የኤርትራ መገናኛ ብዙኋን የጎረቤት አገሮች ሰላምን በማደፍረስ ተግባር ላይ መጠመዳቸው ተገለጸ

መቀሌ ግንቦት 10/2000/ዋኢማ/ የኤርትራ መገናኛ ብዙኋን የአገሪቱን አንገብጋቢ የሰላም፤የዴሞክራሲና የልማት ጉዳዮች ላይ ከማትኮር ይልቅ በጎረቤት አገሮች ሰላም ማደፍረስ ተግባር ላይ መጠመዳቸው አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ የገባ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ አስታወቀ ።

የኤርትራ መንግሥት የግፍ አገዛዝን በመቃወም ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ የገባው በኤርትራ ቴሌቪዥንና ሬድዮ ይሰራ የነበረው ጋዜጠኛ ገብረመድህን አብረሃ እንደገለጸው፤የኤርትራ ህዝብ በሻዕቢያ የሚደርስበት ስቃይና መከራ በአሁኑ ወቅት አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል ።

የሻዕቢያ መንግስት የሚቆጣጠራቸው የኤርትራ መገናኛ ብዙኋን የአገሪቱን አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሆኑ የሰላም፤የዴሞክራሲና የልማት ጉዳዮች ላይ ከማትኮር ይልቅ ዋነኛ አጀንዳቸውና ጊዚያቸው በጎሮቤት አገሮች አልቧልታ ላይ መጠመዳቸውን አመልክቷል ።

የኤርትራ ህዝብ ህልውና ከባድ ፈተና ውስጥ በወደቀበት በአሁኑ ወቅት የኢሳያስ መንግስት የኤርትራ ሃብትና ንብረትን የጎሮቤት አገሮች የውስጥ ጉዳይን ለማተራመስና ተቃዋሚ ድርጅቶች ለመደገፍ እያዋለው እንደሚገኝ ገልጾ የኤርትራ ህዝብ ስለራሱ የውስጥ ጉዳይ የሚመክርበት የሰላም አየር ለማምጣት ሻዕቢያን በቃህ ሊለው ይገባል ብሏል።

ኤርትራ ዜጎቿ የመናገርና የማሰብ መብታቸው አጥተው የሲኦል ኑሮ እንዲገፉ ተገደዋል ያለው ጋዜጠኛ ገብረመድህን በስርዓቱ የተማረሩ ወጣቶች ህይወታቸውን ለማቆየት ወደ ተለያዩ አገሮች መሰደድ ብቸኛው አማራጭ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል።

ብዙሃን ኤርትራውያን ከፖለቲካዊ ስልጣንና ከልማቱ ተገልለው የኢሳያስን አገዛዝ አሜን ብለው እንዲቀበሉ በመሳሪያ ሃይል በታፈኑበት በአሁኑ ወቅት ጥቂት ባለሥልጣናትና ወታደራዊ አዛዦች እንዳሻቸው የሚፈነጩባት አገር እንደሆነች መታዘቡን ገልጿል።

አገሪቱን ለመምራት ህጋዊ መሰረትም ሆነ ተጠያቂነት የሌለው የኢሳያስ መንግሥት ኤርትራን እንደአገር ለጥፋት እየዳረጋት በሚገኝበትና የተለየ አመለካከት የያዙ ዜጎቿ በሚታሰሩባትና በሚገደሉባት በአሁኑ ወቅት የኤርትራ መገናኛ ብዙኋን ኤርትራ ወንጀል የማይፈጸምባት ብቸኛ አገር ነች የሚል መዝሙር መስማት የተለመደ ቅጥፈት መሆኑን አብራርቷል።

የኤርትራ ህዝብ ካሁን ወዲያ የሻዕቢያን የግፍ አገዛዝ ተሸክሞ የሚያዘግምበት ወቅት እያከተመ መሆኑን የተናገረው ጋዜጠኛ ገብረመድህን ሁሉም ዜጋ ለኤርትራ ህዝብና ለአካባቢው ሰላም ጠንቅ የሆነውን ስርዓት ለመጣል መነሳሳት እንዳለበት ጥሪ ማቅረቡን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።