በትግራይ የህጻናት ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

መቀሌ ግንቦት 30/2000/ዋኢማ/በትግራይ ክልል የሚገኙ ችግረኛ ህጻናትን ለመርዳት ህብረተሰቡ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ ።

የህጻናትን ጉዳይ አስመልክቶ በክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት በዓዲግራት ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ እንደተገለጸው በክልሉ 85ሺ ወላጅ አልባ፣5ሺ 800 ጎዳና ተዳዳሪዎችና 20 ሺ አካል ጉዳተኛ ህጻናት ይገኛሉ ።

የቢሮው ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ተክለሃይማኖት ገብረመስቀል ችግረኛ ህጻናቱ ተምረው ራሳቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙ ዜጎች ለማድረግ ህብረተሰቡ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰፊ ሥራ ማከናወን እንደሚገባው አመልክተዋል ።

ህጻናቱን ለመርዳት እሰካሁን ቢሮው ከዩኒሴፍ ያገኘውን አሥር ሚሊየን ብር በክልሉ ለሚገኙ ወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያ ተቋማት በመስጠት ተቋማቱ በንግድ ፣በበግና ፍየል እርባታ ስራ ተሰማርተው ህፃናቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አብራርተዋል ።

በቀጣዩም በህጸናት ላይ የሚደረሱ በደሎችን ለማስቀረትና መብቶቻቸውን ለማስከበር በሁሉም ዞኖች የህጻናት ጉዳይ የሚታይበት ችሎቶች ለማቋቋም ዝግጅት መኖሩን ጠቁመዋል ።

በቢሮው የሲቪል ሰርቪስና ህዝብ ግኑኝነት መምሪያ ተወካይ አቶ ደሞዝ በርሄ በበኩላቸው ለችግረኛ ህጻናቱ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የተለያዩ ፕሮግራሞች ቀርፆ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቅሰው አንድ ተቋም ለአንድ ህጻን የመርዳት ባህል ሊዳብር ይገባዋል ብለዋል ።

በተጨማሪም ህጻናት ወደ ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው የሚረዱበት መንገድ ዕድሮች ፣ትምህርትቤቶችና የሃይማኖት መሪዎች የጀመሩት ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉበት አሳስበዋል።

በውይይቱ ላይ ከ46 ወረዳዎች የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈትቤት ኃላፊዎችና ከተለያዩ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች የተውጣጡ ከ90 በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።