|
የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቻችን ሲቃኙ |
| ሐሰን አሰፋ (ዋኢማ) በአገሪቱ በየአመቱ እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ኤሌክትሪክን ከነፋስ፣ ከከሰል፣ ከጂኦተርማልና ከውኃ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ተቀርፀው ተግባራዊ መሆን ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ በአገር ደረጃ በየዓመቱ በ17
የዛሬ ሁለት ዓመት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረው ግልገል ግቤ አንደኛ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት በተጨማሪ ግንባታቸው እየተካሄደ የሚገኙትን ግልገል ግቤ ሁለተኛና ሶስተኛ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን የቅኝታችን መጀመሪያ እናድርግ፡፡
Gelgel Gibe I hydroelectric power plant
Gelgel Gibe II hydroelectric power plant የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ እንደገለፁልን፤ ከፕሮጀክቱ ጠቅላላ ሥራ ውስጥ እስካለፈው ታህሳስ አጋማሽ ድረስ 60 በመቶው ተጠናቋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት በተራራ ውስጥ የሚያልፍ 26 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የዋሻ ግንባታ መኖሩ ፕሮጀክቱን ለየት ከሚያደርጉት ባህሪ አንዱ ነው፡፡ ከግልገል ጊቤ 1ኛ ኃይል አመንጭቶ የሚወጣውን 100 ሜትር ኪዩብ ውኃ በዋሻው ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ ወደ ግልገል ግቤ 2ኛ ፕሮጀክት የኃይል ማመንጫ ክፍሎች ተወርውሮ በሚገባው የውኃ ኃይል 420 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ ግንባታው በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የወጀብና ጊቤ ወንዝን ከኦሞ ወንዝ ጋር በማገናኘት የሚገነባው ግልገል ግቤ 2ኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለአካባቢው ነዋሪዎች ያበረከተው አስተዋኦ መኖሩንም መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ በተለይም ወደ ፕሮጀክቱ የሚወስደው 135 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ በመገንባቱ የቆሌና ፎፋ የገጠር መንደሮች ለማገናኘት አስችሏል፡፡ ከአንድ ሺ ለሚበልጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል አስገኝቷል፡፡ በተጨማሪ ፕሮጀክቱን በሚገነባው ድርጅት አንድ የእናቶች ማዋለጃ ክሊኒክ ተሰርቶ ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በመቀጠል የግልገል ግቤ ሶስተኛ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክትን እንቃኝ፡፡ ይህ ፕሮጀክት በ14 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባ ሲሆን፤ በዚህም ከሌሎች ፕሮጀክቶች በግዙፍነቱ ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ መብራቱ ተሾመ እንደሚሉት፤ በሳሊኒ የጣሊያን ኩባንያና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን መካከል የፕሮጀክቱ የኮንትራት ስምምነት የተፈረመው በሐምሌ 1998 ነው፡፡ በታህሳስ 1999 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት፤ የውኃ ማጠራቀሚያ ግድቡ 240 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፤ በድንጋይ ተሞልቶ የሚሠራ መሆኑ ከአፍሪካ በዓይነቱ ቀዳሚውን ሥፍራ እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡ ግድቡ 14 ነጥብ 5 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅም እንዳለውም ይገልፃሉ፡፡ ጠቅላላ የፕሮጀክቱ ግንባታ እ.ኤ.አ በ2012 ሲጠናቀቅ፤ አንድ ሺ 870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ በፕሮጀክቱ አስር የኃይል ማመንጫ ክፍሎች እንደሚገነባለት የሚናገሩት አስተባባሪው የማስተላላፊያ፤ ማከፋፈያና የውኃ ማስቀየሻ ግንባታዎችንም እንደሚያካትት አመልክተዋል፡፡ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት መንግሥት የአገሪቱን የአሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በአስተማማኝ ደረጃ በማሟላት ለጎረቤት አገሮች ኤሌክትሪክ በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚያስችለው አስተባባሪው የሚያብራሩት፡፡
ሌላው ፕሮጀክት የተከዜ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ነው፡፡ በዚህ ፕሮጀክት የግድብ፣ የኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ግንባታዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ እስካለፈው ታህሳስ አጋማሽ የ53 በመቶ ሥራቸው መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ
አስተባባሪው እንደገለፁት ማብራሪያ የግድቡ ከፍታ 187 ሜትር ሲሆን፤ 9 ነጥብ 4 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም አለው፡፡ ግድቡ መያዝ ከሚችለው ከዚህ ውኃ ውስጥ ደግሞ 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ያህሉ ሙሉ በሙሉ ወደ አራቱ የኃይል ማመንጫ ክፍሎች በመግባት 300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ግድቡ እስከ መጪው ሰኔ ውኃ ማጠራቀም የሚጀምር ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ የፕሮጀክቱ ሥራ የሚጠናቀቀው በ2002 ዓ.ም መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
Tekeze hydroelectric power plant
የፕሮጀክቱን የግንባታ ሥራ እያካሄደ ያለው ሲ ደብሊው ጂ ኤስ የተባለ የቻይና ኩባንያ የግንባታ ጥራት ተቆጣጣሪ የሆኑት ሚስተር ዴሪክፐን ማን እንደሚሉት ደግሞ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት የተጀመረውን ይህንኑ ፕሮጀክት ደረጃውን ጠብቆ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ ድርጅታቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የተከዜ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ እንደተመደበለት ለማወቅ ተችሏል፡፡ መንግሥት በመደበው 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ባለፈው ዓመት መጨረሻ ግንባታው የተጀመረው ሌላው ፕሮጀክት ደግሞ የበለስ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ነው፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ክፍሌ ሆሮ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ ከጣና ኃይቅ በሰዓት 160 ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በመጠቀም ይህንኑ ውኃ በ12 ኪሎ ሜትር ዋሻ ውስጥ በማሳለፍ ለኃይል ማመንጨት ተግባር ለማዋል በሚያስችል መልኩ የሚገነባ ነው፡፡ እስከ ታህሳስ 1999 ዓ.ም ያለው የፕሮጀክት አፈፃፀም 20 በመቶ የተከናወነ ሲሆን በ2001 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
ፕሮጀክቱ ለኃይል ማመንጨት ከጣና ኃይቅ የሚጠቀመው ውኃ በክረምት ወደ ኃይቁ ውስጥ የሚገባውን ተጨማሪ ተፋሰስ የሚጠቀም መሆኑ በኃይቁ ስነ-ህይወት ላይ አሉታዊ ተዕኖ እንደማያስከትልም አስተባባሪው ያስረዳሉ፡፡ Belesa hydroelectric power plant በሳሊኒ የጣሊያን ኩባንያ አማካኝነት በምዕራብ ጎጃም ዞን አቸፈር ወረዳ የሚገነባው ይኸው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ፤ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ በቅርቡ የግልገል ግቤ 2ኛን የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት በጎበኙበት ወቅት እንደገለፁት፤ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ተግባራት አንዱና ዋነኛው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ ማድረግ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የሚገኘውን 17 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሽፋን በቀጣዩቹ አራት ዓመታት ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ ግብ መጣሉንም ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ዕቅድ ደግሞ በኃይድሮ፣ በነዳጅና በጂኦተርማል እየመነጨ የሚገኘውን ከአንድ ሺ ሜጋ ዋት ያልበለጠ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቦት ወደ አራት ሺ ሜጋ ዋት ለማሳደግ የሚያስችሉ ዘመናዊና ትላልቅ የኃይድሮ አሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የሚሳካ መሆኑን ሚኒስትሩ ያብራራሉ፡፡ እንደ አቶ ዓለማየሁ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉት የግልገል ግቤ 2ኛ፣ በለስ፣ የተከዜ፣ ፊንጫ አካባቢ የሚገኘው የአመረቲትሸና የግልገል ግቤ ሶስተኛ ከፍተኛ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ይኖራል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በአገር ውስጥ በየዓመቱ በ16 በመቶ እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት በማስቻላቸውም ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ አገራት የኤሌክትሪክ ኃይልን ኤክስፖርት በማድረግ (ወደ ውጪ በማስወጣት) ከሽያጩ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት እንደሚያስችሉም ያስረዳሉ፡፡ እንዲሁም በአገር ውስጥ ለሚቋቋሙ ኢንዱስትሪዎችና ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ተቋማት በቂና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት፡፡ በየአመቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎት መጨመር በአገራችን እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት መገለጫ ነው የሚሉት አቶ ዓለማየሁ፤ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መገንባትም ይህ ዕድገት ቀጣይና አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋኦ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ እኛም በመንግሥት በጀትና ከውጪ በተገኘ እርዳታና ብድር በተገኘ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ እየተገነቡ ካሉት አምስት ትላልቅ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል የአራቱን የግንባታ ሂደት ቅኝታችንን አበቃን፤ ቸር ይግጠመን፡፡ |
|
|
|
|