ጥቂት ስለ አቡጃ ስቴዲየም
የአፍሪካ ሚሌኒየም የመጀመሪያ በዓል ባለፈው ሚያዝያ 16 በናይጀሪያ መዲና አቡጃ ሼራተን ሆቴል በድምቀት ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ ኢትዮጵያ ሰላሳ የልዑካን ቡድን አባላቷን አሳትፋለች፡፡ ከልዑካን ቡድኑ አባላት መካከል አራቱ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ ጋዜጠኞቹ ከሚሌኒየም በዓል አከባበሩ በተጓዳኝ በርካታ የአቡጃ ከተማ መገለጫ ሥፍራዎችን የማየት ዕድል ገጥሟቸዋል፡፡ ይህ ጹሑፍ ከከተማዋ መገለጫዎች አንዱ በሆነው የአቡጃ ብሔራዊ ስቴዲየም ላይ አጭር ቅኝት ያደርጋል፡፡

ወደ አቡጃ ጉዞ ሲደረግ ቅድሚያ የሚገኘው ከከተማዋ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ኒናምዲ አዚኪዌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ነው፡፡ ከአውሮፕላን ማረፊያው ተነስቶ ወደ ውቧ አቡጃ ከተማ ሲጓዙ መግቢያው ላይ ከሚገኙ ተቋማት አንዱ የሆነውን የአቡጃ ብሔራዊ ስቴዲየም ያገኛሉ፡፡

ስቴዲየሙ ግንባታው በሐምሌ 1992 ዓ.ም ተጀምሮ የተጠናቀቀው በጥቅምት 1996 ዓ.ም ነው፡፡ ንድፉንና አርክቴክቱን ያዘጋጀው የጀርመኑ የምህንድስና ዘርፍ ሽላይሽ በርገርማን ሲሆን፤ ዋናውን ግንባታ ያካሄደው ጁሊየስ በርገር ናይጀሪያ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ነው፡፡ የቻይናው ሲቪል ምሕንድስና ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በበኩሉ የመጫወቻ መንደሩን ገንብቷል፡፡

ለግንባታው መንስኤም፤ በየአራት ዓመቱ የሚካሔደው ስምንተኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በአቡጃ እንዲካሔድ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ማኅበር ውሳኔ በማሳለፉ ነው፡፡ ጉዳዩ እንቅልፍ የነሳው የናይጀሪያ መንግሥትም በአፋጣኝ ስቴዲየሙ እንዲገነባ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ግንባታውም በ3 ዓመት ከ3 ወራት ተጠናቀቀ፡፡ 360 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ሆነበት፡፡

ስቴዲየሙ በ25ሺ ሜትር ካሬ ላይ ያረፈ ሲሆን ፤ ስልሳ ሺ መቀመጫዎች አሉት፡፡ ባለ ፎቅ ነው፡፡ የላይኛው 28ሺ ተመልካቾችን ሲይዝ፤ የታችኛው 32ሺ ተመልካቾችን ይይዛል፡፡

ጣራው ቀለል ያለና ሽፋን ያለው ነው፡፡ ባለኮንክሪት ቀለበታማ አውታር አለው፡፡ ይህ ደግሞ ከዓለማችን የመጀመሪያ ያደርገዋል፡፡ ለሀገሪቱ ፕሬዚዳንትና ተከታዮቻቸው ልዩ መመልከቻ ሥፍራ አለው፡፡ ይኸው 36 ማማዎች ያሉት ስቴዲየም 36 መግቢያና መውጪያዎች አሉት፡፡ ዘመናዊ መከለያዎች፣ ፖስታ ቤቶች፣ ባንኮችና ለሚዲያ አገልግሎት ምቹ የሆኑ ክፍሎችንም ይዟል፡፡ ሱቆችና ኪዮስኮች በአቅራቢያው ይገኛሉ፡፡ በማንኛውም ሰዓት ዝግጁ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዘዴ አለው፡፡ የሄሊኮፕተር ማረፊያ ሥፍራም በአካባቢው ይገኛለ፡፡

የቤት ውስጥ መጫወቻው አዳራሽ ሶስት ሺ ተመልካቾችን ያስተናግዳል፡፡ ጂምናዚየሙ ሁለት ሺ ሰዎችን የመያዝ አቅም አለው፡፡ የመዋኛ ሥፍራውም ሁለት ሺ ሰዎችን ሊይዝ ይችላል፡፡ ለአራት መቶ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የሌሎች አራት ሺ ተመልካቾች መኪናዎች የሚይዙ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች አሉት፡፡ የሆኪ መጫዎቻው ሶስት ሺ ተመልካቾችን ያስተናግዳል፡፡ አንድ ዘመናዊ ሰው ሰራሽ ሐይቅንም ይዟል፡፡

ይኸው ዓለም አቀፍ የጥንቃቄ ደረጃዎችን የያዘ ስቴዲየም በጠንካራ ብረት አጥሮች ተለብዷል፡፡ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት መከላከያ ጣቢያዎችም አሉት፡፡ ምርጥ የደህንነት ካሜራዎችም ተገጥመውለታል፡፡ የፈንጂ መመርመሪያና በአደጋ ጊዜ ፈጥነው የሚሰሩ የእሳት ቃጠሎ መከላለከያ አውቶማቲክ መሣሪያዎች በአመቺ ሥፍራዎች ተተክለውለታል፡፡ ዙሪያውም በሣርና በማንጎ ዛፎች ያጌጠ ነው፡፡ የሽቦ አጥሮችም ከበውታል፡፡

የአቡጃ ስቴዲየም በተጨማሪም ባህላዊ ትዕይንቶችንና ኮንሰርቶች እየተስተናገደበት ይገኛል፡፡ ለሃይማኖታዊ አገልግሎትም ይውላል፡፡ ይኸው ስታዲየም ዓለም-አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ለመሆኑ በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ተመስክሮለታል፡፡ ስቴዲየሙ ለናይጄያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን "ሱፐር ኢግልስ" የመኖሪያ ቤት ያህል የሚቆጠር ነው፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ አመቺ የአስፓልት መንገዶች በዙሪያው ይገኛሉ፡፡ ስቴዲየሙ ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 7/1996 ዓ.ም የተካሄደውን ስምንተኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አስተናግዷል፡፡ በውድድሩም ከ53 ሀገሮች የተውጣጡ ስድስት ሺ አትሌቶች በ22 የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች ተሳትፈዋል፡፡ አንድ ሺ ሁለት መቶ ባለስልጣናት ውድድሩን ተመልክተዋል፡፡ አንድ ሺ አምስት መቶ ጋዜጠኞች በስቴዲየሙ ተገኝተው ዘግበዋል፡፡

ሀገራችንም ከሚያዝያ 22 እስከ 26/2000 ዓ.ም የተካሄደውን 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አስተናግዳ በድል አጠናቃለች፡፡ ግና! የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ላሚንዲያክ እና የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሚስተር ሀማድ ካልካባን ጨምሮ ከእንግዶቻችንም ሆነ ከተለያዩ የስፖርት ባለሙያዎች አንድ ነገር ተነግሮናል፤ የስታዲየም ግንባታ፡፡ ስለዚህ "ድር ቢያብር…" እንዲሉ የስታዲየሙ ግንባታ ለአትሌቲክሱም ሆኖ እግር ኳስ ዕድገት ወሣኝነት ይኖረዋል፡፡

ከጌታቸው ወልዩ (ዋኢማ)