በአገሪቱ የተጀመረውን ፈጣን ልማት አጠናክሮ ለመቀጠል ደኢህዴን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መዘጋጀቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2000/ዋኢማ/ በአገሪቱ የተጀመረውን ፈጣን ልማት አጠናክሮ ለመቀጠል ደኢህዴን/ኢህአዴግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መዘጋጀቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሞክሪያ ኃይሌ አስታወቁ።

አቶ መኩሪያ ኃይሌ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ደኢህዴን/ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበውን ሰላም ፣ልማትና ዴሞክራሲ ለማጠናከርና የህዝቡን ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋል።

ደኢህዴን/ኢህአዴግ ለህብረተሰቡ ፖለቲካዊ መብት መረጋገጥ የሚታገል ድርጅት ሆኖ ይቀጥላል ያሉት አቶ መኩሪያ፤ 15ኛ ዓመቱን እያከበረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ለተግባራዊነቱ ቃል መግባቱን አስታውቀዋል።

በደቡብ ክልል የሚገኙ 56 ብሔረሰቦች ፍትሃዊ የሆነ ልማትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ደኢህዴን ትግል የሚያደርግ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በልማቱም ዘርፍ እያከናወናቸው ያላቸውን ተግባራት ለማሳደግ ጠንክሮ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

በክልሉ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች የልማት ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች በቀጣይም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደረገውን ርብርብ ህብረተሰቡ ከደኢህዴን/ኢህአዴግ ጐን በመሠለፍ የላቀ አስተዋፅኦ እንዲያደርግም አቶ መኩሪያ አሳስበዋል።

በክልሉ በእያንደንዱ ቀበሌ በእንስሳት፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በሰብል ዘርፍ ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ሦስት ሦስት ባለሙያዎች የተመደቡ ሲሆን፤ አርሶ አደሩ ተጨባጭ የሆኑ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንዲሻሻሉና እንዲወገዱ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተሞች በከተሞች ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን በማስፋፋት፣ እንዲሁም በቤቶች ልማት የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን አቶ መኩሪያ ጠቁመው፤ 300 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ተመድቦ የከተማው ህብረተሰብ ከድህነት የሚወጣበት ሥርዓት መፈጠሩን አስታውቀዋል።

የቤቶች ልማት ለጊዜው በሰባት የክልሉ ከተሞች በ1999 የተጀመረ ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት በ12 ከተሞች የቤቶች ልማት በመከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት በሰባት ከተሞች በመገንባት ላይ ያሉ 5ሺ 260 ቤቶች በመጭው ሁለት ወራት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች እንደሚሸጋገሩ አቶ መኩሪያ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።