ባህርዳር ግንቦት 1/2000 ዓ.ም ዋኢማ/ በአክሽን የባለሙያዎች ማህበር አማካይነት በዩኒቨርስቲዎች መካከል ይካሄድ የነበረው''የአምሳለ ፍርድ ቤት ክርክር''ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በባህርዳር ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት ሰሞኑን መካሄዱ ተገለጸ።
ከፌድራልና ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተወከሉ ዳኞች ለ3 ቀናት በተመራው በዚህ የአምሳለ ፍርድ ቤት ክርክር፣ በሰብአዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ ዙሪያ መንግስታት ማሟላት ስላለባቸው ጉዳዮች፣ ቅሬታዎችና የመብት ጥሰቶች ሲያጋጥሙ ለአፍሪካ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዴት መቅረብ እንዳለበት በሚያትት ጭብጥ ላይ ከ7 ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ 21 የህግ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡
በውድድሩላይ ከመንግስት የባህርዳር፤ጅማ፤ጎንደር፤ሀሮማያና መቀሌ ዩኒቨርስቲዎች፤ከግል ደግሞ የሮያል እና አልፋ ዩኒቨርስቲ ኮሌጆች የተሳተፉ ሲሆን ከ1 ሺህ የሚበልጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተከታትለውታል፡፡
በዚህ ውድድር የጅማ ዩኒቨርስቲ የዋንጫ፤የጎንደርና የሮያል ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነዋል።
የጎንደር ዩንቨርስቲ በጥሩ ተናጋሪነትና የሃሮሚያ ዩኒቨርስቲ በጥሩ ሚሞራደም ፀሐፊነት ልዩ ተሸላሚ ሲሆኑ
በዕለቱ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የህግ ተማሪዎች ህብረት ባለፈው ወሰነ ትምህርት 4 ነጥብ ያመጡ 4 ተማሪዎችንና 3 ነጥብ 86 ነጥብ ላመጣ አንድ ተማሪ የኪስ ገንዘብም ሸልሟል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ ውብሸት ሽፈራው ለተወዳዳሪዎቹና ለተሸላሚዎቹ የተዘጋጀውን ልዩ ልዩ ሽልማት ከሰጡ በኋላ በሰሙት ንግግር የአምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር ከ3ኛ ወገን ወጥቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች ባለቤትነት መካሄዱ የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅና ከዳኝነት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ቅሬታዎችንም ለመከላከል ያስችላል።
ውድድሩ ተማሪዎች በፅንሰ ሀሳብ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ባላደራነታቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ለማየት የተቻለበት በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ውድድሩን ከተከታተሉት የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል የ3ኛ ዓመት የህግ ፋካልቲ ተማሪ የሆነው አብተው ተፈራ እና የቋንቋ 2ኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው እንይሽ ያዛቸው በሰጡት አስተያየት ይህን መሰል የውድድር መድረክ በሌሎችም የትምህርት ዘርፎች በተከታታይ ቢሰጥ በስራ አለም ስንሰማራ የሚጠበቅብንን ሀላፊነት ከወዲሁ ለማወቅ ስለሚያስችል ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው ማለታቸውን ዋልታ ዘግቧል።