በደቡብ የጐብኝዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ማደጉ ተገለፀ

አዲስ አበባ ግንቦት5/2000/ዋኢማ/ ሚሌኒየሙን መነሻ በማድረግ የክልሉን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የመስህብ ሃብቶች ለማስተዋወቅ የተሰራው የፕሮሞሽን ሥራ የጐብኝዎችን ቁጥር ከእጥፍ በላይ እንዳሳደገው የደቡብ ክልል ቱሪዝም ፓርኮችና ሆቴሎች ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ አልማዝ ባየሮ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ሚሌኒየምን ምክንያት በማድረግ ኤጄንሲው የክልሉን የቱሪዝም ሃብቶች ለማስተዋወቅ ዘርፈ ብዙ ሥራ ተሰርቷል።

ሚሌኒየሙ የፈጠረውን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በክልሉ በቱሪዝም የተሰሩ ስራዎችንና ያሉትን ተፈጥሯዊ፣ ታራካዊና ባህላዊ መስህቦች የማስተዋወቅ ስራ በመስራቱም የጐብኝዎች ቁጥርና የተገኘው ገቢ በእጥፍ ጨምሯል።

በ1999 ዓ.ም. ወደ ክልሉ ከመጡ ጐብኝዎች 13.8 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ስድስት ወራት ብቻ ግን ወደ 268,820 ጐብኝዎች ተስተናግደው 14 ሚሊዮን ብርም ገቢ መሆኑን ሃላፊዋ ገልጸዋል።

ከ268,820 ጐብኝዎች ውስጥ 230ሺ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ጐብኝዎች መሆናቸው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሚሌኒየማቸውን የሀገር ውስጥ መስህቦችን በመጐብኘት እያከበሩት እንዳሉም ያሳያል ብለዋል።

ክልሉ የተፈጥሮ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ባለቤት ቢሆንም በቱሪዝም ዘርፍ ብዙም ተጠቃሚ እንዳልነበረ የጠቆሙት ስራ አስኪያጇ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የክልሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለመስህቦች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመሰጠቱ ህብረተሰቡ መስህቦችን መንከባከብና መጠበቅ በመጀመሩ ጥሩ ለውጦች መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

ቱሪስቶችን የሚያስጐበኙ ወጣቶችም በማህበር ተደራጅተውና አስፈላጊው ስልጠና ተሰጥቷቸው በመሆኑ ጐብኝዎች ይደርስባቸው ከነበረ መጉላላትና ውጣ ውረድ ተላቀዋል ብለዋል ።

ጐብኝዎች ከሚያጋጥማቸው ችግሮች ግንባር ቀደም የሆኑት የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የማረፊያ ቦታና እንዲቆዩ የሚያስችሉ ሁኔታዎች አለመኖር ናቸው ያሉት ወ/ሮ አልማዝ ፣በኤጀንሲው በኩል በየዓመቱ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ የማካሄድና ባለሃብቶችን ወደ ቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ሄደው እንዲሰማሩ የማድረግ ስራ በመስራት ችግሮችን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ ክልሉ የሚመጡ ጐብኝዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚያቀርቡትን ቅሬታ ለመፍታት ይቻል ዘንድም የሆቴልና ሬስቶራንት ባለሀብቶች ማህበርን በክልል ደረጃ በማቋቋም ቅሬታዎችን በጋራ የማስተካከል ስራም እየተሰራ ነው ሲሉ ሃላፊዋ ለዋልታ አስታውቀዋል።