በመቀሌ ከተማ 46 ኪሎ ሜትር የውሰጥ ለውስጥ መንገድ መጠገኑና 30 ኪሎሜትር አዲስ መንገድ መከፈቱ ተገለፀ

መቀሌ ግንቦት 5/2000/ዋኢማ/ በመቀሌ ከተማ 46 ኪሎ ሜትር የውሰጥ ለውስጥ መንገድ መጠገኑና 30 ኪሎሜትር አዲስ መንገድ ተከፍቶ ለአገልግሎት መብቃቱን የከተማው ዋና አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ገለጸ ።

በጽሕፈት ቤቱ የፕላንና የመሠረተ ልማት ማዘጋጃ አገልግሎት ኃላፊ አቶ አስጎዶም በርሀ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ በከተማው ለታክሲ አገልግሎት ብቻ የተፈቀደ 46 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ2ነጥብ7 ሚሊየን ብር ወጪ ተጠግኖ ለአገልግሎት በቅቷል።

እንዲሁም በከተማው በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግቶ ከነበረው 33 ኪሎሜትር መንገድ ውስጥ 30 ኪሎሜትሩን ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመክፈትና ጠጠር በማልበስ ለአገልግሎት እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ ከስድስት ሚሊየን ብር በላይ በጀት እየተካሄደ ያለው 2ነጥብ 7 ኪሎሜትር የውስጥ የውስጥ መንገድ ጥርብ ድንጋይ የማንጠፍ ሥራ ውስጥ 75 በመቶ ያህሉ መጠናቀቁና ቀሪው በተያዘው ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅን አስረድተዋል ።

በከተማው 30 ሚሊየን ብር ተመድቦለት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ሲጓተት የነበረው ስድስት ኪሎሜትር ነባር አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ዘንድሮ ተጠናቆ ርክክብ ከመደረጉም በተጨማሪ በስድስት ሚሊየን ብር ወጪ 1ነጥብ 3 ኪሎሜትር አዲስ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ጠቁመዋል ።

በቀዳማይ ወያነ የአካባቢ መስተዳድር በቀበሌ 20ና 16 ከሚገኙ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዮሃንስ ታደሰና ወይዘሮ አጸደ ገብረየሱስ በሰጡት አስተያየት በተለይም የጥርብ ድንጋይ መነጠፉ ከክረምት ጭቃና አቧራ ስለሚከላከልላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል ።