የሶማሊያ የፖለቲካ መሪዎች በአገሪቱ የወደፊት ደህንነት ላይ ትኩረት ሰጥተው መወያየት ጀመሩ

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2000/ዋኢማ/ የሶማሊያ የፖለቲካ መሪዎች በአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፋንታና በህዝባቸው ደህንነት ላይ ትኩረት ስጥተው መወያየት መጀመራቸው በሶማሊያ እየታዩ ላሉት ፖለቲካዊ መሻሻሎች አዎንታዊ ገጽታ እንዳለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

የሶማሊያ የሽግግር መንግስትና ተቃዋሚዎች በተለያዩ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያካህዱት ጉባኤ ትናንት በጂቡቲ ሲጀመር በመንግስታቱ ድርጅት የሶማሊያ ልዩ ተወካይ ሚስተር አሕመዱ ኦልድ አብደላሂ ለድርጅቱ የዜና ማዕከል እንዳስታወቁት፤ የሶማሊያ የፖለቲካ መሪዎች በአገራቸው የወደፊት ህልውና ላይ በትኩረት እየተወያዩ ነው።

በውጭ አገራት የሚሆሩ የሶማሊያ ተወላጆች ለጉባኤው መሳካት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ወጣቶችና የሁሉም የፖለቲካ መሪዎች በጉባኤው ላይ መሳተፍ ሶማሊያውያን በአገራቸው ሰላም ለማምጣት ያደረጉት በአይነቱ የመጀመሪያው መሆኑን አመልክቷል።

ሶማሊያውያን በአገራቸው ያለውን የፖለቲካ፣ የፀጥታና ሰብአዊ ቀውሶችን ለማስወገድ ከመቼውም በላይ መረባረብ እንዳለባቸው ሚስተር አብደላሂ ጠቁመው፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሶማሊያ ጉዳይ ከመሰላቸት ይልቅ ትኩረት ሰጥቶ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በመክፈቻ ስነ -ስርዓቱ ላይ የአፍሪካ ህብረት፣ የአረብ ሊግ ፣አውሮፓ ህብረትና የጂቡቲ የእስልምና ጉዳዮች ሚኒስትር ለጉባኤው ያላቸውን ድጋፍ በተወካዮቻቸው አማካይነት ገለጸዋል።

በውይይቱ ላይ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት፣ የአገሪቱ ተቃዋሚዎች ሕብረት የሆነው አላይንስ ፎር ሪ - ሊብሬሽን ኦፍ ሶማሊያ እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳታፊ መሆናቸውን የተባበሩትን መንግስታት ድርጅት የዜና ማዕከል ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።