በስልጤ ዞን ከ51 ሺ በላይ ተማሪዎች የመደበኛና አማራጭ መሰረታዊ ትምህርት በመከታተል ላይ ናቸው

ሐዋሳ ግንቦት 5/2000/ዋኢማ/ ካለፉት ዘጠኝ ወራት ጀምሮ ከ51 ሺ በላይ ተማሪዎች የመደበኛና አማራጭ መሰረታዊ ትምህርት በመከታተል ላይ መሆናቸውን በደቡብ ክልል የስልጤ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሙሃሙድ መሃመድ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በዞኑ በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ28ሺ 857 ብልጫ ማሳየቱን ያሳየ ሲሆን ለቁጥሩ መጨመር ዋናው ምክንያት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ህጻናት ትምህርት እንዲያገኙ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ቅስቀሳ በመደረጉ ነው ብለዋል።

በዚሁ ምክንያት የዞኑን የትምህርት ሽፋን ዘንድሮ መቶ በመቶ ማድረስ መቻሉን ያመለከቱት አቶ ሙሃሙድ፤ በተለይ የትምህርት ሽፋኑን በማረጋገጥ ጥራቱን ለማስጠበቅ የመንግስትና የህብረተሰቡ ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ተናገረዋል።

በትምህርት ዘመኑ የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ በተደረገው ጥረትም ከ50 በመቶ በላይ ለማድረስ መቻሉን የገለጹት አቶ ሙሃሙድ፤ የዞኑ የመምህራን ተማሪ ጥምርታና የክፍል ተማሪ ጥምርታ 1ለ65 እንዲሁም የተማሪ መጽሀፍ ጥምርታ 1ለ 1 መሆኑን አስረድተዋል ።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ 296 የአንደኛ ደረጃና አማራጭ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 2 ሺ 943 የአንደኛ ደረጃና የአመቻች መምህራን ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ከኃላፊው ገለፃ ለመረዳት መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።