ምሽት 10 የማውቃቸው ልጆች ተገድለው ማደራቸውን አልረሳውም፡፡
ለመገደላቸው ምክንያት የሆነው ደግሞ ቁጭ ብለው ጠላ እየጠጡ መዝሙር ዘመሩ የሚል ነበር፡፡
በወቅቱ የነበረው መንግስት የፊትና የኃላ መስኮቶቹ የተከፍቱ ላንድሮቨር መኪና ላይ
መትረየስ በመደገን አላፊ አግዳሚውን የሚገድልበት ጊዜ ነበረ፡፡ በኢኮኖሚው ረገድም ሲታይ
ስራ አጥነትና ድህነት የበዛባት፤ የትምህርት ዕድል የጠበበባት ሀገር ነበረች፡፡
ኢትዮጵያ፡፡ እኔና ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያንም ሀገራችንን ጥለን የተሰደድነው
ሀገራችንን ጠልተን ሳይሆን በነበረው አፋኝ ስርዓት ተማረን ነበር፡፡
አሁን መጥቸ ያለውን ሁኔታ ሳይ ግን በጣም
የሚገርም ነው፡፡ ያደግኩባት ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ተለውጣ፣ ፓርላማ ተቋቁሞ፣ ተቃዋሚ
የፖለቲካ ድርጅቶች መብታቸው ተጠብቆ፣ ከመንግስት የተለየ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች
ሀሳባቸውን በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣ የሚገለገጹበትና በፓርላማ የሚናገሩበት ሁኔታ
ማየቴ በጣም አስደስቶኛል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሌሎች የገጠር ከተማዎች
ተዘዋውሬ እንዳየሁት ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ በህዝቡ ላይ የሚነበበው የአስተሳሰብ
ለውጥና ለሥራ ታጥቆ የመነሳት ሁኔታ አይቸ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ የመንገድ ግንባታውም
ተአምር ነው፡፡ ከዋና ከተማ ወደ ተለያዩ ክፍለ ሀገሮች የሚሄዱት ዋና ዋና መንገዶች
በአስፋልት ሆነው ህዝቡ በፈለገው ጊዜና ሰዓት በፈለገው መኪና የሚሄድበት በፈለገው ሰዓት
የሚደርስበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በየክልል የውስጥ መንገዶችም በከፍተኛ ደረጃ እየተሰሩ
ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የጤና ጣቢያዎች፣ ክሊንኮችና ትምህርት ቤቶች በየሰፈሩ
ተሰርተዋል፡፡
ድሮ እኛ በኖርንባት ኢትዮጵያ ወጣቱ ለመማር
የነበረው ዕድል ዝቅተኛ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙ ዩኒቨርስቲዎች የመንግስት ብቻ
ሳይሆን የግልም ዩኒቨርስቲዎች ተቋቁመው አይቻለሁ፡፡ በመንግስት ዩኒቨርስቲ መግባት
ያልቻሉ በግል መማር የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገራችንን
ገፅታ ብቻ ሳይሆን የህዝቦቿን የኑሮ ሁኔታ መቀየር የሚቻልበት ደረጃ ላይ መሆኗን
በመገንዘቤ በጣም ተደስቻለሁ፡፡
ዋልታ፡-
በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ባለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ለውጥ ላይ በአሜሪካ
የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያላቸው ግንዛቤ ምን ይመስላል?
ኢንጂነየር መኮንን፡-
ወደ አሜሪካ ከሄድኩ 20 ዓመት ሆኖኛል፡፡ በተለያዩ የአሜሪካን ከተሞች ለስራ የመሄድ
ዕድል ስላጋጠመኝ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ለማነጋገር ችያለሁ፡፡ በርግጥ በርከት ያለው
ኢትዮጵያዊ ሀገር ውስጥ የሚደረገውን ነገር ጥሩ እንደሆነ ግንዛቤ አላቸው፡፡ እንዳጋጣሚ
ሆኖ ግን ነገሮች ሁሉ በጨለምተኝነት እንዲታዩ የሚያደርጉ ጥላቻ ላይ ያጠነጠነ ወሬ
የሚነዙ ሰዎችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ልማትና የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሌለና
ሁሉም ነገር ለይምሰል የሚወራ በማስመሰል የሚናገሩ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የዜና ማሰራጫ
ማዕከላትን ተቆጣጥረዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በኛ የፖለቲካ ባህል የሚቃወሙት ፓርቲ
የሚሰራውን ሁሉ ማጣጣል አስፈላጊም ሲሆን መወንጀል የተለመደ ስለሆነ እንጂ በኢትዮጵያ
ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም እንደዚህ ዓይነት የማጣጣል ፕሮፖጋንዳ
የሚካሄደው፡፡ ሆኖም ግን በርካታ ኢትዮጵያውያን በቂ ግንዛቤ አላቸው የሚል እምነት
አለኝ፡፡
ዋልታ፡-
እንደነዚህ ዓይነት ችግሮችን ለማስወገድ እንዲቻል ግንዛቤን ማስረፅም ሆነ ተጨባጩን ነገር
ማሳየት የሚችል አካል በአካባቢው የለም?
ኢንጂኒየር መኮንን ፡ -
በርግጥ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አሉ፡፡ ግን በዚያ አካባቢ ሁሉም ነገር በፖለቲካ መነፀር
ስለሚታይ እነሱም ቢሆኑ የሚያደርጉት ጥረት የተፈለገውን ያህል ስኬታማ አልሆነም፡፡ እኛም
የኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅትን ለመደገፍ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ሌሎችም እንደኛ ዓይነት
ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው አሉ፡፡ እኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘የኢህአዴግ ደጋፊ ድርጅት’
አቋቁመናል፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆኘ እየሰራሁ ያለሁትም እኔ ነኝ፡፡ ዋና ዓላማው
ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለውን አዎንታዊ እንቅስቃሴ ውጭ ሀገር ለሚኖሩ
ኢትዮጵያውያን የማስተዋወቅ ሥራ መስራት ነው፡፡ በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ዜጎች የኢህአዴግን
እንቅስቃሴ ከማስተዋወቅ ባሻገር በፖለቲካው ዙሪያ የበሰለና በውይይት ችግሮችን ለመፍታት
የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ነው፡፡
ይሄን ደግሞ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት
የኢህአዴግ አመራሮችን በመጋበዝ በተለያዩ የአሜሪካም ሆነ የካናዳ ክፍለ ከተማዎች
በመዘዋወርና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ኢህአዴግ የሚሰራውን ሥራና ያለውን ፖሊሲ
የሚያስተዋውቅበት አጋጣሚ መፍጠር ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጋር ባላቸው
የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ከሚያደርጉት ሀገርን የሚጎዳ ለመቋቋም በዩናይትድ ስቴትስ
ኮንግርስ ሆነ በሰኔት ጥናቶችን እያጠናን የሚናቀርብበት ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ በተጨማሪም
በሀገሪቱ የአቅም ግንባታ ስራ ላይ ያሉን ባለሙያዎች ሁሉ የሚሳተፉበትን መንገድ መቀየስ
ነው፡፡
ዋልታ ፡-
አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች አብዛኛውን ጊዜ ወደ አሜሪካ ሲሄዱ ይስተዋላሉ፡፡ የሚሄዱት
ለምንድን ነው? በአሜሪካ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ያላቸው ተቀባይነትስ ምን
ይመስላል?
ኢንጂኒየር መኮንን፡-
እነዚህ ሰዎች የተቃዋሚ ዋሻ ወይም ጎራ አሜሪካን ሀገር ውስጥ ያለ ይመስላቸዋል፡፡
የውጭ ሀገሩ የተቃዋሚ ጎራ የተቃዋሚ ብቻ መፈንጫ መሆን የለበትም፡፡ ኢህአዴግን
እንደግፋለን የምንል ሰዎችም መንቀሳቀስ አለብን በሚል ነው እኛም የተደራጀነው፡፡ እነዚህ
ተቃዋሚ ነን ባዮች እዚያ እየሄዱ በውሸት፣ በውንዥብርና በማጭበርበር የሚያቀርቡትን ነገር
ህዝቡ ጥያቄ ውስጥ እንዲያስገባው ማድረግና ውሸት መንዣ መድርክ ማሳጣት ነው፡፡ የፖለቲካ
አካሄዳቸውን የሚወስኑት እነሱ ቢሆኑም በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋፅኦ
አደርጋለሁ ብሎ የተነሳ ማንኛውም አመራር ከህዝቡ ጋር ሆኖና ህዝቡ ይደርስበታል የሚለውን
ችግርና ግፍ አብሮ በመካፈል ለውጥ ለማምጣት መታገል እንጂ ውጭ ሆኖ በሪሞት ኮንተሮል
በመቆጣጠር ወይም የውጭ መንግሰታት ዘንድ እየሄዱ በመማጸን በመንግስት ላይ ችግር
እፈጥራለሁ ብሎ መሄድ በጣም ያሳዝናል፡፡
ዋልታ፡-
በአሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ
ያላቸው ተቀባይነትስ ምን ይመስላል?
ኢንጂኒየር መኮነን፡-
ድህረ ምርጫ 97 ትልቅ ተቀባይነት ነበራቸው ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በተፈጠሩ አንዳንድ
ችግሮች ላይ በውጭ የሚኖረው ህዝብ በቂ ግንዛቤ ስላልነበረው ነበር፡፡ እንደ አርበኛ
ይመለከታቸው ነበር፡፡ በመካከላቸው ያለው ልዩነትና ችግር እየጎላ ሲመጣና ያሰቡትን ግብ
የማድረስ ፅናትና አቋም ያልነበራቸው በመሆኑ ያው በስልጣን ሽኩቻ ላይ ባጠነጠነ ሁኔታ
ላይ እየተጣሉ ከሶስት ከአራት እየተከፋፋሉ እርስበርሳቸው እየተወነጃጀሉ ባንዳ፣ ሌባ፣
ሆዳም መባባል ሲጀምሩ ሲያይ ግን ሲደግፋቸው የነበረው ኮሙዩኒቲ ማንነታቸውን አውቆ
አግልሏቸዋል፡፡ ህዝቡ የተቃዋሚውን ማንነት የተረዳበትና የኢህአዴግን ማንነት ደግሞ
ለመረዳት ዕድል ያገኘበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ዋልታ፡-
ተቃዋሚዎች በአሜሪካ ካለው የኢትዮጵያ
ከሙዩኒቲ ጋር ሲገናኙ በዋናነት የሚያነሱት ችግር ምንድን ነው?
ኢንጂኒየር መኮንን፡-
አንድ ዋና ችግር ብለው የሚያነሱት የመብት አለመከበርና የዴሞክራሲ ሂደት አለመኖር ሲሆን
ሌላው ደግሞ ፌዴራላዊ አስተዳደር በህዝቦች ላይ ችግር እንደፈጠረና ሀገሪቱ አደጋ ላይ ነች
የሚል ነው። የሚያሳዝነው ግን ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም እያሉ እነሱ ራሳቸው በውጭ
ሀገር የሚያደርጉት ነገር ከዴሞክራሲ በጣም የራቀ ነው፡፡ በማንኛውም ሀገር የዴሞክራሲ
ስርዓት ወይም መልካም አስተዳደር በጥቂት ዓመታት አይገነባም፡፡ በሂደት የሚከሰቱ አንዳንድ
ችግሮች ቢኖሩም ጊዜው እየፈታቸው ህዝቡም በዴሞክራሲ ባህል እየታነፀ ሲሄድ መፍትሔ እያገኙ
ሁኔታዎች ሁሉ እየተስተካከሉ መሄዳቸው አይቀርም፡፡
ተቃዋሚዎች የሚያቀርቡት በኢትዮጵያ
ብሔር/ብሔረሰቦች መካከል ሽኩቻ እንደተፈጠረ፣ ኢትዮጵያ ከመፈራረስ ከመሰባበር
እንደደረሰች፣ ፈረንጆቹ ኢለቨንዝ አወር የሚሉት አይነት ደረጃ ላይ እንደተደረሰ አድርገው
ነው፡፡ እኔ እንዳያሁት ከሆነ ኢትዮጵያውያኖች ቀደም ሲል በነበሩት ስርዓቶች ማንነታቸው
ሳይታወቅ ክብራቸው እየተነካ በባህላቸው እንዳይኮሩና በቋንቋቸው እንዳይናገሩ ሲደረጉ
የነበሩ ሲሆን አሁን በቋንቋቸው መናገር፣ ባህላቸውን ማንፀባረቅና ከሌላው ጋር በእኩል
ደረጃ እንዲታዩ መደረጉን ጥሩ ሆኖ ስላገኙት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን
ፈጥረው ነው ያየሁት፡፡
ዋልታ፡-
ኢትዮጵያ ለተከታታይ አምስት ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧ በመንግስት ተወካዮች ብቻ
ሳይሆን እንደ ዓለም ባንክና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በመሳሰሉ ተቋማትም
ተረጋግጧል፡፡ ለዚህ ዕድገት በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ቀላል እንዳልሆነ
መገመት ይቻላል፡፡ ይህንን መልካም ጅማሮ ለማጠናከር ሀገራቸውን እንዲያግዙና መዋዕለ
ንዋያቸውን በሀገር ኢንቬስት እንዲያደርጉ የሚደረግ ጥረት ካለ ቢገልፁልን?
ኢንጂኒየር መኮንን፡-
ከኢትዮጵያ በሚመጡ ባለስልጣናት በኩል በሀገሪቱ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለህዝቡ
እንዲያቀርቡ ማቀናጀት፣ ማስታወቂያዎችን መለጠፍ፣ ፅሁፎችን መፃፍና ያለውን ለውጥ ማሳየት
የሚያስችል ስራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው። አሁን ሀገርን ጠቅሞ ራስን የመጥቀም
አጋጣሚው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ እስካሁን ያለው ተሳትፎ ጥሩ ነው ግን የበለጠ ማድረግ
ይቻላል፡፡ እኛ የሚጠበቅብንን ሁሉ እንሰራለን፡፡
ዋልታ፡-
ኢንጂኒየር መኮንን ካሳ ላደረጉልን ትብብር በጣም እያመሰገን በመጨረሻ ማስተላለፍ
የሚፈልጉት መልእክት ካለ?
ኢንጂኒየር መኮንን፡-
የኢህአዴግ ደጋፊ ድርጅት ራዕይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡
አንድ ሰው የተለየ የፖለቲካ አመለካከት በመያዙ እንደጠላትነት መታየቱ የለበትም፡፡
ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በሚያስማሙን ዓበይት ነገሮች ላይ አብሮ ለመስራት የሚያስችል
ሁኔታ ለመፍጠር ነው ጥረታችን፡፡ ድሮ እኛም አሁን በተቃዋሚ ጎራ ከተሰለፉት ጋር አብረን
የተሰለፍንበት ወቅት ነበር፡፡ ግን ከእነሱ የተለየንበት ዋናው ምክንያት ጊዜያችንን
እየወሰድን አንዳንድ ነገሮችን እየገመገምን አያየንና በዚህ በዚህ ኢህአዴግ ጥሩ ስራዎችን
ሰርቷል የምንልበት ደረጃ ላይ መድረሳችን ነው፡፡አንዳንዶቹ ግን በጭፍን ጥላቻ ላይ
የተመሰረተ ተቃውሞ ነው የያዙት፡፡ ይሄ ደግሞ ሀገርን አይጠጨቅምም፡፡ በፖለቲካ አመለካከት
መለያየት ማለት በጠላትነት መተያየት ማለት አይደለም። ኢህአዴግ እየሰራ ያለው ሀገርን
ይጠቅማል ብለው የሚያስቡ ካሉ አሁን መድረክ ተፈጥሯል ከኛ ጋር ሆነው መስራት ይችላሉ። |