የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ውጤት እያሳየ ነው

አዲስ አበባ ጥር 14/2000 በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በተደጋጋሚ ለሚከሰተው የምግብ እጥረትና የረሃብ ተጋላጭነት ችግር ዘለቄታዊ መፍትሄ በመስጠት ረገድ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ መሆኑ መረጃው ያመላክታል።

ከማስታወቂያ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በዚህ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ማዕቀፍ ሥር የሴፍትኔት፣ የሰፈራና የሌሎች የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ያካተተ ሲሆን የፕሮግራሙ ግብም ከ8.29 እስከ 15 ሚሊዮን የሚደርሱ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው የቤተሰብ አባላት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ መሆኑን ያሳያል።

በመሆኑም እ.ኤ.አ.  በ2005 በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሐረሪ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እንዲሁም በድሬዳዋ ጊዜያዊ አስተዳደር በሚገኙ 192 ወረዳዎች በተጀመረው የሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉና ስር ለሰደደ ለምግብ ዋስትና መታጣት ችግር የተጋለጡ 5 ሚሊዮን 664 ሺህ 471 ህዝቦች የፕሮግራም ተጠቃሚ ሲሆኑ በዚሁ ዓመት ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ የተመደበው 811 ሚሊዮን 325 ሺ 652 ብር እና 224 ሺ 140 ነጥብ 91 ሜትሪክ ቶን ምግብ ሥራ ላይ መዋሉ መረጃው ያመላክታል።

እ.ኤ.አ. በ2006ም በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮምያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች፣ በሐረሪ እና በአፋር ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ በሚገኙ 234 ወረዳዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጦ የነበረውን 7 ሚሊዮን 192 ሺ 72 ህዝብ ለመታደግ በተካሄደው ቀጣይ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የተመደበው 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እና 385 ሺ 318 ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል ሥራ ላይ መዋሉን መረጃው ጠቁሟል።

የምግብ ዋስትና ፕሮግራም አካል በሆነው የሰፈራ ፕሮግራምም ፈቃደኛ የሆኑ 440 ሺ አባወራዎችን ለም በሆኑ አካባቢዎች በማስፈር የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ በተያዘው እቅድ መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2002/3 – 2005/6 ድረስ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሚገኙ 64 ወረዳዎች በተቋቋሙ 198 የሰፈራ ጣቢያዎች 320 ሺ 403 ወንዶች እና 660 ሺ 273 ሴቶች በድምሩ 980ሺ 676 ህዝብ መስፈሩን ያሳያል።

እንዲሁም እ.ኤ.አ. ከ2002/03 – 2004/5 ከሰፈሩት 149ሺ 631 የቤተሰብ ኃላፊዎች ውስጥ 132 ሺ 496 ማለትም 88.5 በመቶ የሚሆኑት በምግብ ራሳቸውን መቻላቸው ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ፕሮግራሙ በተነደፈበት ወቅት ለችግሩ ከተጋለጠው 15 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 5 ሚሊዮን ስር ለሰደደ የምግብ እጥረት የቀረው 10 ሚሊዮን ደግሞ ለጊዜያዊ ችግር የተጋለጠ እንደነበር ጠቅሶ መንግሥትም ለፕሮግራሙ ስኬት አስፈላጊውን የገንዘብና የማቴረያል ድጋፍ በመስጠት በፕሮግራሙ ዘመን መጨረሻ /2002 ዓ.ም/ ስር የሰደዳ የምግብ ዋስትና እጦት ያለባቸው ቤተሰቦችን ችግር በዘለቄታው ለመፍታት ጠንክሮ በመስራት ላይ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል።

   ምንጭ፡- የማስታወቂያ ሚኒስቴር