መቀሌ ግንቦት 5/2000/ዋኢማ/በመቀሌ ከተማ ያለውን ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለማቃለል ስድስት ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች በመቆፈር ላይ መሆናቸውን የከተማው የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጊዴና አበበ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ በተያዘው ዓመት በተመደበ 11ሚሊየን ብር በጀትና በቱርክ ከኢስታምቡል ከተማ በተገኘ የመቆፈሪያ ማሽን ድጋፍ በከተማው እያጋጠመ ያለውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለማቃለል የውኃ ጉድጓዶች ቁፋሮ በመካሄድ ላይ ነው።
በከተማው ኪሓ በተባለ ሥፍራ እየተቆፈሩ ያሉት የውኃ ጕድጓዶች በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ በከተማው ውስጥ ያለውን 51 በመቶ የውሃ አቅርቦት ሽፋን ወደ 78 በመቶ እንደሚያደርሰው አስረድተዋል ።
በቀጣዩ አምስት ዓመታትም ከዓለም ባንክ በሚገኝ 40 ሚሊየን ብር ብድርና ከጽሕፈት ቤታቸው በሚመደበው 10 ሚሊየን ብር በጀት 20 ተጨማሪ ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶችን ለመቆፈር የሚያስችል ዝግጀት መደረጉን ገልፀዋል።
የከተማዋን ዘላቂ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለማስወገድ በእስራኤል ባለሙያዎች ሲካሄድ የነበረው የግድብ ግንባታ ጥናት በመጠናቀቁ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ግባ በታባለ ወንዝ ላይ የኮንስትራክሽን ሥራ እንደሚጀመር አቶ ጊዴና ገልጸዋል ።