16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳካ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2000/ዋኢማ/ 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳካ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አስታወቀ። በሻምፒዮናው ምንም አይነት ቅሬታ ከየሀገራቱም ይሁን ከአትሌቶች አለመቅረቡ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ዛሬ በጽህፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው፤ 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከተጠበቀው በላይ በሁሉም መልኩ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዶ ተጠናቋል።

በፌደሬሽኑ የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባልና አቃቤ ነዋይ አቶ አማኑኤል አብርሀም፣የቴክኒክ መምሪያ ኃላፊው አቶ ዱቤ ጅሎና የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አዳም ታደሰ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ውድደሩን ደማቅና ውጤታማ ለማድረግ ለ120 ዳኞች ኢንተርናሽናል የዳኝነት ስለጠና በመስጠት ያለምንም ቅሬታ ሁሉንም ወገኖች ያረካ የዳኝነት ስራ ተካሂዷል።

በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ በተዘጋጀው 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ምንም አይነት ቅሬታና ክስ አለመቅረቡን ተናግረዋል።

እንዲሁም ውድደሩ ከ70 በላይ በሚሆኑ አገሮች በቀጥታ የቴሌቭዥን ሰርጭት የተላለፈ በመሆኑ ለአገሪቱ ገጽታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግርና አገራዊ የስፖርት አቅም ግንባታን ያጠናከረ በመሆኑ ለቀጣይ ስራ መሰረት ጥሎ ማለፉን ተናግረዋል።

በአገራችን ብዙም ባልተለመዱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት ባልተመዘገበባቸው አጫጭር ርቀት ሩጫዎች የአገራችን አትሌቶችና ሙያተኞች ልምድ የወሰዱበት ሻምፒዮና እንደነበርም ተናግረዋል።

በተለይ አገራችን በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ9ኛ ደረጃ በታች ወጥታ የማታውቅ መሆኗን ጠቁመው፤ በዚህ ውድደር ግን በ15 ሜዳሊያዎች የ3ኛ ደረጃ ማግኘቷ ውድድሩን ልዩ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል።

ውደደሩን ስኬታማ ለማድረግ በ18 ሚሊየን ብር የፌደሬሽኑ ዋና ጽህፈት ቤት ህንጻ ግንባታ፣ የማማሟቂያ ሜዳ፣ የተሟሉ የውድደር እቃዎችና ስታዲየሙን የማስተካከል ስራዎች በፌደሬሽኑ ተሰርተው ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለውድደሩ ማማርና ስኬታማነት መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውድድሩ እንዲሳካ በባለቤትነት ስሜት ያደረጉትን አሰተዋጽኦ ፌደሬሽኑ ማመስገኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።