በክልሉ ለጥቃቅንና አነስተና ተቋማት መስሪያ ቦታ በ270 ሚሊየን ብር ወጪ ግንባታ እየተካሄደ ነው

ሐዋሳ ግንቦት 4/2000/ዋኢማ/ በደቡብ ክልል የተቋቋሙ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን የገበያና የመስሪያ ቦታ ችግር ለመፍታት በ270 ሚሊየን በር በጀት የግንባታ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤጄንሲ አስታወቀ።

የኤጄንሲው ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን የገበያ፣ የመስሪያና ማምረቻ ቦታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ኤጄንሲው በክልሉ በተመረጡት 44 ከተሞች የህንፃ ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛል።

አሁን ከተጀመረው የህንፃ ግንባታ በተጨማሪ ቀደም ሲልም የገበያ ማበረታቻ ህገ ደንብ ፀድቆ ከ300 ሺ ብር በታች በክልሉ የሚደረጉ ጨረታዎች ለኢንተርፕራይዞች ብቻ እንዲተውና ምርቶቻቸውን ከቤቶች ልማት ጋር የማስተሳሰሩ ስራ የነበረውን የገበያ ችግር ያቃለላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ኢንተርፕራይዞች የሚፈልጉትን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ በክልሉ ውስጥ በተመረጡት 128 ቦታዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ67 ሺ በላይ ሰዎች ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን አመልክተዋል።

ኤጄንሲው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት የመስሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት ከመስጠት ባሸገር የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን በመስጠት ውጤታ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ለኢንተርፕራይዙ በመጀመሪያው ዙር ከተሰራጨው 67 ሚሊየን ብር ብድር ከ89 በመቶ በላይ ተመላሽ መደረጉን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅትም 200 ሚሊየን ብር ብድር ተዘጋጅቶ በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።