ባህርዳር ግንቦት 1/2000 ዓ.ም ዋኢማ/ ሙስናን መከላከልና መልካም አስተዳደር ማስፈን የሚቻለው በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚ አካላትናህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤና ቁርጠኛ አቋም ኖሯቸው ተቀናጅተው ሲሰሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ እሸቴ ተስፋዬ ከክልሉ ለተወጣጡ ከ220 በላይ የዞንና ወረዳ የህዝብ ቅሬታ ሰሚ አካላት በባህርዳር ከተማ ስለ ሙስና አጠቃላይ ምንነት የተዘጋጀውን የ5 ቀን ስልጠና በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት ሙስናን ለመከላከል አንዱ መንገድ በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚ አከላትና የህበረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ሲቻል ነው፡፡
ሙስናን ቀላልና ትልቅ ብሎ ደረጃ በማውጣት ሳይሆን ከሚያስከትለው አጠቃላይ ጥፋት አኳያ በመመዘን መከላከል ካልተቻለ የአንድ መንግስት ቅድሚያ ግዴታዎች በመባል የሚታወቁትን የአገርን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ተግባራትን ባግባቡ ለመወጣት የሚደረገውን ጥረት ለአደጋ እንደሚያጋልጠው ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በአንድ አገር መልካም አስተዳደር እየሰፈነ ነው ለማለት ከሚጠቀሱ መሰረታዊ ነጥቦች መካከል አንዱ ሙስናን ለመከላከል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ የሚመለከት ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ፣ሙስናን ተከላክሎ መገኘት ደግሞ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና የልማት ድጋፍ ለማግኘት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ስልጠናውም ሙስናን ለመከላከል የሚደረገው አገራዊ ጥረት አንዱ አካል መሆኑን አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ሙስና የሚያደርሰውን ጥፋት ግምት ውስጥ በማስገባት ከ5 ዓመት በፊት መንግስታት የሚመሩበት አለማቀፍ የፀረ-ሙስና ቃል ኪዳን ሰነድ መቀበላቸውን እና በአህጉራችንም የአፍሪካ ህብረት የፀረ-ሙስና መከላከል የቃል ኪዳን ሰነድ የሚል መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
አገራችንም ለሁለቱ ሰነዶች ተፈፃሚነት በመስራት ላይ ከመሆኗም ባሻገር ሙስናና መከላከል የህልውና ጉዳይ መሆኑን በማጤን የሙስና ወንጀል ህግ ማውጣቷን ጠቅሰዋል፡፡
ፈጣን ውሳኔ በመስጠት፤የህግ ክፍተቶች እንዲሟሉና ሙሰኞች ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ የውሳኔ ሀሳብ ለመንግስት ለማቅረብ በየደረጃው ያሉ ቅሬታ ሰሚዎች የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ የስልጠናው ተሳታፊዎች ሙስናን በመከላከል ትግል ውስጥ ምን እባል ይሆን ለሚለው ጎጂ ልማዳዊ አስተሳሰብ ሰለባ ሳይሆኑ ይህን ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ ለ200 ሺህ የክልሉ ነዋሪዎች ስለሙስና ምንነት የግንዘቤ ማስጨበጫ ትምህርት የሰጠ ሲሆን በተመረጡ 39 ወረዳዎች እና በ154 ቀበሌዎች የሙስና ገጽታን የሚያሳይ ናሙና ጥናት ማካሄዱን ተናግረዋል።
እንዲሁም 1ሺህ 800 ጥቆማዎች ቀርበውለት፤በ150 መዝገቦች ስር በ250 ተጠርጣሪ ግለሰቦች ላይ ክስ መስርቶ በ50ዎቹ ተከሳሾች ከ6 ወር እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና 10 ሺህ ብር የሚደርስ የገነዘብ ቅጣት ውሳኔ ማሰጠቱን እና ሌሎች ጉዳዮች በመታየት ላይ እንደሚገኙ አቶ እሸቴ ገልጸዋል።
ለተሳታፊዎቹ የሙስናን አለማቀፍ ገጽታ፤የመልካም አስተዳደር መሰረታዊ እሳቤዎች፤ የህዝብ ቅሬታ አቀባበልና አፈታት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ታውቋል ሲል ዋልታኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።