ኢ.ዴ.ኃ.ህ. እና ምርጫ 2000

መስፍን ሺፈራው       

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት (ኢ.ዴ.ኃ.ህ) በሀገሪቱ ከተደራጁት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ነው። ፓርቲው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውስጥ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ሻል ያለ መቀመጫ ያለው ፓርቲ ነው።

ፓርቲው ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ምርጫዎች ተሳትፏል። ነገር ግን በ2000 በሚካሄደው የአካባቢና የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ለመሳተፍ ተመዝግቦ የምርጫው እለት ሲቃረብ ከምርጫ ራሱን ማግለሉን ገልጿል።

ህብረቱ ከምርጫው ራሱን ያገለለው አባሎቼ በገዢው ፓርቲ ወከባ ይፈፀብቸዋል፣ ምክንያት እየተፈለገ ይከሰሳሉ፣ እጩዎቼ እንዳይመዘገቡ ተደርጓል፣ የምርጫ ቦርድ የምርጫ ህጉን ለመተግበር ፈቃደኛ አይደለም፣ ገለልተኛም አልሆንም ወዘተ በሚል ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።

ፓርቲው ከምርጫው ራሱን ለማግለል እነዚህን ምክንያቶች ያቅርብ እንጂ እውነታው ከዚህ የተለየ ነው። ምክንያቱም አሁን በህብረቱ የተጠቀሱት ችግሮች በዚህኛው ምርጫ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቀደምት ምርጫዎችም ሲነሱ የነበሩ  በመሆናቸው ነው።

ህብረቱ እነዚህን ምክንያቶች ያቀረበው ለመሸፈኛ እንጅ ትክክለኛ አይደሉም። ለዚህም ሁለት ነባራዊ ሁኔታዎችን በማንሳት የህብረቱ ምክንያቶች አሳማኝ አለመሆናቸውን ማሳየት ይቻላል።

አንዱ ነባራዊ ሁኔታ አሁን በተካሄደው ምርጫ 32 ፓርቲዎች ተሳትፈዋል። ከመንግሥት ሚዲያ ጀምሮ ሀሳባቸውን እምነታቸውንና አቋማቸውን በተለያዩ መንገዶች እንዲያራምዱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ለህዝብ ሲገልፁ ከርመዋል፤ ከዚህም በላይ የገዥውን ፓርቲ የሚያንቋሽሽ አቋም በእነዚህ መድረኮች አራምደዋል። ይህን ተግባር የምርጫ ስነምግባር መመሪያው የማይፈቅድ ቢሆንም ተቀዋሚ ፓርቲዎች በግልጽ ሲያረራምዱት ከርመዋል።

ሁለተኛው ነባራዊ ሁኔታ በሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ እንደገና ሲዋቀር ኢዴኃህን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች መክረውበት ተቀብለውት የተፈጸመ መሆኑና የምርጫ ህጉም ቢሆን ሃሳባቸውን እንዲሰጡበት ተደርጎ የጸደቀ ሆኖ እያለ  ኢዴኃህ ይህንን ከምርጫ ራሱን ለማግለል እንደምክንያት ማቅረቡ ነው።  

በመሆኑም ከሁለቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ስንነሳ ህብረት ከምርጫው ራሱን ያገለሉትን ምክንያት ለመቀበል ያዳግታል። ይሄ ሽፋን ሆነ እንጂ ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ሁለት ናቸው። አንደኛው ምክንያት ከ1997 ምርጫ ወዲህ ተቀባይነቱ በከፍተኛ ደረጃ በመውረዱና በአንጻሩ ህዝቡ ከኢህአዴግ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት መፈለጉ የጎን ውጋት ስለሆነበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በህብረቱ ውስጥ ያለው መከፋፈል ነው።

በሀገራችን አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ፕሮግራማቸው ኢህአዴግን በመቃወምና የእሱን ሥራ በማንኳሰስ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ግልፅ ነው። ሕብረትም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ከጭፍን ተቃውሞ ያለፈ ለህዝቡ በተግባር ሊያከናውናቸው የሚችለው አማራጮች ማቅረብ ላይ ችግር ነበረበት።

ለምርጫ ብቻ የማያደርጉትን እናደርጋለን ብሎ ማቅረብና  ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚሄድ ፕሮግራም አቅርቦ መንቀሳቀስ ለየቅል በመሆናቸው ሕዝቡ ከኢህአዲግ ጋር ያለውን ቅሬታ በማስወገድ ከኢህአዲግ ጋር ተቀራርቦ መስራት ሲጀምር ሕብረቱ ሊያቀርበው የሚችለው ነገር በመጥፋቱ ከህዝቡ እየራቀ ሄዷል። ይሄም ሁኔታ በአሁኑ ምርጫ ህብረት ቦታ ሊያገኝ አንደማይችል አስገንዝቦታል።

ሁለተኛው ምክንያት በራሱ በህብረቱ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት ነው። በመሠረቱ ለህዝብ ጥቅም ያለቆመ ድርጅት ረጅም ርቀት መሄድ እንደማይችል በቀደሞው የቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ውስጥ  በግልጽ ታይቷል። ህብረትም በመሰረቱ የነጠረ የፖለቲካ አቋም ይዞ ህዝቡን ለመጥቀም ከመቆም ይልቅ ፓርቲውን ሽፋን በማድረግ የምትገኘውን ጥቅም አመቀራመት በመሆኑ በውስጡ መከፈፈል ተፈጥሯል። ለአብነት ያህል የህብረት አባል ድርጅት በሆነው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ውስጥ መከፋፈል መፈጠሩና ይሄም ወደሌሎች መስፋፋቱ ራሱን ከምርጫ እንዲያገል አስገድዶታል።

ከዚህ ውጭ ህብረት እንደሚለው ወከባና እንግልት ስለተፈፀመብኝ ነው የሚለው አሁን በሀገሪቱ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ተቀባይነት የሌለውየፖለቲካ ስልት ነው።ይሄ አባበል እውነት ከሆነ በሌሎች ቀደምት ምርጫዎች ላይ ለምን ራሱን አላገለለም? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ህብረት ራሱን ከምርጫ ማግለሉ ‘’ቆሜላችኋለሁ የሚላቸው ወገኖችን’’ በምርጫው አማራጭ እንዳያገኙ ከማድረግ ያለፈ ምንም ትርጉም የለውም። ይህ ተግባሩ ይበልጥ የህዝብ አመኔታን ያሳጣዋል እንጂ በምንም መስፈርት ህዝባዊ ሊያደርገው አይችልም። በዚህ ተግባሩም ህብረት ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና ለሕዝብ ያለው ክብር በግልጽ አሳይቷል።

ህብረት በራሱ ምክንያት ከምርጫው ቢገልልም ህዝቡ በነቂስ በመውጣት በምርጫው የሚፈልገውን ፓርቲ ወይም ግለሰብ መርጧል። በምርጫው ሂደትም ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲፈፀም አስተዋፅኦ አድርጓል። በምርጫው ሂደት ምንም ዓይነት ወከባና የምርጫውን ዲሞክራሲያዊ የሚያጎድፍ ተግባር እንዳልተፈፀመ ህዝቡ በየሚዲያዎች በሰጠው አስተያየቶች አረጋግጧል።