አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2000/ዋኢማ/ በኦሮሚያ ክልል ከ635 ሺ በላይ ወጣቶች ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል ማግኘታቸውን የክልሉ ወጣቶች ጉዳይና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ። የክልሉን ወጣቶች ፌዴሬሽን ለመመስረት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተመልክቷል።
በቢሮው የወጣቶች አቅም ግንባታና ፕሮጄክት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጫልችሳ ቶለሳ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በገጠርና በከተሞች የሚገኙ 639 ሺ 655 የክልሉ ወጣቶች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የስራ ዕድሉን ያገኙት በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በባለሃብቶች በተፈጠሩላቸው ምቹ ሁኔታና በወጣቶቹ የግል ጥረት ነው።
የስራ ዕድሉን ካገኙት መካከል 454 ሺ 342 የገጠር ወጣቶች በጥቃቅን የንግድ ስራዎች፣ በግንባታ ስራ፣ በብሎኬት ማምረት፣ በድንጋይና አሸዋ ማቅረብና ሌሎች ተመሳሳይ የስራ ዘርፎች ሲሰማሩ ቀሪዎቹ በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ 185 ሺ 313 ወጣቶች ደግሞ በአነስተኛና ጥቃቅን የስራ ዘርፎች፣ ባለሃብቶች በከፈቱት የስራ መስክ፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶችና በግላቸው ጥረት የስራ ዕደል ማግኘታቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
በተያዘው ዓመት በክልሉ ለግማሽ ሚሊየን ወጣቶች የስራ ዕድል ለማስገኘት ዕቅድ መያዙን ያመለከቱት ኃላፊው፤ በዘጠኝ ወራቱ ውሰጥ ብቻ ከዕቅዱ በላይ ሊከናወን የቻለው 21 ሴክተር መስሪያ ቤቶች የወጣቶችን ጉዳይ በባለቤትነት ይዘው በመንቀሳቀሳቸው፣ ወጣቶችን የማወያየትና ግንዘቤ የማሳደግ ስራ በስፋት በመካሄዱና ወጣቱ ከጠባቂነት አስተሳሰብ ተላቆ ራሱን ለመለወጥ ከፍተኛ ተነሳሽነት በማሳየቱ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል ባለፉት ሁለት ዓመታት የሰጠው 150 ሚሊየን ተዘዋዋሪ ብድርና በተከታታይ እተመዘገበ የሚገኘው የኢኮኖሚ እድገት ለስራ ዕድሎቹ መገኘት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አቶ ጫልችሳ ተናግረዋል።
የክልሉ ወጣቶች በተደራጀ መልኩ በመንቀሳቀስ የመብቶቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑም በቀጣዩ ዓመት የወጣቶች ፌዴሬሽንን ለመመስረት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅትስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በተያዘው ዓመት ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ተዳክመው የነበሩ የወጣት ማህበራት በአዲስ መልክ እንዲደራጁ መደረጉን አመልክተዋል።
የፌዴሬሽኑ መመስረት የወጣቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለማቃለልና ተሳትፎአቸውን ለማጎልበት የሚያስል ከመሆኑም በላይ የማስፈፀም አቅማቸውን ለማሰደግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።