የኢትዮጵያ የጥራትና የደረጃዎች ባለስልጣን ዓለም አቀፍ እውቅና ባገኘባቸው መስኮች የጀመረውን ስራ ቀጥሏል

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2000/ዋኢማ/የኢትዮጵያ የጥራትና የደረጃዎች ባለስልጣን ዓለም አቀፍ እውቅና ባገኘባቸው የተለያዩ የማይክሮ ባዮሎጂ የላቦራቶሪ የፍተሻ መስኮች የምግብና የምግብ ውጤቶችን በላቦራቶሪ የመፈተሽ ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ትምህርት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሲሳይ አሰፌ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የላብራቶሪ ፍተሻውን አጠናክሮ መቀጠሉ ለህብረተሰቡ ማህበራዊ ደህንነትና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

እንዲሁም ሀገሪቷ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ለማፋጠን የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ በላብራቶሪው ተፈትሸው ጥራታቸው የተረጋገጡ ምርቶች በየትኛውም ገበያ ላይ የተሻለ ተቀባይነት እንዲሚያገኙ ኃላፊው ተናግረዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን የሚሰጠው በጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ስጋ፣ ቲማቲም ድልህ፣ ወተትና የወተት ክሬም፣ ማካሮኒ፣ ፓስታና እንደ ብስኩት ያሉ ደረቅ ምግቦች ላይ ሲሆን በባለስልጣኑ ጥራታቸው ከተረጋገጠ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንደሚያገኙ ገልፀዋል።

እንዲሁም በዱቄትና የዓሳ ምርቶች ላይም የጥራት ማረጋገጫ እንደሚሰጥ የተናገሩት ሃላፊው፤ በቢራና ለስላሳ መጠጦች፣ የተለያዩ ጭማቂዎችና ውኃ ላይም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘባቸው የላቦራቶሪ ፍተሻ መስኮች በመሆናቸው የጥራት ማረጋገጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዓለም አቀፍ እውቅና ከማግኘቱ በፊት አምራቾች ምርቶቻቸውን ወደ ተለያዩ ሀገራት በመውሰድ የጥራት ደረጃውን ያስመረምሩ እንደነበርና በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ ወጪና ለጊዜ ብክነት ይጋለጡ እንደነበር ሃላፊውን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።