ከ134 ኩባኒያዎች ጋር የቡና ንግድ ምልክት ፍቃድ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2000/ዋኢማ/ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የቡና ንግድ በሚካሄድባቸው 29 አገሮች የተረጋገጠውን የባለቤትነት መብት ጥቅም ላይ ለማዋል ከ134 ኩባኒያዎች ጋር የቡና ንግድ ፍቃድ ምልክት ስምምነት መፈረሙን የኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ኢትዮጵያ የልዩ ቡና ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ ያደረገችው ጥረትና ባጭር ጊዜ ውስጥ ያገኘችው ውጤት ለሌሎች ታዳጊ አገሮች በአርአያነት እንደሚጠቀስ ተጠቁሟል።

የጽህፈት ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ዛሬ በጋራ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ደቡብ አፍሪካና አውሮፓ በሚገኙ 29 አገሮች የኢትዮጵያ የባለቤትነት መብት የተረጋገጠላቸውን ሲዳሞ፣ ሐረርና ይርጋ ጨፌ ቡና የንግድ ምልክቶችን ለመጠቀም የፍቃድ ስምምነቱን የፈረሙት 84 ዓለም አቀፍና 50 የአገር ውስጥ የቡና ንግድ ኩባኒያዎች ናቸው።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ጌትነት ሁነኛው እንደገለጹት፤ ከክፍያ ነፃ የሆነ የንግድ ፍቃድ ምልክቱን ለመጠቀም ስምምነት የፈረሙት ኩባኒያዎች አጠቃላይ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ቡናዎች የሚወክለውን ምልክትና ለሐረር፣ ይርጋ ጨፌና ሲዳሞ ቡናዎች የተሰጡትን የንግድ ምልክቶች በቡና መያዣዎቻቸው ላይ በመለጠፍ ለቡና ጠጪዎችና ተጠቃሚዎች የማስተዋወቅ ተግባር ያከናውናሉ።

በስምምነቱ መሰረት አገሪቷም የቡና ጥራትን በመጠበቅ ቀጣይነት ባለው መልኩ ምርቱን ለኩባኒያዎቹ የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት ገልጸው፤ ለዚህም እንዲረዳ ስምምነቱን የፈረሙት ዓለም አቀፍ ኩባኒያዎችና የአገር ውጥ ቡና ላኪዎችና የቡና ዩኑየኖች በጋራ የሚሰረቡት መድረክ መፈጠሩን ተናግረዋል።

ከስልሳ በመቶ በላይ የውጭ ምንዛሪ ድርሻ ያለውና ከ15 ሚሊየን በላይ ህዝብ መተዳደሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና በልዩ ጣዕሙ በዓለም አቀፍ ቡና ጠጪዎች ተቀባይነት ያለው ቢሆንም በግንዛቤና አቅም ማነስ ምክንያት አዕምሮአዊ ንብረትነቱ በውጭ ኩባኒያዎች ተወስዶ መቆየቱን የጠቀሱት ተወካዩ፤ ከአራት ዓመት ወዲህ በተደረገው ጥረት አሁን የተገኘው ውጤት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።

የጽህፈት ቤቱ የህግ፣ ፖሊሲና ፕላን ዳይሬክተር ወይዘሮ ኢፍቲያ ማርይሁን በበኩላቸው፤ የሶስቱ የተፈጥሮ ቡናዎች የንግድ ምልክት ባለቤትነት መረጋገጡና ከቡና ንግድ ኩባኒያዎች ጋር የፍቃድ ስምምነት መፈረሙ የምርቱን የመወዳደር አቅም ከማሳደግና አምራቹን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ለአገሪቷ ዝናን ያተርፋል።

በጽህፈት ቤቱ ከአራት ዓመት በፊት በተጀመረው የኢትዮጵያ የቡና ንግድ ምልክትና ፍቃድ ፕሮጄክት አማካይነት የብዙ ዘመን አርሶ አደሩ የጥረት ውጤት የሆነው የአዕምሮአዊ ንብረት ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረትና ባጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘው ውጤት ለሌሎች ታዳጊ አገሮችም በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የስራ ኃላፊዎቹ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የብዙ ዘረ-መልና የእርሻ ምርቶች ባለቤት በመሆኗ አሁን የተገኘውን ውጤት መነሻ በማድረግ ከቡና ባሻገር ለድህነት ቅነሳውና ለሚሌኒየሙ የልማት ግቦች መሳካት አስተዋጽኦ ያለቸውን የተለያዩ አዕምሮአዊ ንብረቶች የባለቤትነት መብት ለማረጋገጥ ጽህፈት ቤቱ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ ኃላፊዎቹ ማስታወቃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።