የወደቀ ሁሉ ተደናቀፍኩ ባይልስ...!

ፋሲካ ሊፈሰክ አንድ ሳምንት ነበር የቀረው። የሆሳዕና በዓል ዕለት። የክርስትና እምነት ተከታዮች ፀሎት ለማድረስ ማልደው ከሄዱባቸው ቤተክርስቲያናት መመለስ ጀምረዋል። ጊዜው ሶስት ሰዓት ገደማ ነው። ከሳምንታት በፊት ያስቸግር የነበረው አቧራ ሰሞኑን በጣለው የበልግ ዝናብ ተጠራርጎ አካባቢውና ሰማዩ ጥርት ብለዋል። ተፈጥሮ የቸረችው ንፁህ አየር ከእንጦጦ ጫፍ ተነስቶ ያለማቋረጥ ወደ አዲስ አበባ እየፈሰሰ መሆኑ ቆዳ ላይ በስሱ ሽው…ው…ው ሲልና ውስጥን ሲያረሰርስ ያስታውቃል።

በዚህ ውብ ዕለት ነው በከተማዋ ለአካባቢና ማሟያ ምርጫ 2000 ድምጽ የተሰጠው። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 18 የምርጫ ክልል ቀበሌ 02/03 የቅርስ ባለአደራ ተብሎ በሚጠራው ግቢ ውስጥ በተቋቋመው የምርጫ ጣቢያ ውስጥ በመስቀል ቅርጽ የተቋጠሩ የዘንባባ ቅጠል በግንባራቸው ላይ አስረው ከሆሳዕና በዓል የተመለሱ ነዋሪዎች በብዛት ተሰብስበዋል።

እንደየአመጣጣቸው አንድ አስር እየሆኑ በተዘጋጀላቸው አግዳሚ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ስለዕጩ ተወዳዳሪዎችና ፓርቲዎች ማንነት፣ ምልክታቸውና ስለአመራረጡ የሚሰጣቸውን ገለፃ ለአምስት ደቂቃዎች ያህል ይከታተላሉ። ወይዘሮ ፋናዬ ተስፋ ገለፃውን በጥሞና ከሚከታተሉት ሰዎች መካከል ተቀምጣለች። ከፊለፊቷ ያዘለችው ህፃኗን ጀርባ በእጇ እያሻሸች ዓይኗን በግድግዳ ላይ በተለጠፈው የድምጽ መስጫ ሞዴል ወረቀት ላይ ተክላ ማብራሪያውን ትሰማለች።

ፊቱን ወደ እናቱ አዙሮ የታዘለው የፋናዬ ድንቡሽቡሹ ህፃን አንገቱን በየተራ ወደ ግራና ቀኝ እያዞረ ከጎኑ የተቀመጡትን ሰዎች በፈግታ ይመለከታቸዋል። እንዲያጫዉቱት የሚፈልግ ይመስላል። ሰዎቹ ግን ትኩረታቸውን ወደ ገለፃው በማድረጋቸው ይህንን አላስተዋሉም።

ህፃኑ የዛሬ ሃያ ዓመት ገደማ ራሱን የሚችል ጎረምሳ ሲሆን አገሪቷም ያስቀመጠችውን ራዕይ ካሳከች መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ትሰለፋለች። ምናልባትም የህጅፃኑ እኩዮችድህነት ተረት መሆኑን ያበስሩን ይሆናል። የአገሪቷን ራዕይ ለማሳካት ደግሞ አመኔታ የሚጣልባቸውና ከህዝቡ ጋር ለመስራት የተዘጋጁ አመራሮች ያስፈልጋሉ። በተለይም ለህዝቡ ቅርበት ባላቸው የታችኛው የአስተዳደር እርከኖች የሚካሄደው ምርጫ ከዚህ አኳያ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።

ወይዘሮ ፋናዬ የተሰጠውን ገለፃና ማብራሪያ ተከታትላ ለተነሱ ጥያቄዎችም የተሰጡ ምላሾችን ካዳመጠች በኋላ ወደ መዝገብ ሹሞች እንድታመራ ተነገራት። ቀደም ሲል የተቀበለችውን የምርጫ ካርድ ስታሳይ የመዝገብ ሹሙ የካርዱን ቁጥር ተከትሎ ስሟን በመዝገብ ላይ በመፈለግ እንድትፈርም አመለከታት። በተነገራት መሰረት ፊርሟዋን አኑራ ስለመምረጧ የሚያረጋግጠውን የቀለም ምልክት በጣቷ ላይ በማስደረግ የድምጽ መስጫ ወረቀት ተቀብላ በምስጢር ድምጽ ወደሚሰጥበት የተጋረደ ቦታ ውስጥ ገባች።

ከደቂቃዎች በኋላ ሁለት ለየብቻ የተጣጠፉ ወረቀቶቸን ይዛ ወጣችና አንድ በአንድ በኮሮጆው ውስጥ ጨመረች። አንዱ ለቀበሌ ሌላኛው ደግሞ ለክፍለ ከተማ ምክር ቤት ተወካዮቸዋን የመረጠችባቸው ወረቀቶች መሆናቸው ነው። በሂደቱ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቁጭ ያሉት የህዝብ ታዛቢዎችና የዕጩ ተወዳዳሪ ተወካዮች ከምስጢራዊው ቦታ በስተቀር በድምጽ መስጫ ክፍሉ ውስጥ የሚካሄደው እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በንቃት ይከታተላሉ።

የድምጽ አሰጣጡ ሂደት ነፃና ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ መርካቷን ወይዘሮ ፋናዬ አጫውታናለች። "የ97ቱ ምርጫ ብዙ ጣጣዎች ነበሩበት። የዛሬው ግን ወከባና ግርግር አይታይበትም፤ ስርዓቱ ብቻ ያስደስታል። ዕጩዎቹን በፓርቲያቸው ዓላማና በስነ ምግባራቸው መዝኜ በትክክል ያስተዳድሩናል ብዬ ያመንኩባቸውን ነው የመረጥኩት። ስለሆነም ወደፊት በልማቱና በአስተዳደሩ የተሻለ ነገር እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ።" ስትል ሞቅ ያለ ፈገግታ መገበችን።

በዚሁ የምርጫ ጣቢያ ድምጹን ሰጥቶ ሲወጣ ያገኘነው ወጣት ያኩቡ ታምራት በበኩሉ የዘንድሮው ምርጫ በዕውቀትና በግል ውሳኔ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው ብሏል። ለመጀመሪያ ጊዜ ዕድሜው ለመምረጥ ደርሶ ድምጹን የሰጠው በአገር አቀፉ ምርጫ 97 እንደነበር የሚናገረው ወጣት ያኩቡ፤ ያኔ ግን በቡድናዊነት ስሜትና ጫና ምክንያት አመዛዝኖ መምረጥ እንዳልተቻለ ያስታውሳል።

"ተወዳዳሪ ፓርቲዎችና ዕጩዎቻቸውን መመዘንና ለይቶ መምረጥ ወሳኝ ነው። እኔ እንዲያውም ግዴታ ነው ብዬ አምናለሁ። በአሁኑ ወቅት ፖሊሶች ጥሩ የፀጥታ ስራ እየሰሩ ቢሆንም በተለይ በቀበሌ አስተዳደሮች አካባቢ ብዙ ጉድለቶች አሉ። እዚህ አካባቢ ለውጦቸን ማየት እንፈልጋለን። የለውጥ ሰዎችን ወደ ቦታው ማምጣት የሚቻለው በምርጫ ብቻ በመሆኑ ነው እኔም ዛሬ መጥቼ ድምጼን የሰጠሁት። ተወካዮችን መምረጥ ቢያንስ በቀጣዩ ጉድለቶች እንኳን ቢፈጠሩ ቅሬታ ለማቅረብና ማስተካከያ እንዲደረግ ለማስቻል ያመቻል ብዬ አምናለሁ።"

በወረዳ 18 የምርጫ ክልል ቀበሌ 41 የምርጫ ጣቢያ ሶስትና በወረዳ 15 የምርጫ ክልል ቀበሌ 27 የምርጫ ጣቢያ 1ሀ ድምፃቸውን የሰጡት አቶ ፍቃዱ ሮባና ወጣት ትኩ ገብረማርያምም የምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ይናገራሉ። ዕድገቱ የታየው በአንድ በኩል የህብረተሰቡ ግንዛቤ ጎልብቶ እያንዳንዱ ሰው በሰከነ አዕምሮ ነገሮችን ማየት መቻሉ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ፓርቲዎችም ለህግና ስርዓት ተገዢ ለመሆን ፍላጎት መሳየት በመጀመራቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።

በሚያዚያ 5 እና 12 የተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሟያ፣ የአዲስ አበባ፣ የክፍለ ከተሞችና የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ የአገሪቷን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወደፊት ያራመደ እንደሆነ የዕጩ ተወዳዳሪ ተወካዮችና የህዝብ ታዛቢዎች አረጋግጠዋል። አቶ አባድር በሽር በወረዳ 18 የምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማሟያ ምርጫ በግል የተወዳደሩትን ዕጩ በመወከል ነበር በቀበሌ 41 የምርጫ ጣቢያ ሶስት በታዛቢነት የተቀመጡት። ዕድሉን አግኝተው የድምጽ አሰጣጡን ሂደት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ ለመከታተል በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸውልናል።

"በምርጫ ጣቢያው ቀደም ብለን ከለሊቱ 11 ሰዓት ነበር የተገኘነው። ሁለችንም ቦታ ቦታችን ይዘን የሰነድ ቆጠራ ተከናወነ። በምርጫ አስተባባሪዎች አማካይነት የቀረበው ኮሮጆ ባዶ መሆኑን ካረጋገጥን በኋላ ተቆልፎ ድምጽ በሚሰጥበት ሥፍራ ላይ ተሰቀለ። የድምጽ አሰጣጡ ሂደት በምርጫ ቦረድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሰዓቱን ጠብቆ ሲጠናቀቅ በር ተዘግቶ የኮሮጆው አረንጓዴ ቁልፍ ከተሰበረ በኋላ ድምጹ ተራግፎ ተቆጠረ። በእያንዳንዱ የድምጽ መስጫ ጀርባ ላይ የምርጫ ቦርድ ማኅተም መደረጉ እየተረጋገጠ ቆጠራው ሲጠናቀቅ ወደ ኮሮጆው ተመልሶ በአዲስ ቁልፍ በጥንቃቄ ተቆለፈ። ሐሜት የሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ።"

የምርጫ ጣቢያ ሁለት የህዝብ ታዛቢ አቶ ለገሠ ደበሌ እንዳሉትም የድምጽ አሰጣጡ ሂደት የተሰካ ነበር። ለስኬቱም ህዝቡ፣ የምርጫ አስተባባሪዎች፣ ፖሊሶችና ተወዳዳሪዎች የየራሳቸውን ጥረት በማድረጋቸው በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል አቶ ለገሠ።

በተቆጠረው ድምጽ መሰረት የምርጫ አስተባባሪዎቹና ተዛቢዎች መተማመኛ ተፈራርመው ውጤቱ በማግስቱ በየምርጫ ጣቢያው ሲለጠፍ መራጩ በብዛት ወጥቶ ተመልክቷል። ይህም በማለዳ ተነስቶ የዘራው ዘር መብቀሉን ከሚያይ አርሶ አደር ጋር ይመሳሰላል።

ምርጫ በኢትዮጵያ በማዕከላዊ መንግስት ደረጃ ተግባራዊ መሆን የጀመረው አሁን ባለንበት ከፍለ ዘመን ውስጥ ቢሆንም ባህላዊ ምርጫ ግን ከጥንት ጀምሮ እንደነበረ ታሪክ መዝግቧል። ኢትዮጵያዊያን በባህላዊ ህጎችና ባህላዊ መዋቅሮች እምነት የሚጥሉባቸውን የአገር ሽማግሌዎችና በተግባራቸው የተመሰከረላቸውን ሰዎች ከመካከላቸው እየመረጡ ራሳቸውን ሲያስተዳድሩና ማህበራዊ ኑሮአቸውን ሲመሩ ስለመቆየታቸው የኦሮሞ የገዳ ስርዓት፣ የአማራ ሸንጎና የጋምቤላው ጀንዶንጎ ለአብነት ይጠቀሳሉ።

ምርጫው በማዕከላዊ መንግስት ደረጃ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ በንጉሰ ነግስቱ ዘመን ለመወዳደር ሃብት፣ ርስትና ከዘውድ አገዛዙ ጋር የተሳሰረ የዘር ሐረግ እንደ ዋናኛ መስፈርት ከመቅረቡም በላይ የአመራረጡ ሂደትም በዚሁ ልክ የሚቃኝ ነበር።

በወታደራዊው የደርግ ስርዓት ወቅትም ዕጩዎችን የመጠቆም መብት የነበራቸው የኢሠፓ አካላትና ወታደራዊ ክፍሎች ብቻ በመሆናቸው ተቃዋሚ ሆኖ ለመቅረብም ሆነ በግል ለመወዳደር ዕድሉ ዝግ የነበረ ብቻ ሳይሆን ለመወዳደር ማሰቡም በፀረ ህዝብነት አስፈርጆ ሌላ መዘዝ ማስከተሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

በዚህ ወቅት ቀድሞ የነበረው ባህላዊ የዴሞክራሲ ስርዓት እየደበዘዘ መጥቶ የህዝቡ መብት የተጨፈለቀበትና አምባገነንነት የነገሰበት ነበር ለማለት ይቻላል። በአገሪቷ ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለውና በህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚካሄድ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ስርዓት የተጀመረው በ1987 ዓመተ ምህረት ነው። ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫው በህዝቡ ተሳትፎ እየጎለበተ በመምጣት አገር አቀፍ ምርጫዎችን ተከትሎ ዘንድሮ ለሶስተኛ ዙር በተካሄደው የአካባቢ ምርጫ በመላ አገሪቷ ከ26 ሚሊየን በላይ መራጮች ተሳትፈዋል።

በአካባቢ ምርጫው የሚያሸንፉ ዕጩዎች አገልጋይነታቸውን ለመረጣቸው ህዝብ በማሳየት በተግባር የሚፈተኑ ስለመሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ህዝቡ በቀን ተቀን እንቅስቃሴው ተመራጮቹን ስለሚያገኛቸው በመልካም ተግባራቸው ለማመስገንና ሲያጠፉ ለማውገዝ የቀበሌና የወረዳ ምክር ቤት መዋቅር ከሌሎቹ የአስተዳደር እርከኖች የተሻለ ሆኖ ይገኛል።

በዚህ ደረጃ ተወዳድሮ ለማሸነፍና ህዝቡን ለማገልገል ከመጀመሪያው ፅኑ ዓላማ ይዞ መገኘትና መዘጋጀት የግድ ይላል። ካልሆነ ቃልና ተግባር ለየቅል መሆኑ ይጋለጥና ራቁት መቅራት ይመጣል። ጉዳዩ ለአንዳንዶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋት መሆኑን ከቅርቡ የአካባቢ ምርጫ ክስተት መረዳት ይቻላል።

ከጅምሩ ለፓርላማ ውድድር ብቻ ትኩረት ያደረጉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለክልልና ለከተማ ምክር ቤቶች በተወሰነ ደረጃ ቢወዳደሩም ወረዳና ቀበሌ ላይ ሲደርሱ ተንጠባጥበዋል። አንዳንዶቹም ባለቀ ሰዓት ላይ ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች የሚደመጡ ቢሆኑም እውነታው ግን ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዓላማ ባለመያዝና ዝግጅት ባለማድረግ ተወዳድረው ከሚሸነፉ ወደ ኋላ መሸሽን እንደ አማራጭ መውሰዳቸው እንደሆነ መገመት ይቻላል።

የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማጠናከር ቃል ገብተው መንገድ ከጀመሩ በኋላ ውስጣቸው ተሸንፎ በራሳቸው ጊዜ የወደቁት ተደናቀፍን ቢሉ ሽንፈትን መደበቂያ አይሆንምና ለወደፊቱ ሊማሩበት ይገባል እንላለን።

ምርጫ 2000 በሂደቱ የህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ ባህል እየጎለበተ መምጣቱን አብስሯል። የቅርብ አመራሮች ለመምረጥ የተደረገው ርብርብ ለሌሎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ሊጠናከር የሚገባው ልምድ ነው። በፓርቲዎች መካከል የታየውን ጨዋነት የተሞላበት የውድድር መንፈስም ልናደንቀው ይገባል።

በተፈራ በቀለ /ከዋኢማ/