አዲስ አበባ ግንቦት 1/2000/ዋኢማ/ ባለፉት አምስት ዓመታት ለ46 ሚሊየን ሰዎች በስነ-ተዋልዶ ጤናና በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ያተኮረ ትምህርትና አገልግሎት መሰጠቱን ፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ አስታወቀ።
ድርጅቱ ዛሬ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ለአምስት ዓመታት በስነ-ተዋልዶ ጤናና በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ሲያከናውን የነበረው ስራ መጠናቀቁን አስመልክቶ በዘርፉ ያስመዘገበው ውጤት ይፋ ተደርጓል።
በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ አቶ ጥላሁን ግዴይ በዚሁ ወቅት ባቀረቡት ሪፖርት፤ ድርጅቱ በ370 ወረዳዎች ለሚገኙ 46 ሚሊየን ሰዎች የቤተሰብ ምጣኔና የስነ-ተዋልዶ ጤና ትምህርትና አገልግሎት ሰጥቷል።
በተጨማሪም ከ2ሺ 400 በላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የጤና ተቋማትን፣ የወጣቶች ማዕከላትንና ሌሎች የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመጠቀም በየዓመቱ ለአራት ሚሊየን የቤተሰብ መሪዎች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የፓዝፋንደር ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሮላይን ክሮስበይ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው በዓለም ላይ ትኩረት ሰጥቶ በስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ በመስራት ላይ ከሚገኝባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደሟ መሆኗን ጠቁመዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በዘርፉ ከታቀደው በላይ ውጤታማ ስራ መሰራቱን የጠቆሙት ምክትል ፕሬዚዳንቷ፤ ድርጅታቸው አሁን ትኩረት አድርጎ ከሰራባቸው የኦሮሚያ፣ አማራ ፣ደቡብና ትግራይ ክልሎችና አዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች ክልሎችም ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ ያሉትን ተግባራት በተሻለ መልኩ በመቀጠል ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የአገሪቱ ህዝብ በስነ-ተዋልዶ ጤና ለመድረስ የሚያስችል የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማፈላለግ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚሁ ጉባኤ ላይ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ዕርዳታ ሰጪዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።