አዲስ አበባ ግንቦት 4/2000/ዋኢማ/ተገቢ ያልሆነ የንግድ እንቅስቃሴን ለማስቀረትና ነጻ የንግድ ውድድርን ለማጎልበት የውድደር ህግንና ፖሊሲን በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ማስረጽ እንደሚገባ የፌደራል ንግድ አሰራር አጣሪ ከሞሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ አቶ ሐርቃ ሐሮዮ በግዮን ሆቴል በንግድ ውድድር ህግና ፖሊሲ ዙሪያ ያተኮረውን አውደ ጥናት ዛሬ ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ በየወቅቱ የሚለዋወጠውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማቃለል በንግዱ ማህበረሰብና በሚመለከታቸው አካላት ዘንድ የውድደር ህግና ፖሊሲን ማሳወቅ ተገቢ ነው።
የንግዱ ማህበረሰብና ህብረተሰቡ በንግድ ውድደር ህግና ፖሊሲ በመመራት በየወቅቱ በሸቀጦች ላይ የሚታየውን የዋጋ መናር ማቃለል እንደሚቻል ጠቁመው፤ የውድደር ህጉ ማደግና መዳበር ለነጻ የገበያ ውድድር ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የንግድ ውድደር ህግ ለአገር ዕድገትና ብልጽግና መሰረት እንደሆነ የገለጹት አቶ ሀርቃ ፤ የውድድሩ ጽንሰ ሀሳብ ጥራትና አስተማማኝ አገልግሎት ያለውን ዕቃ ሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበት ህግ መሆኑን ተናግረዋል።
አውደ ጥናቱ በአገሪቱ በ1995ዓ.ም የወጣው የንግድ ውድድር ህግ ዓላማዎች መታወቅ ባለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ስለማይታወቁ በዓለም አቅፍ ደረጃ ያሉ ህጎችን በመመልከት በንግደ ውድድር ስርዓት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የከትስ ኢንተርናሽናል ማዕከላዊ አስተባባሪና ምክትል ሀላፊ ሚስተር ሪጂት ሴንጉፕታ በበኩላቸው ፤ የንግድ ውድድር ህግ በአንደ አገር መኖር ለንግድ እንቅስቃሴው አይነተኛ ሚና ከመጫወቱም በተጨማሪ የህጎቹን ጽንሰ ሀሳብ ለማስረጽ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።
ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት 30 የሚሆኑ መንግስታዊና መንግሰታዊ ያልሆኑ አካላት የተገኙ ሲሆን፤በህንድና በተለያዩ አገሮች ያሉት የንግድ ውድድሮች፣ የህግና የፖሊሲ ተሞክሮዎች መቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።