ባህርዳር ግንቦት 5/2000/ ዋኢማ/ ከደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 56 ብሔረሰቦች የተወጣጡ የልዑካን ቡድን አባላት በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን ፋግታ ለኮማ ወረዳ በመገኘት የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸው ተገለጸ።
የፋግታ ለኮማ ወረዳ ማስታወቂያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና ዶክመንቴሽን ዴስክ ባለሙያ አቶ አንሙት ገነቱ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ የልዑካን ቡድን አባላቱ በወረዳው''አስማጅጉላ''በተባለ ቀበሌ በስነ-ፆታና በቤት አያያዝ ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት ከአርሶ አደሮች ጋር የልምድ ልውውጥ አካሄደዋል።
ቀበሌው በተለያዩ የስራ ዘርፎችና አስራ ስድስቱን የጤና ኤክስቴሽን ማዕቀፎች ተግባራዊ በማድረግ በኩል በዞኑ ውጤታማ በመሆኑ ለልምድ ልውውጡ መመረጡን ባለሙያው ገልጸዋል።
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ቅርርብን በማጠናከር ለአገራዊ ዕድገት በጋራ ለመስራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ የልዑካን ቡድኑ አባላት ወደ ክልላቸው ሲመለሱ በልምድ ልውውጡ የተገኙ ጠቃሚ ልምዶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደተዘጋጁ በአስተያየት መስጫ ሰነድ ላይ መግለፃቸውን ተናግረዋል።