አዲስ አበባ ግንቦት 5/2000/ዋኢማ/ ኤርትራና ጅቡቲ በዓለም አገራት ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘውን የመልካም ጉርበትና መርህ በማክበር የድንበር አንድነትንና የግዛት ሉዑላዊነት እንዲያከብሩ የአረብ ሊግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጠየቁ ተገለጸ።
ኩና የተባለውን የኩዌት የዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደዘገበው፤ የአረብ ሊግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኤርትራና ጅቡቲ መካከል የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ ለማርገብ ያስችላል ያለውን የመፍትሄ ሀሳብ ረቂቅ አዘጋጅቷል።
ምክር ቤቱ በረቂቅ ሀሳቡ ሁለቱ ጎረቤት አገሮች ውዝግቡን ከሚያባብሱ ተግባራት በመታቀብ ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መጠየቁን ዘገባው አመልክቷል።
የአረብ ሊግ የድንበር ውዝግቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በማድረግ ላይ ያለውን ጥረት ኤርትራ በአዎንታዊ መልኩ በመቀበል ድጋፍ እንድታደርግ አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ ፣ ከአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ እና ከአረብ ሊግ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤቶች ጋር በመሆን የአረብና የአፍሪካ አገራት በጋራ ግጭቶችን ለማስወገድ የሚያደርጉትን ጥረት ሌሎች አካላት እንዲደግፉ መጠየቁን የኩዌት የዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።