አዲስ አበባ ግንቦት 5/2000/ዋኢማ/ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪ ልማት በከተማዋ የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል አወንታዊ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ። በክፍለ ከተማው የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የሚሌኒየም በዓል ዛሬ ተከበረ።
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ይርጋለም ኩመልቲ ለበዓሉ ተሳታፊዎች እንዳስታወቁት፤ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪ ልማት በከተማዋ የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር በማቃለል በኩል እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ ሲሆን ውጤቱም በተግባር እየታየ ነው።
በርካታ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በህብረት ስራ ማህበራት በመደራጀት በተለያዩ ሙያዎች መሰማራታቸውንና ምርታማ መሆናቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በሚያገኙት ገቢም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከማስተዳደራቸውም በላይ ለሌሎችም የስራ ዕድል እየፈጠሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ በመስኩ የተሰማሩ ወጣቶች በስራቸው ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለወደፊቱም ጥረታቸውን በማሳደግ ለሌሎች አርዓያነት ያለው ተግባር ማከናወን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በክፍለ ከተማው የጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ቡድን መሪ አቶ ራጲራ አለሙ በበኩላቸው፤ በ415 የህብረት ሥራ ማኅበራት በተለያዩ የሙያ መስኮች ለተደራጁ ከ16 ሺ የሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ በማምረትና አገልግሎት ስራ ላይ ለተሰማሩት ማህበራትና ግለሰቦች ከ19 ሺ የሚበልጥ የመስሪያ ቦታ ተዘጋጅቶ መሰጠቱን ጠቁመው፤ ማህበራቱ ያለባቸውን የመስሪያ ካፒታል ዕጥረት ለማቃለልም ብድር እንዲያገኙ መደረጉንና ለአባላትና ለማህበራቱ መሪዎች ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዓሉ የተከበረበትን አዳራሽ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ማህበራት አባላት እንደሰሩት አመልክተው፤ በዓሉ ከተከበረ በኋላም የስልጠና መስጫና የመሰብሰቢያ ቦታ በመሆን እንደሚያገለግል ተናግረዋል።
በበዓሉ ላይ የበለጠ ውጤታማ የሆኑ ማህበራት ልምዳቸውን ለሌሎች ያካፈሉ ሲሆን፤ ማህበራቱም ለስራቸው ስኬት ዕገዛ ላደረጉላቸው የቀበሌና የክፍለ ከተማ የስራ ኃላፊዎች ሽልማት መስጠታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።