የእንደጋኝ ወረዳ ተወላጅ ባለሀብቶች ያሳዩትን አበረታች የልማት ውጤት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

ወልቂጤ ግንቦት 5/2000/ዋኢማ/ በጉራጌ ዞን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሚገኙ የእንደጋኝ ወረዳ ተወላጅ ባለሀብቶች በሚሌኒየሙ ከመንግሥት ጋር በጀመሩት እንቅስቃሴ ያሳዩትን አበረታች የልማት ውጤት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ። የመራቢቾ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ተከበረ።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ይግለጡ አብዛ የመራቢቾ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል አከባበር ላይ እንደገለጹት፤ የእንደጋኝ ወረዳ ያለበትን የልማት ችግር ለመፍታት ባለሀብቶች የሚያደርጉትን ጥረት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።

በመላው አገሪቱ ከተሞች የሚገኙ የወረዳው ተወላጆች በአዲሱ ሚሌኒየም የአካባቢያቸውን የልማት ችግር ለመፍታት ከመንግስትና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው የጀመሩት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያሳየ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ለተግባራዊነቱ መረባረብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ሞሎሮ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የህብረተሰቡና የአካባቢው ተወላጆች የልማት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ተወላጆቹ የ50 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረውን የመራቢቾ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አገልግሎት ለማሻሻል ለቤተመጻሕፍት ግንባታ፣ ለተዳከሙ የመማሪያ ክፍሎች ጥገና፣ ለመቀመጫ ወንበሮች፣ ለግቢው አጥርና ለተለያዩ የውስጥ ቁሳቁስ ማሟያ ከ500 ሺህ ብር በላይ ማሰባሰባቸውን አቶ ንጋቱ አስረድተዋል።

እንዲሁም የ10ኛን ክፍል ካጠናቀቁ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች የመሰናዶ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የወረዳው አመራር አባላት የአንድ ወር ደመወዛቸውን፣ እንዲሁም የወረዳው የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው ከ10 እስከ 50 በመቶ ተቀናሽ በማድረግ ከ138 ሺብር በላይ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ አስተዳደር የወረዳውን የትምህርት አገልግሎት ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 100 ሺ ብር ድጋፍ እንደሚሰጥ ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ይግለጡ አብዛ በዚሁ ጊዜ ቃል ገብተዋል።

የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስሜ ገብረስላሴ በበኩላቸው መንግስት በወረዳው ልማት ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥረቱ ከዞኑ ወጪ ባሉ ባለሀብቶችና ምሁራን ሊደገፍ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የወረዳው አንጋፋ ምሁር ዶክተር ሀይሌ ወልደማርያም እንደገለፁት፤ ለማንኛውም ዕድገት ቁልፍ መሳሪያ የሆነውን ትምህርት ለማስፋፋት ባለሀብቶችና ምሁራን አቅማቸውን ከመንግስትና ከህብረተሰቡ አቅም ጋር አቀናጅተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በአንድ የአካባቢው ተወላጅ ከ176 ሺ ብር በላይ በሚገመት ወጪ የተገነባ የትምህርት ቤቱ ቤተመጻሕፍት የተመረቀ ሲሆን፤ በወረዳው ልማት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች ሽልማት ተሰጥቷል።

በበዓሉ ላይ የሚመለከታቸው የዞንና የወረዳ አመራር አካላት፣ ከዞኑ ውጪ የሚገኙ ባለሀብቶች፣ ምሁራን እንዲሁም በወረዳው የመንግስት ሰራተኞችና የተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎች ተሳታፊ መሆናቸውን የጉራጌን ዞን ማስታወቂያና ባህል መምሪያ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።