ቆም ብለን ድህነትን እናስብ-አዲስ አዋጅ፤ አዲስ ታሪክ

አብደላ ዑመር(ዋኢማ)

ኢትዮጵያ ሀገራችን በታረኳ የተለያዩ ሁኔታዎችን አሳልፋለች።በጎም ከፉም።ደግ ከሚባሉት ውሰጥ ዋነኛው የአሁኑ ትውለድም እየኮራበት ያለው ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ መኖሯ ነው።ይህን ለመቀዳጀት ደግሞ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ብዙ መስዋዕትነቶችን ከፍለዋል።ኢትዮጵያ ሀገራችን ነጻነቷን ሊዳፈሩ የመጡትን ለማንበርከክ ብዙ አዋጆችን አወጀች።አዋጆቹም ውጤታማ ነበሩ፤የታለመላቸውን ግብም መቱ።ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛዋ ነጻነትዋን አስከብራ የኖረች ሀገር ተብላ ለልጆቿም ሆነ ለተቀረው የአፍሪካ ፍሬ ኩራት ሆነች።ታዲያ ይህ በመስዋዕትነት የተገኘ ክብር ነው።ዘልዓለማዊ ክብር።

አሁን ደግሞ ሀገራችን በሌላ ብሄራዊ ውርደት ውስጥ ትገኛለች፤በረኃብና በኋላ ቀርነት ማጥ ውስጥ።ይህ  ግን አሁን የተፈጠረ አይደለም፤ከሀገራችን ጋራ አብሮ ለዘመናት የኖረ ቢሆን እንጂ።የቀደሙት ትውልዶች ሉዓላዊነቷን ላለማስደፈረር ይዋደቁበት በነበረበት ጊዜም ይህ ለክብሯ ጥላሸት የሆነ መገለጫዋ አብሯት ነበረ።የሚገርመው ግን አንድም ቀን አዋጅ አልታወጀበትም።ለምንም ነገር እጅ የማይሰጡት ኢትዮጵያውያን ድህነትንና ኋላቀርነትን ተቀብለው ለዘመናት አብረውት ኖረዋል።አሁን ግን ይህ አስቀያሚ መገለጫ እንገሽግሿቸዋል።ስለዚም ያን ከአንደበታቸው ወጥቶ ግቡን ሳይመታ የማይመለሰውን አዋጃቸውን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አወጁ።ቆም ብለን ድህነትን እናስብ፤አዲስ ምዕራፍ፤አዲስ አዋጅ፤በድህነት ላይ የተጎሸመ አዲስ ነጋሪት፤የጀግኖቹ የክተት ጥሪ አስተጋብቷል።

ከላይ እንደጠቀስኩት ሀገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃነትዋን አስከብራ የኖረች ብቸኛዋ ሀገር፤ረጅምና የሚያኮራ የስልጣኔ ታሪክ ያላት አገር በመሆኗ እንኮራባታለን ልንኮራባትም ይገባናል።እነዚህ የኩራት ምንጮቻችን ሁሉ ያለፉት ትውልዶች በጥረታቸው፣በላባቸውና በደማቸው ያስገኟቸው የስራ ውጤቶች ናቸው።ነገር ግን ሊያሳፍሩና ሊያሸማቅቁ የሚገቡ የብሄራዊ ውርደት ገጽታዎችም አሉብን።

በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ተመጽዋች ነች።ይህች ትልቅ የነጻነት ዝና ያላት ሀገር እራሷን መመገብ አቅቷት እንደህዝብ ምግብ ልመና ወደ አደባባይ እየወጣን ነው።ከልመና በላይ የአንድን ህዝብ ክብር የሚገፍና የሚያዋርድ ነገር የለም።ልመናችን ምላሽ እንዲያገኝም የመጽዋቾቻችንን ፍላጎት ማሟላት አለብን።በዚህም ምክንያት ሉዓላዊነታችንን በሚዳፈር መልኩ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም ይሞክራሉ።የቅርብ ጊዜ ትዝታችን የሆነውን HR2003 ልብ ይሏል።ታዲያ ይህ በሆነበት ሁኔታ አስተማማኝ የሆነ ነፃነት አለን ብሎ መናገር ይቻላል?

የአሁኑ የአገራዊ ውርደታችን መሰረታዊ ምንጭ ድህነትና ኋላቀርነት ነው።ታዲያ ከዚህ አሸማቃቂና አዋራጅ ከሆነ ሁኔታ ሀገራችንን ለማላቀቅ አንድ የጋራ አገራዊ እምነትና አመለካከት ይዘን ተከባብረንና ተፈቃቅደን በአንድነት ለመረባረብ ነው በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ቃል የገባነው።በአንድ ቃል የአገራዊ ውርድታችን ብቸኛ መፍትሄና ምንጩን ለማድረቅ የሚያስችለን አማራጭ ፈጣን፣ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት እውን ለማድረግ ነው ቃል የገባነው።

በአሁኑ ሰዓት በዓለም የኢኮኖሚ ማማ ላይ የሚገኙት ጀርመንና ጃፓን በታሪክ ከባድ አገራዊ ውርደት የደረሰባቸው አገሮች ናቸው።እነዚህ ሁለት ሀገራት የውርደቱን ምንጭ ለይተው በማወቅ፣ሁሉም ነገር ይህንን የውርደት ምንጭ ለማድረቅ ባለመ መልኩ ተንቀሳቅሰው አሁን ካሉበት ደረጃ መድረሳቸውን የተለያዩ መዛግብት ያስረዳሉ።

እኛ ኢትዮጵያውያን በድህነትና ኃላቀርነት ምክንያት እንደህዝብና እንደሀገር ትልቅ ውርደት ውስጥ ነው ያለነው።ይህንን  ብሄራዊ ውርደት ተረድተን ውርደቱን ከምንጩ ለማድረቅ በአንድነት ሁሉንም ነገር ችለን መረባረብ ብቸኛ አማራጫችን ነው።እጅግ ብዙ ሊባል ባይችልም ባለፉት ጥቂት አመታት የተወሰነ ርቀት መሄድ ችለናል።ባለፉት ጥቂት አመታት የታየው ለውጥም ለዘመናት ተጭኖን የኖረውን ድህነት አሽቀንጥሮ መጣል እንደሚቻልም አሳይቶናል።

ስለሆነም ካለፉት ጥቂት አመታት ልምዶቻችንና ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ለኛ የሚጠቅመንን በመውሰድ የብሄራዊ ውርድታችን ምንጭ የሆነውን ድህነት አስወግደን ካለፉት ትውልዶች የወረስነውን ኩራት አጣምረን መጓዝ ይኖርብናል።ይህንንው ለማድረግ ነው ለአንዲት ደቂቃ ቆመን ትልቁን ጠላት ከነምናምኑ ለማሽቀንጠር ቃል የገባነው።