አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2000/ዋኢማ/ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራታቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ለ75ሺ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ልማታዊ ባለሃብቶች በአዲሱ ሚሌኒየም ለኢትዮጵያ ህዳሴ በሚል መርህ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት፤ ባለሃብቶቹ የተሰማሩት በእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት፣ በግብርና፣ በእጣንና ሙጫ እንዲሁም በሆቴሎችና ማዕድን ልማት መስኮች ነው።
ዞኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑንና የተለያዩ አማራጮች እንዳሉት የገለጸት አቶ ንጋቱ፤ በመንግስት በኩል መሰረተ ልማቶችን የማሟላት፣ መልካም አስተዳደርን የማስፈንና ለባለሃብቶች ተገቢው ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታ መመቻቸቱ ለባለሃብቶቹ ተሳትፎ ማደግ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት የተካሄደው ፎረም በአስተዳደሩና በባለሃብቶች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት በማጠናከርና ችግሮችን በመፍታት ሌሎች ባለሃብቶች ወደ ዞኑ በመምጣት በፈለጉት የስራ መስክ እንዲሰማሩ እንደሚያበረታታቸው ጠቁመዋል።
የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳኜ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስርዓቶች የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ የዞኑ ነዋሪዎች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠው መቆየታቸውን ጠቁመው፤ አሁን ተግባራዊ በመደረግ ላይ በሚገኘው የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት ተሳትፎ ከሚያደርጉ ባለሃብቶች ልማት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
መምሪያው ለዞኑ ኢንቨስትመንት ዕድገት አመቺ የሆኑ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑንና ይህን የሚያስተባብር አንድ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸው፤ በተለይም በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በሆቴሎችና ቱሪዝም ዘርፍ በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎች መኖራቸውን አመልክተዋል።
በፎረሙ ላይ በዞኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የተሻለ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሃብቶች የዋንጫና የሰርተፍኬት ሽልማት መሰጠቱንና በፎረሙ ላይ ከ200 የሚበልጡ ባለሃብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች መሳተፋቸውን ዞኑን ማስታወቂያና ባህል ማስተባበሪያ ዋና መምሪያን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።