በግድቦች ያጋጠመውን የውሃ መጠን መቀነስ ተጽዕኖን ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2000/ዋኢማ/ በኃይል ፍላጎት ማደግና በበልግ ዝናብ መቅረት ምክንያት በግድቦች ያጋጠመውን የውሃ መጠን መቀነስ ተጽዕኖ ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የመስኩ የስራ ኃላፊዎች አስታወቁ። የኤሌክትሪክ ኃይል ዕጥረትን ተከትሎ ተግባራዊ በሆነው የፈረቃ ፕሮግራም ህብረተሰቡ የሚያደረገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

የውሃ ሃብት ሚኒስትር አቶ አስፋው ዴንጋሞ፣ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑና የሌሎች የመስኩ መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፍ ዙሪያ የታየው ዕድገት የኃይል ፍላጎትን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ስላደረሰውና የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ስላልጣለ በግድቦች የሚገኘው ውሃ መጠን ቀንሷል።

የውሃ ሀብት ሚኒስትር አቶ አስፋው ዴንጋሞ እንደገለጹት፤ ባለፈው ክረምት በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉም ግድቦች መያዝ የሚችሉትን ያህል ውሃ ይዘው ነበር።

አስፋው ዴንጋሞ

ይሁንና በአገሪቱ የኃይል ፍላጎት በማደጉ ውሃው ጥቅም ላይ ሲውል መቆየቱን ጠቁመው፤ የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ የተነሳ ተጨማሪ ውሃ ወደ ግድቦች ባለመግባቱና በተፈጠረው ሙቀት የውሃ ትነት መጠን በመጨመሩ በግድቦቹ ያለው ውሃ መጠን አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በደረቃማው የአየር ሁኔታ የተነሳ በግድቦች ያጋጥም የነበረው 10 በመቶ የውሃ ትነት ወደ 20 በመቶ ማደጉ የውሃ እጥረቱን ማባባሱን ጠቁመው፤ ይህንኑ ችግር ለመቋቋም ያለውን ውሃ በመቆጠብ ለኃይል ማመንጫነት በማዋል እስከመጪው ክረምት ድረስ ችግሩን ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ በበኩላቸው፤ መንግስት የኃይል እጥረትን በዘለቄታው ለመፍታት የሚያስችለውን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይሁንና የአገሪቱን ዕድገት ተከትሎ የተከሰተው የኃይል ፍላጎት ዕድገት በደረቃማ የአየር ሁኔታ መባባሱን ጠቁመው፤ በግድቦች ያለውን ውሃ በቁጠባ በመጠቀም የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለተጠቃሚዎች በፈረቃ ማከፋፈል በማስፈለጉ ተግባራዊ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በወር ለ10 ቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደማያገኝ በወጣው ፕሮግራም መገለጹን አመልክተው፤ እስከ ሰኔ 2000 ተግባራዊ በሚሆነው በዚሁ ፕሮግራም ህዝቡ ኃይልን በቁጠባ በመጠቀም የጀመረውን ትብብር እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ምህረት ደበበ በበኩላቸው፤ አምራች ድርጅቶች የጥገና ጊዜያቸውን ኤሌክትሪክ በፈረቃ ወደሚከፋፈልባቸው ወራት በማምጣት ለተፈጠረው አገራዊ ችግር ወገናዊ ትብብራቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።