አዲሶቹ የአፍሪካ ህብረት የበላይ የስራ አመራሮች ከሚዲያ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ አስታወቁ

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2000/ዋኢማ/ አዲሶቹ የአፍሪካ ህብረት የበላይ የስራ አመራሮች የአህጉሪቱን ሰላምና ፀጥታን ጨምሮ ህብረቱ በሚያካሂዳቸው የተለያዩ ስራዎች ላይ ከሚዲያ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሚስተር ጃን ፒንግ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ከውጭና አገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጋር የትውውቅ ፕሮግራም በካሄዱበት ወቅት እንደገለፁት፤ህብረቱ ወደፊት ከጋዜጠኞች ጋር እጅ ለእጅ ተያየዞ ይሰራል።

ሚስተር ጃን ፒንግ

በአህጉሪቷ በሚካሄዱ የሰላም፣ የፀጥታና የልማት ስራዎች፣ በወቅታዊ መረጃዎች ፣የተለያዩ ጉባኤዎች ሲካሄዱ ስለጉባኤው መረጃን በሀላፊነት የሚሰጥ አካል ስለመኖር፣ መረጃ በሚሰጥበት ወቅት ስለሚከሰተው የቋንቋ ችግር እና በቋሚነት በህብረቱ ስለሚሰሩና ስለሚካሄዱ ተግባራት ከጋዜጠኞች ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

መረጃ የሚሰጥበት ቋሚ ቦታ አለመኖርና ለሕዝብ መድረስ ያለበትን መረጃ ለማድረስ ችግር ማጋጠም በሚሉት ነጥቦች ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች የህብረቱ የበላይ የስራ ሃላፊዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ አሉ የተባሉት ችግሮችን በአስቸኳይ በማስወገድ የመረጃ ፍሰቱ የተፋጠነ እንዲሆን እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የህብረቱ ሊቀመንበር ጃን ፒንግ እንደተናገሩት፤ ህብረቱ ቃል አቀባይ የሚኖረው ሲሆን፤ በየአንዳንዱ አህጉራዊ ጉባኤ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይዘጋጃል።

እያንዳንዱ የህብረቱ የስራ ክፍሎች የሚፈጽሟቸውን ስራዎች በተመለከተ በየግል ለጋዜጠኞች መረጃ የሚሰጡበት ሁኔታ እንደሚመቻች የስራ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል።

ህብረቱ በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ከሚሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ በተለያዩ ልማታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውቸውን ተግባራት ለህዝብ ጆሮ ለማድረስ ከጋዜጠኞች ጋር መስራት እንደሚፈልግ አመልክቷል።

የአፍሪካ ህብረት ለማከናወን ላቀዳቸውና ለሚያካሂዳቸው ተግባራት መሳካት ሚዲያ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚገባው የስራ ሃላፊዎቹ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።